ምዕራፍ ሃያ ሁለት
ፈተናዎች ቢደርሱበትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል
1, 2. ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ በቅፍርናሆም ንግግር ባቀረበበት ወቅት ምን ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል? ሆኖም ምን ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ?
ጴጥሮስ ኢየሱስን ያዳምጡት በነበሩት ሰዎች ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት በአንክሮ እየተከታተለ ነው። ቦታው ቅፍርናሆም የሚገኘው ምኩራብ ውስጥ ነው። ጴጥሮስ የሚኖረው በዚህ ከተማ ሲሆን ዓሣ የማጥመድ ሥራውንም የሚያካሂደው ቅፍርናሆም በሚገኘው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ላይ ነበር፤ አብዛኞቹ ወዳጅ ዘመዶቹና በሥራ ምክንያት የሚያውቃቸው ሰዎችም የሚኖሩት በዚሁ ከተማ ነበር። ጴጥሮስ፣ የአገሩ ሰዎች ለኢየሱስ የእሱ ዓይነት አመለካከት ይኖራቸዋል ብሎ ተስፋ አድርጎ ይሆናል፤ እንዲያውም በምድር ላይ ከኖሩት አስተማሪዎች ሁሉ ከሚበልጠው ከኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት መማር እንደሚያስደስታቸው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ዳሩ ምን ያደርጋል በዚህ ቀን ሁኔታው ጴጥሮስ እንዳሰበው ሳይሆን ቀረ።
2 ብዙዎቹ ኢየሱስን ማዳመጥ አቆሙ። አንዳንዶቹ ኢየሱስ የተናገረውን በመቃወም ሲያጉረመርሙ ይሰማ ጀመር። ይሁንና ከሁሉ በላይ ጴጥሮስን የረበሸው ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዳንዶቹ ለኢየሱስ መልእክት የሰጡት ምላሽ ነበር። መንፈሳዊ ትምህርት ሲያገኙ፣ አዲስ ነገር ሲያውቁና እውነትን ሲረዱ በፊታቸው ላይ ይታይ የነበረው ደስታ በዚህ ወቅት እንደ ጉም በኖ ጠፋ። እንዲያውም የተበሳጩ አልፎ ተርፎም በንዴት የበገኑ ይመስላሉ። አንዳንዶቹም የኢየሱስ ንግግር የሚሰቀጥጥ እንደሆነ ተናገሩ። ከዚህ በላይ ኢየሱስን ማዳመጥ ስላልፈለጉ ምኩራቡን ለቀው ሄዱ፤ እሱን መከተላቸውንም አቆሙ።—ዮሐንስ 6:60, 66ን አንብብ።
3. ጴጥሮስ የነበረው እምነት ምን እንዲያደርግ ረድቶታል?
3 ይህ ወቅት ለጴጥሮስም ሆነ ለሌሎቹ ሐዋርያት አስቸጋሪ ነበር። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ በዚያ ቀን የተናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ አልገባውም ነበር። ኢየሱስ የተናገረው ነገር እንዲሁ በደፈናው ከተወሰደ ሌሎችን ቅር ሊያሰኝ እንደሚችል ሳይረዳ አልቀረም። ታዲያ ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? ለጌታው ያለው ታማኝነት ፈተና ላይ ሲወድቅ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም። ጴጥሮስ የነበረው እምነት እንደነዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም እንዲችልና ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል የረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ሌሎች ታማኝ ሳይሆኑ ቢቀሩም እሱ ግን ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል
4, 5. ኢየሱስ ሰዎች ከእሱ ከሚጠብቁት ተቃራኒ የሆነ ነገር ያደረገው እንዴት ነበር?
