ሕይወት ያላት ፕላኔት
አንዳንዶች በአጋጣሚ የተከሰቱ እንደሆኑ የሚያስቧቸው በርካታ ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም ነበር፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን የሰው ልጆች እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ አላወቋቸውም ወይም ሙሉ በሙሉ አልተረዷቸውም። በአጋጣሚ የሆኑ ናቸው ከሚባሉት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
-
ምድር ፍኖተ ሐሊብ በተባለው ጋላክሲና በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያለችበት ቦታ እንዲሁም ይህች ፕላኔት ያላት ምሕዋር፣ ጋደል ማለቷ፣ የምትሽከረከርበት ፍጥነትና በዓይነቷ ልዩ የሆነች ጨረቃ ያላት መሆኑ
-
ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሏት መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና ከባቢ አየር
-
በፕላኔቷ ላይ ያለው አየርና ውኃ እንዲጣራና መጠኑ እንደተጠበቀ እንዲቀጥል የሚያደርጉ የተፈጥሮ ዑደቶች
ስለ እነዚህ ጉዳዮች እያነበብክ ስትሄድ ‘ምድር እንዲህ ያሉ ገጽታዎች ሊኖሯት የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? ወይስ በዓላማ ስለተሠራች?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
የምድር “አድራሻ”
ብዙውን ጊዜ ሰዎች አድራሻቸውን ሲጠየቁ የሚኖሩበትን አገር፣ ከተማ እንዲሁም የጎዳናውን ስም ይጠቅሳሉ። የምድርን አድራሻ በዚህ መንገድ ለመግለጽ ብንሞክር ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ የምድር “አገር” ሲሆን ፀሐይንና በዙሪያዋ የሚገኙትን ፕላኔቶች ያካተተው ሥርዓተ ፀሐይ ደግሞ “ከተማዋ” ይሆናል፤ እንዲሁም ምድር በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ የምትጓዝበት ምሕዋር “በጎዳና” ሊመሰል ይችላል። በሥነ ፈለክ መስክም ሆነ በፊዚክስ ረገድ ከፍተኛ እድገት ላይ በመደረሱ የሳይንስ ሊቃውንት ፕላኔታችን በጽንፈ ዓለም ውስጥ ልዩ በሆነ ቦታ ላይ መቀመጧ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በተመለከተ ጥልቅ የሆነ እውቀት ማግኘት ችለዋል።
እስቲ በመጀመሪያ ስለ “ከተማችን” ማለትም ስላለንበት ሥርዓተ ፀሐይ እንመልከት። የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ፍኖተ ሐሊብ በተባለው ጋላክሲ ውስጥ የሚገኝበት ቦታ በጣም ተስማሚ ነው፤ ወደ ጋላክሲው መካከለኛ ክፍል ብዙም አልተጠጋም ወይም አልራቀም። ሳይንቲስቶች “ለመኖሪያ አመቺ የሆነ ቀጠና” ብለው የሚጠሩት የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ያለበት ቦታ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮችን በትክክለኛው መጠን ይዟል። ከዚህ አካባቢ በጣም ከራቅን እነዚህ ንጥረ ነገሮች በበቂ መጠን አይገኙም፤ ወደ ጋላክሲው መካከለኛ ክፍል በጣም ከተጠጋን ደግሞ ጎጂ የሆኑ ጨረሮች በብዛት ስለሚገኙ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በጣም አደገኛ ይሆናል። ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት “የምንኖረው በጣም ምርጥ በሆነ አካባቢ ነው” በማለት ተናግሯል።1
