የማቴዎስ ወንጌል 26:1-75

  • ካህናት ኢየሱስን ለመግደል አሴሩ (1-5)

  • አንዲት ሴት ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት በኢየሱስ ላይ አፈሰሰች (6-13)

  • የመጨረሻው ፋሲካና ይሁዳ የፈጸመው ክህደት (14-25)

  • የጌታ ራት ተቋቋመ (26-30)

  • ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚክደው ተናገረ (31-35)

  • ኢየሱስ በጌትሴማኒ ጸለየ (36-46)

  • ኢየሱስ ተያዘ (47-56)

  • በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ለፍርድ ቀረበ (57-68)

  • ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው (69-75)

26  ኢየሱስ ይህን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2  “እንደምታውቁት ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ* ይከበራል፤+ የሰው ልጅም በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አልፎ ይሰጣል።”+ 3  በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ+ ተብሎ በሚጠራው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው 4  የተንኮል ዘዴ በመጠቀም ኢየሱስን ለመያዝና* ለመግደል ሴራ ጠነሰሱ።+ 5  ይሁን እንጂ “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይፈጠር በበዓሉ ወቅት መሆን የለበትም” ይሉ ነበር። 6  ኢየሱስ በቢታንያ፣ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን+ ቤት ሳለ 7  አንዲት ሴት በጣም ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እሱ ቀረበች፤ እየበላ ሳለም ዘይቱን ራሱ ላይ ታፈስ ጀመር። 8  ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲያዩ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? 9  ይህ ዘይት እኮ በውድ ዋጋ ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር።” 10  ኢየሱስ ስለ ምን እየተነጋገሩ እንዳለ አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። 11  ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።+ 12  ይህች ሴት ዘይቱን በሰውነቴ ላይ ስታፈስ እኔን ለቀብር ማዘጋጀቷ ነው።+ 13  እውነት እላችኋለሁ፣ በመላው ዓለም ይህ ምሥራች በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”+ 14  ከዚህ በኋላ፣ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ+ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ+ 15  “እሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው።+ እነሱም 30 የብር ሳንቲሞች* ሊሰጡት ተስማሙ።+ 16  ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። 17  የቂጣ* በዓል+ በሚከበርበት የመጀመሪያ ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።+ 18  እሱም “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህሩ “የተወሰነው ጊዜዬ ደርሷል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ” ብሏል’ በሉት” አላቸው። 19  ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ። 20  በመሸም ጊዜ+ ከ12 ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።+ 21  እየበሉ ሳሉም “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ።+ 22  እነሱም በዚህ እጅግ አዝነው ሁሉም ተራ በተራ “ጌታ ሆይ፣ እኔ እሆን?” ይሉት ጀመር። 23  እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር በሳህኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው።+ 24  እርግጥ፣ የሰው ልጅ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው+ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!+ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”+ 25  አሳልፎ ሊሰጠው የተዘጋጀው ይሁዳም “ረቢ፣ እኔ እሆን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው። 26  እየበሉም ሳሉ ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ቆረሰው፤+ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት “እንኩ፣ ብሉ። ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” አለ።+ 27  ጽዋ አንስቶም አምላክን ካመሰገነ በኋላ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፦ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤+ 28  ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ+ የሚፈሰውን+ ‘የቃል ኪዳን+ ደሜን’+ ያመለክታል። 29  ነገር ግን እላችኋለሁ፦ በአባቴ መንግሥት አዲሱን ወይን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከአሁን በኋላ ከዚህ ወይን አልጠጣም።”+ 30  በመጨረሻ የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።+ 31  ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’+ ተብሎ ስለተጻፈ በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ላይ በሚደርሰው ነገር የተነሳ ትሰናከላላችሁ። 32  ከተነሳሁ በኋላ ግን ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”+ 33  ይሁንና ጴጥሮስ መልሶ “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” አለው።+ 34  ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፣ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።+ 35  ጴጥሮስም “አብሬህ መሞት ቢያስፈልገኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” አለው።+ የቀሩት ደቀ መዛሙርትም ሁሉ እንደዚሁ አሉ። 36  ከዚያም ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ጌትሴማኒ ወደተባለ ቦታ መጣ፤+ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።+ 37  ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ከሄደ በኋላ እጅግ ያዝንና ይረበሽ ጀመር።+ 38  ከዚያም “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ።* እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።