4 ጴጥሮስ፣ የኢየሱስ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ግር ያሰኘው ነበር። ምክንያቱም ጌታው
ሰዎች ከሚጠብቁት ተቃራኒ የሆነ ነገር እንደሚናገርና እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ጊዜ አስተውሏል። ከአንድ ቀን በፊት እንኳ ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቦ ነበር። በዚህም የተነሳ ሰዎቹ ኢየሱስን ሊያነግሡት ሞከሩ። ይሁንና ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቅፍርናሆም እንዲሄዱ ካደረገ በኋላ ከዚያ አካባቢ ሸሽቶ ሄደ፤ ይህም ብዙዎችን አስገርሟቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ሌሊት በጀልባ እየተጓዙ ሳሉ ሌላ እንግዳ ነገር ተመለከቱ፤ ኢየሱስ በማዕበል በሚናወጠው የገሊላ ባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እምነቱን የሚያጠናክር ጠቃሚ ትምህርት አግኝቷል።5 በማግስቱ ጠዋት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሰዎቹ በጀልባ ተሳፍረው ተከትለዋቸው እንደመጡ ተረዱ። ይሁንና ከሁኔታው መገንዘብ እንደሚቻለው ሰዎቹ ተከትለዋቸው የመጡት በመንፈሳዊ ተርበው ሳይሆን ኢየሱስ እንደገና በተአምር እንዲመግባቸው ፈልገው ስለነበር ነው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ሥጋዊ አስተሳሰብ ስለነበራቸው ኢየሱስ ገሠጻቸው። (ዮሐ. 6:25-27) ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር ጀምሮት የነበረው ይህ ውይይት ቅፍርናሆም በሚገኘው ምኩራብም ቀጥሎ የነበረ ሲሆን በዚህ ጊዜም ኢየሱስ ወሳኝ ሆኖም ለመቀበል የሚከብድ አንድ እውነት በማስተማር ሕዝቡ ያልጠበቀውን ነገር ተናገረ።
6. ኢየሱስ ምን ምሳሌ ተናገረ? አድማጮቹስ ምን ምላሽ ሰጡ?
6 ኢየሱስ፣ እነዚያ ሰዎች እሱን የሥጋዊ ምግብ ምንጭ አድርገው ሳይሆን ከአምላክ የተገኘ መንፈሳዊ ዝግጅት ይኸውም ሰው ሆኖ ባሳለፈው ሕይወትም ሆነ በሞቱ ሌሎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችል አካል እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት ይፈልግ ነበር። ስለዚህ ራሱን በሙሴ ዘመን ከሰማይ ከወረደው ዳቦ ማለትም ከመና ጋር በማመሳሰል ምሳሌ ሰጣቸው። አንዳንዶቹ በተቃወሙት ጊዜ ሕይወት ማግኘት ከፈለጉ ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት አስፈላጊ መሆኑን በማብራራት በጣም ግልጽ የሆነ ምሳሌ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ይበልጥ ተቆጡ። አንዳንዶቹ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከልም ብዙዎቹ እሱን መከተላቸውን ለማቆም ወሰኑ። *—ዮሐ. 6:48-60, 66
7, 8. (ሀ) ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ገና ያልተረዳው ነገር ምን ነበር? (ለ) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ላቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠው እንዴት ነው?
7 ታዲያ ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? እሱም ቢሆን በኢየሱስ አነጋገር ግራ ተጋብቶ መሆን አለበት። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል መሞት እንዳለበት ገና አልተረዳም ነበር። ታዲያ ጴጥሮስ በዚያን ቀን ኢየሱስን ጥለውት እንደሄዱት ወላዋይ ደቀ መዛሙርት እሱም ጥሎት ለመሄድ ተፈትኖ ይሆን? በጭራሽ! ጴጥሮስን ከእነዚያ ሰዎች የተለየ እንዲሆን ያደረገው አንድ ወሳኝ ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ወደ ሐዋርያቱ ዞር ብሎ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። (ዮሐ. 6:67) ኢየሱስ የተናገረው ለ12ቱ ሐዋርያት ቢሆንም መልስ የሰጠው ጴጥሮስ ነበር። ይህ ሐዋርያ ብዙውን ጊዜ ከሌሎቹ ቀድሞ የመመለስ ልማድ ነበረው። ምናልባትም ከሌሎቹ በዕድሜ የሚበልጠው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆነ ይህ ከመካከላቸው የተሰማውን በግልጽ የሚናገረው ጴጥሮስ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ በእርግጥም ያሰበውን ነገር ከመናገር ወደኋላ ብሎ አያውቅም ማለት ይቻላል። ጴጥሮስ በዚህ ወቅት “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት በአእምሮው ውስጥ ይመላለስ የነበረውን ግሩምና ፈጽሞ የማይረሳ ሐሳብ ተናገረ።—ዮሐ. 6:68
9. ጴጥሮስ ለኢየሱስ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