እጅግ ተስማሚ የሆነ “ጎዳና”፦ “በከተማ” በተመሰለው በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ምድር የምትጓዝበት “ጎዳና” ወይም ምሕዋርም ቢሆን “ምርጥ” ነው። ከፀሐይ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የምድር ምሕዋር ያለበት ክልል ከመጠን በላይ ቀዝቃዛ ወይም እጅግ ሞቃት ባለመሆኑ ሕይወትን ለማቆየት ተስማሚ ነው። ከዚህም በላይ ምድር የምትጓዝበት ጎዳና ወደ ክብነት ያደላ ቅርጽ ያለው በመሆኑ ከዓመት እስከ ዓመት ከፀሐይ ያለን ርቀት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው።
ፀሐይ ደግሞ እንከን የማይወጣላት “የኃይል ማመንጫ” ነች። ፀሐይ አስተማማኝ ከመሆኗም ሌላ መጠኗም ሆነ የምታመነጨው ኃይል ተስማሚ ነው። በእርግጥም “በጣም ልዩ የሆነች ኮከብ” ተብላ መጠራቷ ተገቢ ነው።2
በጣም ጥሩ “ጎረቤት”፦ ለምድር “ጎረቤት” ምረጥ ብትባል ከጨረቃ የተሻለ ጎረቤት ማግኘት አትችልም ነበር። የጨረቃ ዳያሜትር የምድርን ዳያሜትር አንድ አራተኛ ገደማ ይሆናል። በመሆኑም በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ
ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ጨረቃዎች ጋር ስትወዳደር የእኛ ጨረቃ ከምድር አንጻር በጣም ትልቅ ናት። ይህ የሆነው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው? አይመስልም።እንዲህ የምንልበት አንዱ ምክንያት፣ ጨረቃ በውቅያኖሶች ላይ ለሚነሳው ማዕበል ዋነኛ መንስኤ ስለሆነች ነው፤ ይህ ደግሞ የምድርን ሥነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ምድር በዛቢያዋ ላይ ስትሽከረከር ንቅናቄ እንዳይኖራት ጨረቃ አስተዋጽኦ ታደርጋለች። ፕላኔቷ ምድራችን ተስማሚ የሆነ ጨረቃ ባይኖራት ኖሮ አሹረው እንደ ለቀቁት እንዝርት በዛቢያዋ ላይ ትውተረተር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ምናልባትም ወድቃ በጎኗ ትሽከረከር ነበር! ይህ ደግሞ በአየር ንብረት፣ በውቅያኖሶች ላይ በሚነሳው ማዕበልና በሌሎች ነገሮች ረገድ ለውጥ እንዲፈጠር በማድረግ አውዳሚ የሆኑ አደጋዎችን ያስከትል ነበር።
ምድር ጋደል ያለችበት መጠንና የምትሽከረከርበት ፍጥነት፦ ምድር 23.4 ዲግሪ ያህል ዘንበል ማለቷ በዓመት ውስጥ ወቅቶች እንዲፈራረቁ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር እንዲሁም በተለያዩ የምድር ክፍሎች የተለያየ የአየር ጠባይ እንዲኖር አስችሏል። ሬር ኧርዝ—ኋይ ኮምፕሌክስ ላይፍ ኢዝ አንኮመን ኢን ዚ ዩኒቨርስ የተባለው መጽሐፍ “ፕላኔታችን የምትሽከረከርበት ዛቢያ ጋደል ያለው ‘በትክክለኛው’ መጠን ይመስላል” ብሏል።3
በተጨማሪም ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ የምትሽከረከርበት ፍጥነት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት “ትክክለኛ” እንዲሆን አድርጓል። ምድር በዛቢያዋ ላይ የምትሽከረከርበት ፍጥነት አሁን ካለው በጣም ቢቀንስ ኖሮ ቀኖቹ ስለሚረዝሙ በፀሐይ በኩል ያለው የምድር ክፍል ከመጠን በላይ ይሞቅ ነበር፤ በሌላ በኩል ያለው የምድር ክፍል ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ ይሆን ነበር። ከዚህ በተቃራኒ፣ ምድር የምትሽከረከርበት ፍጥነት በጣም ቢጨምር ቀኖቹ አጥረው ምናልባትም ከጥቂት ሰዓታት ያልበለጡ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ምድር በፍጥነት መሽከርከሯ የማያባራ አውሎ ነፋስና ሌሎች አደጋዎች ያስከትል ነበር።