+ 39  ትንሽ ወደ ፊት ራቅ በማለት በግንባሩ ተደፍቶ “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ+ ከእኔ ይለፍ። ሆኖም እንደ እኔ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አንተ ፈቃድ ይሁን”+ ብሎ ጸለየ።+ 40  ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት እንኳ ነቅታችሁ መጠበቅ አልቻላችሁም?+ 41  ወደ ፈተና እንዳትገቡ+ ነቅታችሁ ጠብቁ፤+ ሳታሰልሱም ጸልዩ።+ እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ* ነው፤ ሥጋ* ግን ደካማ ነው።”+ 42  እንደገናም ሄዶ ለሁለተኛ ጊዜ “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሳልጠጣው ይለፍ። ካልሆነ ግን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም”+ ሲል ጸለየ። 43  ዳግመኛም ተመልሶ ሲመጣ እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ስለነበር ተኝተው አገኛቸው። 44  እንደገናም ትቷቸው ሄደና ለሦስተኛ ጊዜ ስለዚያው ነገር ደግሞ ጸለየ። 45  ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል። 46  ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።” 47  ገና እየተናገረ ሳለ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።+ 48  አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙት” በማለት ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 49  ይሁዳም በቀጥታ ወደ ኢየሱስ በመሄድ “ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። 50  ኢየሱስ ግን “ወዳጄ፣ እዚህ የተገኘህበት ዓላማ ምንድን ነው?” አለው።+ በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። 51  ሆኖም ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ሰዶ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው።+ 52  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤+ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።+ 53   ለመሆኑ በዚህች ቅጽበት ከ12 ሌጌዎን* የሚበልጡ መላእክት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ የማልችል ይመስልሃል?+ 54  እንዲህ ከሆነ ታዲያ፣ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” 55  በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ አስተምር ነበር፤+ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም።+ 56  ይህ ሁሉ የሆነው ግን በነቢያት መጻሕፍት* የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።”+ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ።+ 57   ኢየሱስን ያሰሩት ሰዎች ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ወደተሰበሰቡበት+ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ+ ወሰዱት። 58  ይሁንና ጴጥሮስ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ በርቀት ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላም መጨረሻውን ለማየት ከቤቱ አገልጋዮች ጋር ተቀመጠ።+ 59  በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል እየፈለጉ ነበር።+ 60  ይሁንና ብዙ የሐሰት ምሥክሮች ቢቀርቡም ምንም ማስረጃ አላገኙም።+ በኋላ ሁለት ሰዎች ቀርበው 61  “ይህ ሰው ‘የአምላክን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” አሉ።+ 62  በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ቆሞ “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” አለው።+ 63  ኢየሱስ ግን ዝም አለ።+ ሊቀ ካህናቱም “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” አለው።+ 64  ኢየሱስም “አንተው ራስህ ተናገርከው። ነገር ግን እላችኋለሁ፦ ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ+ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ+ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”+ አለው። 65  በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ እንዲህ አለ፦ “አምላክን ተሳድቧል! ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል? ስድቡን እንደሆነ እናንተም ሰምታችኋል። 66  እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” እነሱም “ሞት ይገባዋል”+ ብለው መለሱ። 67  ከዚያም ፊቱ ላይ ተፉበት፤+ በቡጢም መቱት።+ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት+ 68  “ክርስቶስ ሆይ፣ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን?” አሉት። 69  ጴጥሮስ ከቤት ውጭ፣ ግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት አገልጋይ ወደ እሱ መጥታ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርክ!” አለችው።+ 70  እሱ ግን “ስለ ምን እየተናገርሽ እንዳለ አላውቅም” በማለት በሁሉም ፊት ካደ። 71  ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሲሄድ ሌላ ሴት አየችውና በዚያ ለነበሩት ሰዎች “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።+ 72  እሱም “ሰውየውን አላውቀውም!” ብሎ በመማል ዳግመኛ ካደ። 73  ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአካባቢው ቆመው የነበሩት መጥተው ጴጥሮስን “አነጋገርህ* ያስታውቃል፤ በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አሉት። 74  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም!” በማለት ይምልና ራሱን ይረግም ጀመር። ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። 75  ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ”+ ሲል ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ለማሰርና።”
ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።
ወይም “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች።”
ወይም “ፈቃደኛ።”
የሰው ዘር ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለው መሆኑን ያመለክታል።
“ሌጌዎን” በጥንት የሮም ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ አንድን ትልቅ ክፍለ ሠራዊት ያመለክት ነበር። እዚህ ላይ ቃሉ ብዛትን ያመለክታል።
ወይም “ቅዱሳን መጻሕፍት።”
ወይም “አፍህ።”