ክፍል 9
በቤተሰብ ሆናችሁ ይሖዋን አምልኩ
“ሰማይን፣ ምድርን . . . የሠራውን አምልኩ።”—ራእይ 14:7
በዚህ ብሮሹር ውስጥ እንደተማራችሁት መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰባችሁን የሚጠቅሙ ብዙ መመሪያዎች ይዟል። ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል። የእሱን አምልኮ ካስቀደማችሁ ሌሎቹ “ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል” በማለት ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:33) ይሖዋ ወዳጆቹ እንድትሆኑ ይፈልጋል። ከእሱ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቀሙ። አንድ ሰው ሊያገኘው ከሚችለው መብት ሁሉ የላቀው የአምላክ ወዳጅ መሆን ነው።—ማቴዎስ 22:37, 38
1 ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና አጠናክሩ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “‘እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ’ ይላል ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ።” (2 ቆሮንቶስ 6:18) አምላክ የቅርብ ወዳጆቹ እንድትሆኑ ይፈልጋል። ወዳጆቹ እንድትሆኑ ከሚረዷችሁ ነገሮች አንዱ ደግሞ ጸሎት ነው። ይሖዋ “ዘወትር ጸልዩ” በማለት ይጋብዛችኋል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) የልባችሁን ሐሳብና የሚያስጨንቋችሁን ነገሮች መስማት ይፈልጋል። (ፊልጵስዩስ 4:6) አባት ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ሲጸልይ የቤተሰቡ አባላት አምላክ ለእሱ ምን ያህል እውን እንደሆነ መመልከት ይችላሉ።
ለአምላክ ሐሳባችሁን ከመግለጽ በተጨማሪ እናንተም እሱን ማዳመጥ ይኖርባችኋል። ይህን ማድረግ የምትችሉት ቃሉንና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት ነው። (መዝሙር 1:1, 2) የምትማሩትን ነገር አሰላስሉበት። (መዝሙር 77:11, 12) አምላክን ለማዳመጥ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራችሁ መገኘትም ያስፈልጋችኋል።—መዝሙር 122:1-4
ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ለማጠናከር ከሚረዷችሁ ጠቃሚ መንገዶች መካከል ሌላው ደግሞ ስለ እሱ ለሰዎች መናገር ነው። ይህን አዘውትራችሁ ባደረጋችሁ መጠን ይበልጥ ወደ እሱ እየቀረባችሁ ትሄዳላችሁ።—ማቴዎስ 28:19, 20
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለጸሎት የሚሆን ጊዜ መድቡ
-
ቤተሰባችሁ ከመዝናኛ ይበልጥ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ይስጥ
2 የቤተሰብ አምልኳችሁን አስደሳች አድርጉት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:8) ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ማውጣትና አዘውትራችሁ ፕሮግራሙን መከተል ያስፈልጋችኋል። (ዘፍጥረት 18:19) ይሁን እንጂ ከዚህም የበለጠ የሚያስፈልግ ነገር አለ። አምላክ የየዕለቱ ሕይወታችሁ ክፍል መሆን አለበት። ‘በቤታችሁ ስትቀመጡ፣ በመንገድ ላይ ስትሄዱ እንዲሁም ስትተኙና ስትነሱ’ ስለ አምላክ በመናገር ቤተሰባችሁ ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንዲያጠናክር አድርጉ። (ዘዳግም 6:6, 7) ግባችሁ “እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን” በማለት እንደተናገረው እንደ ኢያሱ ይሁን።—ኢያሱ 24:15
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
እያንዳንዱ የቤተሰባችሁ አባል የሚያስፈልገውን ነገር ያገናዘበ ቋሚ የሆነ የልምምድ ፕሮግራም ይኑራችሁ