9 ይህ አነጋገር ልብ የሚነካ አይደለም? ጴጥሮስ በኢየሱስ ላይ የነበረው እምነት ድንቅ የሆነ አንድ ባሕርይ ይኸውም ታማኝነት እንዲያዳብር ረድቶታል። ጴጥሮስ፣ ይሖዋ ያዘጋጀው ብቸኛው የመዳን ዝግጅት ኢየሱስ እንደሆነ በግልጽ ተገንዝቦ የነበረ ሲሆን ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት ያስተማራቸው ትምህርቶች ለመዳን እንደሚያበቁ ተረድቶ ነበር። ጴጥሮስ ግራ የሚያጋቡት አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለገ ምንም ሌላ መሄጃ እንደሌለው አውቆ ነበር።
ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች እኛ ከምናስበው የተለዩ ወይም ከግል ምርጫችን ጋር የሚጋጩ ቢሆኑም እንኳ ታማኝ መሆን ይኖርብናል
10. የጴጥሮስን ዓይነት ታማኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
10 አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? የሚያሳዝነው ነገር በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እንደሚወዱት ቢናገሩም ፈተና ሲያጋጥማቸው ለእሱ ታማኝ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ለክርስቶስ እውነተኛ ታማኝነት ማሳየት ከፈለግን ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ላስተማራቸው ነገሮች የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች እኛ ከምናስበው የተለዩ ወይም ከግል ምርጫችን ጋር የሚጋጩ ቢሆኑም እንኳ እነዚህን ትምህርቶች መማር፣ ትርጉማቸውን መረዳትና በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንድናገኝ የሚፈልገውን የዘላለም ሕይወት መውረስ የምንችለው ታማኞች ከሆንን ብቻ ነው።—መዝሙር 97:10ን አንብብ።
እርማት ቢሰጠውም ታማኝ ሆኗል
11. ኢየሱስ ተከታዮቹን ወዴት ይዟቸው ሄደ? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
11 ውጥረት የበዛበት ያ ቀን ካለፈ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ሐዋርያቱንና የተወሰኑ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ረጅም ጉዞ አደረገ። በተስፋይቱ ምድር ሰሜናዊ ጫፍ ላይ የሚገኘው በበረዶ የተሸፈነው የሄርሞን ተራራ አናት፣ አንዳንድ ጊዜ ከገሊላ ባሕር እንኳ ይታያል። ኢየሱስና ተከታዮቹ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች የሚወስደውን አቀበታማ መንገድ እየወጡ ሲሄዱ የተራራው ግዝፈት ይበልጥ ጎልቶ እየታየ ይሄዳል። * በስተ ደቡብ አቅጣጫ አብዛኛውን የተስፋይቱ ምድር ገጽታ ማየት በሚያስችለው በዚህ ማራኪ ቦታ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ተከታዮቹን አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ጠየቃቸው።
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ሕዝቡ ስለ እሱ ያለውን አመለካከት ማወቅ የፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ ለኢየሱስ የሰጠው መልስ እውነተኛ እምነት እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” አላቸው። ጴጥሮስ የዚህን ጥያቄ መልስ ለመስማት የጓጓውን ኢየሱስን ዓይን ዓይኑን ሲመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ በዚህ ሉቃስ 9:18-20
ጊዜም የጌታውን ደግነትና ጥልቅ የማስተዋል ችሎታ ማንበብ እንደቻለ መገመት አያዳግትም። ኢየሱስ አድማጮቹ ከተመለከቱትና ከሰሙት ነገር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ እንደደረሱ ማወቅ ፈልጎ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም በኢየሱስ ማንነት ዙሪያ በሰፊው የሚነገሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች በመጥቀስ ለጥያቄው መልስ ሰጡ። ይሁንና ኢየሱስ በዚህ ብቻ አልረካም። የቅርብ ተከታዮቹም እንደ ሌሎቹ የተሳሳተ አመለካከት ይኖራቸው ይሆን? በመሆኑም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው።—13 በዚህ ጊዜም ፈጠን ብሎ መልስ የሰጠው ጴጥሮስ ነበር። በአብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ የነበረውን ሐሳብ እንዲህ ሲል በግልጽና በድፍረት ተናገረ፦ “አንተ መሲሑ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ።” ጴጥሮስ ትክክለኛ መልስ በመስጠቱ ኢየሱስ በፈገግታ እያየው ከልብ ሲያመሰግነው በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል። ኢየሱስ፣ እውነተኛ እምነት ላላቸው ሰዎች ይህንን ታላቅ እውነት የገለጠላቸው ይሖዋ አምላክ እንጂ ሰው እንዳልሆነ ለጴጥሮስ አስገነዘበው። ጴጥሮስ፣ ይሖዋ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከገለጣቸው እውነቶች ሁሉ የሚበልጠውን እውነት ይኸውም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን መሲሕ ወይም ክርስቶስ ማንነት ማስተዋል ችሏል!—ማቴዎስ 16:16, 17ን አንብብ።
14. ኢየሱስ ለጴጥሮስ የትኞቹን ወሳኝ የሆኑ ኃላፊነቶች ሰጠው?