ምድርን እንደ ጋሻ ሆነው የሚከልሏት ነገሮች
ጠፈር፣ ገዳይ የሆኑ ጨረሮችና ሚቲሮይድ የሚባሉ ጠጣር ነገሮች የሞሉበት ስለሆነ አደገኛ ቦታ ነው። ሰማያዊ ቀለም ያላት ፕላኔታችን አደገኛ ነገሮች በሞሉበት ቀጠና ውስጥ ብትሆንም በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙም ጉዳት አያገኛትም። ለምን? ምድር እንደ ጋሻ የሆኑ በጣም አስደናቂ መከላከያዎች ስላሏት ነው፤ እነሱም ኃይለኛ የሆነ መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና ለእሷ ታስቦ የተሠራ ከባቢ አየር ናቸው።
የምድር መግነጢሳዊ መስክ፦ የምድር መካከለኛ ክፍል የኳስ ቅርጽ ያለውና የሚሽከረከር የቀለጠ ብረት ነው፤ ይህም ፕላኔታችን እስከ ጠፈር የተዘረጋ ከፍተኛ ኃይል ያለውና ሰፊ ቦታ የሚሸፍን መግነጢሳዊ መስክ እንዲኖራት አስችሏል። ለምድር እንደ ጋሻ ከለላ የሚሆንላት ይህ መግነጢሳዊ መስክ ከሕዋ የሚመጣ ጎጂ ጨረር ሙሉ በሙሉ ወደ እኛ እንዳይደርስ እንዲሁም ከፀሐይ የሚመነጩ ጎጂ ነገሮች አደጋ እንዳያስከትሉብን ይከላከልልናል። ከፀሐይ ከሚመነጩት አደገኛ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ እንደ ኤሌክትሮንና ፕሮቶን ያሉ በኃይል የተሞሉ ቅንጣቶች ያለማቋረጥ የሚፈሱበት የፀሐይ ነፋስ (ሶላር ዊንድ)፣ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ሃይድሮጂን ቦምቦች ጋር የሚመጣጠን ኃይል በደቂቃዎች ውስጥ የሚያመነጩት የፀሐይ ወላፈኖች (ሶላር ፍሌር) እንዲሁም ኮሮና በተባለው የፀሐይ ውጨኛ ክፍል ላይ የሚፈጠሩና በቢሊዮን ቶን የሚመዘን ቁስ አካል ወደ ሕዋ የሚተፉ ፍንዳታዎች (ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን)።
የምድር መግነጢሳዊ መስክ ምን ያህል ጥበቃ እንደሚያደርግልን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በገዛ ዓይንህ ማየት ትችላለህ። ሶላር ፍሌር እና ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን በምድር መግነጢሳዊ ዋልታዎች አካባቢ በሚገኘው የላይኛው የከባቢ አየር ክፍል ላይ በቀለማት ያሸበረቀ ደማቅ ብርሃን ማለትም አውሮራ እንዲታይ ያደርጋሉ።የምድር ከባቢ አየር፦ የተለያዩ ጋዞች ስብስብ የሆነውና ምድርን እንደ ብርድ ልብስ የሸፈናት ከባቢ አየር የምንተነፍሰው አየር እንድናገኝ ከማስቻሉም ሌላ ተጨማሪ ጥበቃ ያደርግልናል። ስትራቶስፌር የሚባለው የከባቢ አየር ክፍል ኦዞን የተባለ የኦክስጅን ቅንብር ይዟል፤ ኦዞን ወደ ምድር ከሚመጣው አልትራቫዮሌት ጨረር ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነውን ውጦ ያስቀረዋል። በዚህ መንገድ ይህ የኦዞን ሽፋን ሰዎችን እንዲሁም ፕላንክተን የሚባሉትን በባሕር ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ዕፅዋትንና እንስሳትን ጨምሮ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ከአደገኛ ጨረር ይከላከላል፤ ከምንተነፍሰው ኦክስጅን አብዛኛውን የምናገኘው ከፕላንክተን ነው። በስትራቶስፌር ውስጥ የሚገኘው የኦዞን መጠን ሁልጊዜ አንድ ዓይነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሁኔታው ይቀያየራል፤ የአልትራቫዮሌት ጨረሩ ይበልጥ ኃይለኛ በሚሆንበት ጊዜ የኦዞኑም መጠን ይጨምራል። ይህም የኦዞን ሽፋን ለምድር አስደናቂና አስተማማኝ ከለላ እንዲሆናት አድርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ ከባቢ አየር፣ በጠፈር ውስጥ ያሉ መጠናቸው ከአነስተኛ ቅንጣት እስከ ትልቅ ድንጋይ የሚለያዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነገሮች በምድር ላይ በየዕለቱ ከሚያደርሱት ውርጅብኝ ይከላከልልናል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በከባቢ አየር ውስጥ ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ በዚህ ጊዜ ደማቅ ብርሃን ስለሚፈጥሩ ሚቲዮር ወይም ተወርዋሪ ኮከቦች ተብለው ይጠራሉ። ይሁን እንጂ ለምድር ጋሻ ሆኖ የሚያገለግለው ከባቢ አየር እንደ ሙቀትና ብርሃን የመሳሰሉት ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ጨረሮች እንዳያልፉ አይከለክልም። እንዲያውም ከባቢ አየር ከፀሐይ የሚመጣው ሙቀት ለሁሉም የምድር ክፍል እንዲዳረስ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ምሽት ላይ ምድርን እንደ ብርድ ልብስ በመሸፈን ሙቀቱ ቶሎ እንዳይወጣ ይከላከላል።
የምድር ከባቢ አየርና መግነጢሳዊ መስክ በሚያስደንቅ መንገድ የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎች እስከ አሁንም ድረስ ስለ እነዚህ ነገሮች አሠራር ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። በምድር ላይ ሕይወት እንዲቀጥል ስላስቻሉት ዑደቶችም ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል።
ፕላኔታችን እንደ ጋሻ የሆኑላት ሁለት አስደናቂ መከላከያዎች ሊኖሯት የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው?
ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ዑደቶች
አንድ ከተማ ንጹሕ አየርና ውኃ ባያገኝ እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ቢዘጉ ብዙም ሳይቆይ በሽታና ሞት እንደሚከተል የታወቀ ነው። እስቲ አስበው፦ ሬስቶራንቶች ለምግብ መሥሪያ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችን ከሌላ ቦታ የሚያስገቡ ሲሆን ቆሻሻዎችን ደግሞ ወደ ውጪ አውጥተው ይጥላሉ፤ ፕላኔታችን ግን እንደዚህ አይደለችም። ለሕልውናችን የግድ አስፈላጊ የሆኑትን ንጹሕ አየርና ውኃ የምናገኘው ከሌላ ዓለም አይደለም፤ በምድር ላይ ያለው ቆሻሻም ቢሆን ተጭኖ ወደ ሌላ ዓለም አይላክም። ታዲያ ምድር ንጹሕና ለመኖሪያ ተስማሚ ሆና መቀጠል የቻለችው እንዴት ነው? በውኃ፣ በካርቦን፣ በኦክስጅን፣ በናይትሮጅንና በመሳሰሉት የተፈጥሮ ዑደቶች ምክንያት ነው፤ ስለ እነዚህ ዑደቶች እዚህ ጽሑፍ ላይ ቀለል ያለ ማብራሪያ ቀርቧል።
የውኃ ዑደት፦ ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነው። ማናችንም ብንሆን ያለ ውኃ ከጥቂት ቀናት በላይ መቆየት አንችልም። የውኃ ዑደት በምድር ዙሪያ ንጹሕና ለመጠጥነት የሚውል ውኃ እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል። የውኃ ዑደት ሦስት ደረጃዎች አሉት። (1) የፀሐይ ሙቀት ውኃ አላስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ተለይቶ እንዲተንና ወደ ከባቢ አየር እንዲገባ ያደርጋል። (2) የተነነው ውኃ ሲቀዘቅዝ ደመና ይፈጥራል። (3) ደመናው ደግሞ በዝናብና በበረዶ መልክ ወደ ምድር ይወርዳል። ወደ ምድር የወረደው ውኃ እንደገና ሲተን ዑደቱ በአዲስ መልክ ይጀምራል። በየዓመቱ ምን ያህል ውኃ በዚህ ዑደት ውስጥ ያልፋል? መላውን የምድር ገጽ 80 ሴንቲ ሜትር በሚደርስ ጥልቀት ሊሸፍን የሚችል ውኃ በዚህ ዑደት እንደሚያልፍ ይገመታል።4
የካርቦንና የኦክስጅን ዑደት፦ እንደምታውቀው በሕይወት ለመኖር መተንፈስ ይኸውም ወደ ሰውነትህ ኦክስጅን ማስገባትና ከሰውነትህ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ማስወጣት ያስፈልግሃል። ይሁን እንጂ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችና እንስሳት እንዲህ ዓይነት የአተነፋፈስ ሂደት ስለሚከተሉ ከባቢ አየር፣ በውስጡ ያለው ኦክስጅን አልቆ በካርቦን ዳይኦክሳይድ የማይጥለቀለቀው ለምንድን ነው? የኦክስጅን ዑደት ስላለ ነው። (1) ዕፅዋት እኛ ወደ ውጭ የምናስወጣውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወስደው ከፀሐይ ብርሃን በሚያገኙት ኃይል በመታገዝ ካርቦሃይድሬትና ኦክስጅን ያመርታሉ፤ ይህ አስደናቂ ሂደት ፎቶሲንተሲስ በመባል ይታወቃል። (2) እኛ ኦክስጅኑን ወደ ሰውነታችን ስናስገባ ዑደቱ ዙሩን ይጨርሳል። ዕፅዋት ካርቦሃይድሬትና ኦክስጅን በሚያመርቱበት ጊዜ ሁሉ አካባቢን አይበክሉም፣ ምንም ነገር አያባክኑም እንዲሁም አንዳችም ድምፅ አያሰሙም።
የናይትሮጅን ዑደት፦ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስፈልገው ሌላው ነገር ደግሞ እንደ ፕሮቲን ያሉ ኦርጋኒክ ሞለኪውሎች መመረታቸው ነው። (ሀ) እነዚህን ሞለኪውሎች ለማምረት ናይትሮጅን ያስፈልጋል። ጥሩነቱ በከባቢ አየር ውስጥ ካሉት ጋዞች 78 በመቶ የሚሆነው ናይትሮጅን ነው። ናይትሮጅን በመብረቅ አማካኝነት ዕፅዋት በቀጥታ ሊጠቀሙባቸው ወደሚችሉ ውሕዶች ይለወጣል። (ለ) ከዚያም ዕፅዋት በእነዚህ ውሕዶች ተጠቅመው ኦርጋኒክ ሞለኪውሎችን ይሠራሉ። እነዚህን ዕፅዋት የሚመገቡ እንስሳትም ናይትሮጅን ያገኛሉ። (ሐ) በመጨረሻም ዕፅዋትና እንስሳት ሲሞቱ በውስጣቸው ያሉትን የናይትሮጅን ውሕዶች ባክቴሪያዎች በመነጣጠል ይለያዩአቸዋል። በዚህ የመበስበስ ሂደት አማካኝነት ናይትሮጅን ወደ አፈርና ወደ አየር ስለሚመለስ ዑደቱ ይጠናቀቃል።
ፍጹም የሆነ ዑደት!
ሰዎች በቴክኖሎጂ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ቢደርሱም በየዓመቱ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ ብዙ ቶን የሚመዝኑ መርዛማ ቆሻሻዎችን ይጥላሉ። ምድር ግን ውስብስብ የሆኑ ኬሚካላዊ ሂደቶችን በመጠቀም ሁሉንም ዓይነት ቆሻሻዎች ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ስለምታደርግ ፍጹም የሆነ ዑደት አላት ማለት ይቻላል።
ምድር ቆሻሻ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል የምታደርግበት ሂደት ምንጩ ምን ይመስልሃል? ስለ ሃይማኖትና ሳይንስ ነክ ጉዳዮች የሚጽፉት ማይክል አንቶኒ ኮሪ “የምድር ሥነ ምህዳር እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ ቢሆን ኖሮ በተፈጥሮ ላይ የሚታየው እንዲህ ያለ ፍጹም በሆነ መልኩ የተቀናጀ ሂደት ሊኖር አይችልም ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።5 አንተስ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ?