ምዕራፍ 89
ወደ ይሁዳ ሲጓዝ በፔሪያ አስተማረ
-
ማሰናከል ከባድ በደል ነው
-
ይቅር ማለትና እምነት ማሳየት
ኢየሱስ “ከዮርዳኖስ ማዶ” በሚገኘው ፔሪያ በሚባለው አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቷል። (ዮሐንስ 10:40) አሁን በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ሊያቀና ነው።
ኢየሱስ የሚጓዘው ብቻውን አይደለም። ደቀ መዛሙርቱን እንዲሁም ቀረጥ ሰብሳቢዎችንና ኃጢአተኞችን ጨምሮ “እጅግ ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዘ” ነው። (ሉቃስ 14:25፤ 15:1) ኢየሱስ የሚናገረውንም ሆነ የሚያደርገውን ነገር የሚነቅፉት ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም አብረውት ናቸው። ኢየሱስ ስለጠፋችው በግ፣ ስለ ጠፋው ልጅ እንዲሁም ስለ ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር የሚያወሱትን ምሳሌዎች ስላካፈላቸው ሊያሰላስሉበት የሚገባ ብዙ ነገር አለ።—ሉቃስ 15:2፤ 16:14
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ሐሳብ የተናገረው በቅርቡ ተቃዋሚዎቹ የሰነዘሩበትን ነቀፌታና ትችት በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም። ቀደም ሲል በገሊላ ካስተማራቸው ነገሮች አንዳንዶቹን እንደገና ጠቀሳቸው።
ከእነዚህም መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፦ “ሰዎችን የሚያሰናክሉ ነገሮች መከሰታቸው የማይቀር ነው። ሆኖም ለመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ለዚያ ሰው ወዮለት! . . . ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤ ከተጸጸተም ይቅር በለው። በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህ እንኳ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ሰባት ጊዜ ወደ አንተ ከመጣ ይቅር ልትለው ይገባል።” (ሉቃስ 17:1-4) ጴጥሮስ መጨረሻ ላይ የተጠቀሰውን ነጥብ ሲሰማ እስከ ሰባት ጊዜ ድረስ ይቅር ስለማለት ቀደም ሲል አንስቶ የነበረውን ጥያቄ አስታውሶ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 18:21
ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሰጣቸውን ትምህርት ተግባራዊ ያደርጉ ይሆን? ኢየሱስን “እምነት ጨምርልን” ብለው ሲጠይቁት “የሰናፍጭ ዘር የሚያህል እምነት ካላችሁ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ከዚህ ተነቅለህ ባሕሩ ውስጥ ተተከል!’ ብትሉት ይታዘዛችኋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጣቸው። (ሉቃስ 17:5, 6) በእርግጥም ትንሽ እምነት እንኳ ትልቅ ነገር ማከናወን ይችላል።
በመቀጠልም ኢየሱስ ትሑት የመሆንን እና ለራስ ሚዛናዊ አመለካከት የመያዝን አስፈላጊነት ለሐዋርያቱ ለማስተማር እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ መካከል አራሽ ወይም እረኛ የሆነ ባሪያ ያለው ሰው ቢኖር፣ ባሪያው ከእርሻ ሲመለስ ‘ቶሎ ናና ወደ ማዕድ ቅረብ’ ይለዋል? ከዚህ ይልቅ ‘ራቴን አዘጋጅልኝ፤ በልቼና ጠጥቼ እስክጨርስም ድረስ አሸርጠህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ መብላትና መጠጣት ትችላለህ’ አይለውም? ባሪያው የተሰጠውን ሥራ በማከናወኑ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋል? በተመሳሳይ እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።”—ሉቃስ 17:7-10
ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የእሱን ፈቃድ የማስቀደምን አስፈላጊነት መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የአምላክ ቤተሰብ አባል በመሆን እሱን ማምለክ ትልቅ መብት እንደሆነ ማስታወስ አለባቸው።
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ፣ ማርያምና ማርታ የላኩት አንድ መልእክተኛ መጣ። የአልዓዛር እህቶች የሆኑት እነዚህ ሴቶች የሚኖሩት በይሁዳ በምትገኘው ቢታንያ ነው። መልእክተኛው “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” አለው።—ዮሐንስ 11:1-3
ኢየሱስ፣ ወዳጁ አልዓዛር በጠና እንደታመመ ቢያውቅም በሐዘን አልተዋጠም። እንዲያውም እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕመም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነው እንጂ በሞት የሚያበቃ አይደለም፤ ይህም የአምላክ ልጅ በዚህ አማካኝነት ክብር ይጎናጸፍ ዘንድ ነው።” ከዚያም ባለበት ቦታ ሁለት ቀን ከቆየ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ተመልሰን ወደ ይሁዳ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን “ረቢ፣ በቅርቡ እኮ የይሁዳ ሰዎች በድንጋይ ሊወግሩህ ፈልገው ነበር፤ ታዲያ ወደዚያ ተመልሰህ ልትሄድ ነው?” በማለት ተቃውሟቸውን ገለጹ።—ዮሐንስ 11:4, 7, 8
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “በቀን ውስጥ ብርሃን የሚሆንበት 12 ሰዓት አለ አይደል? ማንም ሰው በቀን ብርሃን የሚሄድ ከሆነ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ ምንም ነገር አያደናቅፈውም። ሆኖም በሌሊት የሚሄድ ሰው በእሱ ዘንድ ብርሃን ስለሌለ ይደናቀፋል።” (ዮሐንስ 11:9, 10) ኢየሱስ ይህን ሲል አምላክ ለአገልግሎቱ የመደበለት ጊዜ ገና እንዳላበቃ መግለጹ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ያለውን አጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይኖርበታል።
ኢየሱስ አክሎ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር እረፍት ላይ እንደሆነና እንደሚያገግም ስላሰቡ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶ ከሆነ ይሻለዋል” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አልዓዛር ሞቷል፤ . . . ያም ሆነ ይህ ወደ እሱ እንሂድ” በማለት በግልጽ ነገራቸው።—ዮሐንስ 11:11-15
ቶማስ፣ ኢየሱስ በይሁዳ ሊገደል እንደሚችል ቢገነዘብም እሱን መደገፍ ስለፈለገ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት “ከእሱ ጋር እንድንሞት አብረነው እንሂድ” አላቸው።—ዮሐንስ 11:16