14 ጥንት በተነገረ አንድ ትንቢት ላይ ክርስቶስ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ ተብሎ ተገልጿል። (መዝ. 118:22፤ ሉቃስ 20:17) ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ትንቢቶችን በአእምሮው በመያዝ ጴጥሮስ መሲሕ መሆኑን ባወቀው ድንጋይ ወይም ዐለት ላይ ይሖዋ አንድ ጉባኤ እንደሚመሠርት ገለጸ። ከዚያም ኢየሱስ ለጴጥሮስ በዚያ ጉባኤ ውስጥ የሚያከናውናቸውን በጣም ወሳኝ የሆኑ አንዳንድ ኃላፊነቶች ሰጠው። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ኢየሱስ ለጴጥሮስ የሰጠው ከሌሎች ልቆ እንዲታይ የሚያደርገው ሥልጣን ሳይሆን ብዙ ሥራ ማከናወን የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው። ኢየሱስ “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ለጴጥሮስ ሰጥቶታል። (ማቴ. 16:19) በመሆኑም ጴጥሮስ ሦስት የተለያዩ ወገኖች ይኸውም መጀመሪያ አይሁዶች ቀጥሎ ሳምራውያን በመጨረሻም አሕዛብ ወይም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት የመግባት ተስፋ እንዲያገኙ የሚያስችለውን በር የመክፈት መብት ተሰጥቶታል።
15. ጴጥሮስ ኢየሱስን እንዲገሥጸው ያነሳሳው ምንድን ነው? ምንስ አለው?
15 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይጠበቃል፤ ይህ አባባል እውነት መሆኑም በጴጥሮስ ላይ ታይቷል። (ሉቃስ 12:48) ኢየሱስ፣ በኢየሩሳሌም የሚጠብቀውን ሥቃይና ሞት ጨምሮ ስለ መሲሑ የተነገሩ ሌሎች ወሳኝ እውነቶችን መግለጡን ቀጠለ። ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ ተረበሸ። ኢየሱስን ለብቻው ገለል አድርጎ በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” በማለት ገሠጸው።—ማቴ. 16:21, 22
16. ኢየሱስ ለጴጥሮስ እርማት የሰጠው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለሁላችንም የሚሆን ምን ጠቃሚ ምክር ይዟል?
ማቴ. 16:23፤ ማር. 8:32, 33) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለሁላችንም የሚሆን ጠቃሚ ምክር ይዟል። ብዙውን ጊዜ በአምላክ አስተሳሰብ ከመመራት ይልቅ በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመራት ይቀናናል። አንድን ሰው ለመርዳት አስበን የምናደርገው ነገር ግለሰቡ ከአምላክ ይልቅ ሰይጣንን እንዲያስደስት የሚያበረታታው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ጴጥሮስ ምን ምላሽ ሰጠ?
16 ጴጥሮስ ይህን የተናገረው ለእሱ አስቦ ስለነበር የኢየሱስ ምላሽ እንደሚያስደነግጠው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ጀርባውን ለጴጥሮስ በመስጠት፣ ተመሳሳይ ነገር እያሰቡ ሳይሆኑ ወደማይቀሩት ወደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እያየ “ከአጠገቤ ራቅ [“ወደ ኋላዬ ሂድ፣” የ1954 ትርጉም]፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው። (17. ኢየሱስ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ” ሲለው ምን ማለቱ ነበር?
17 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ “ሰይጣን” ሲለው ቃል በቃል ሰይጣን ዲያብሎስ ብሎ እየጠራው እንዳልሆነ ተገንዝቦ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ደግሞም ኢየሱስ ጴጥሮስን የተናገረው ሰይጣንን በተናገረበት መንገድ አይደለም። ኢየሱስ ሰይጣንን “ከፊቴ ራቅ” ያለው ሲሆን ጴጥሮስን ግን “ወደ ኋላዬ ሂድ” ብሎታል። (ማቴ. 4:10) ኢየሱስ ይህን ያደረገው መልካም ጎኖች ያሉትን ይህን ሐዋርያ ዓይንህን ላፈር ሊለው ፈልጎ ሳይሆን የተሳሳተ አስተሳሰቡን ለማረም ስለፈለገ ብቻ ነው። ደግሞም ጴጥሮስ እንደ እንቅፋት ከጌታው ፊት መጋረጡን ትቶ ከኋላው በመሆን ድጋፍ የሚሰጥ ተከታዩ መሆን እንደሚያስፈልገው መግለጹ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም።
ከኢየሱስ ክርስቶስና ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ጋር ይበልጥ እየተቀራረብን መሄድ የምንችለው የተሰጠንን ተግሣጽ በትሕትና የምንቀበልና ከተግሣጹም ትምህርት ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ብቻ ነው
18. ጴጥሮስ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው በምን መንገድ ነው?
18 ታዲያ ጴጥሮስ ተከራክሮ ወይም ተናዶ አሊያም አኩርፎ ይሆን? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ የተሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስን የሚከተሉ ሁሉ አልፎ አልፎ እርማት ያስፈልጋቸዋል። ከኢየሱስ ክርስቶስና ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ጋር ይበልጥ እየተቀራረብን መሄድ የምንችለው የተሰጠንን ተግሣጽ በትሕትና የምንቀበልና ከተግሣጹም ትምህርት ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ብቻ ነው።—ምሳሌ 4:13ን አንብብ።
ታማኝ መሆኑ ወሮታ አስገኝቶለታል
19. ኢየሱስ አድማጮቹን ግር የሚያሰኝ ምን ነገር ተናገረ? ጴጥሮስስ ምን አስቦ ሊሆን ይችላል?
19 ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ እንደሚከተለው በማለት አድማጮቹን ግር የሚያሰኝ ሌላ ነገር ተናገረ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።” (ማቴ. 16:) ይህ ሐሳብ የጴጥሮስን የማወቅ ጉጉት እንደቀሰቀሰው ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል? ምናልባት ጴጥሮስ በጊዜው ጠንከር ያለ እርማት ተሰጥቶት ስለነበር እንዲህ ዓይነቱን ልዩ መብት ላላገኝ እችላለሁ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። 28
20, 21. (ሀ) ጴጥሮስ ያየው ራእይ ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ። (ለ) በራእዩ ላይ የታዩት ሰዎች ያደረጉት ውይይት ጴጥሮስ አመለካከቱን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነው?
20 ይሁን እንጂ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ያዕቆብን፣ ዮሐንስንና ጴጥሮስን ይዞ “ወደ አንድ ረጅም ተራራ” ወጣ፤ ምናልባትም ይህ ተራራ ከነበሩበት ስፍራ ብዙም የማይርቀው የሄርሞን ተራራ ሊሆን ይችላል። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እንቅልፍ እየታገላቸው ስለነበር ይህ የሆነው ማታ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ ተጫጭኗቸው የነበረውን እንቅልፍ የሚያባርር አንድ ነገር ተከሰተ።—ማቴ. 17:1፤ ሉቃስ 9:28, 29, 32
21 ኢየሱስ እያዩት መለወጥ ጀመረ። የፊቱ መልክ እንደ ፀሐይ አበራ። ልብሱም ነጭ ከመሆኑ የተነሳ አንጸባረቀ። ከዚያም አንደኛው ሙሴን ሌላኛው ደግሞ ኤልያስን የሚመስሉ ሁለት ሰዎች ከኢየሱስ አጠገብ ታዩ። እነዚህ ሰዎች “በኢየሩሳሌም ሉቃስ 9:30, 31
ስለሚፈጸመው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት ሁኔታ” ከኢየሱስ ጋር ተነጋገሩ፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው እየተነጋገሩ የነበሩት ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነበር። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ሥቃይ ሊደርስበት አይገባም ብሎ ማሰቡ ስህተት እንደነበር ግልጽ ነው!—22, 23. (ሀ) ጴጥሮስ ደግና ንቁ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ በዚያ ሌሊት ምን ሌላ መብት አግኝተዋል?
22 ጴጥሮስ በሆነ መንገድ በዚህ አስደናቂ ራእይ ውስጥ መሳተፍ እንዳለበት ተሰምቶት የነበረ ከመሆኑም በላይ ራእዩ ረዘም ላለ ጊዜ ቢቆይ ደስ ሳይለው አይቀርም። ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ተለይተው ሊሄዱ ስለመሰለው ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ “መምህር፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል።” ከሞቱ ረጅም ጊዜ የሆናቸውን ሁለቱን የይሖዋ አገልጋዮች መስለው በራእይ የተገለጡት ሰዎች ድንኳን እንደማያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ይሁንና ጴጥሮስ ደግና ንቁ መሆኑ እንድትወደው አያደርግህም?—ሉቃስ 9:33
23 ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ በዚያ ሌሊት ሌላ መብት በማግኘት ተባርከዋል። በተራራው ላይ እንዳሉ ደመና መጥቶ ሸፈናቸው። ከደመናውም የይሖዋ አምላክ ድምፅ እንዲህ ሲል ተሰማ፦ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።” ከዚያም ራእዩ ሲያበቃ በተራራው ላይ ኢየሱስና እነሱ ብቻ ቀሩ።—ሉቃስ 9:34-36
24. (ሀ) ጴጥሮስ ያየው ራእይ ጥቅም ያስገኘለት እንዴት ነው? (ለ) እኛስ ከራእዩ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
24 ይህ ራእይ ለጴጥሮስም ሆነ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው! ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ በዚያ ሌሊት ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሲሆን የሚኖረው ክብር ምን ሊመስል እንደሚችል የመመልከትና ‘ግርማውን በገዛ ዓይኑ የማየት’ መብት እንዳገኘ ጽፏል። ይህ ራእይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትንቢቶች እውነት መሆናቸውን ያረጋገጠ ከመሆኑም ሌላ የጴጥሮስን እምነት በማጠናከር ወደፊት ለሚደርስበት ፈተና አዘጋጅቶታል። (2 ጴጥሮስ 1:16-19ን አንብብ።) እኛም እንደ ጴጥሮስ ይሖዋ በእኛ ላይ ለሾመው ጌታ ታማኝ መሆናችንን የምናሳይ፣ ከእሱ የምንማር፣ የሚሰጠንን ተግሣጽና እርማት የምንቀበል እንዲሁም በየዕለቱ በትሕትና የምንከተለው ከሆነ ይህ ራእይ እምነታችንን ሊያጠናክርልን ይችላል።
^ አን.6 በምኩራቡ የነበረው ሕዝብ በዚህ ዕለት የሰጠውን ምላሽ ከአንድ ቀን በፊት ኢየሱስ የአምላክ ነቢይ እንደሆነ በአድናቆት ስሜት ተውጦ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ስናወዳድር ሕዝቡ ምን ያህል ወላዋይ እንደሆነ በግልጽ ማየት እንችላለን።—ዮሐ. 6:14
^ አን.11 ኢየሱስና ተከታዮቹ ከባሕር ወለል በታች 210 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ከገሊላ ባሕር ዳርቻ ተነስተው ድንቅ የተፈጥሮ ውበት የተላበሰውን አካባቢ እያቋረጡ 350 ሜትር ገደማ ከፍታ ወዳለው ቦታ ተጓዙ፤ የመንገዱ ርዝመት 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል።