ምሳሌ 21:1-31
21 የንጉሥ ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው።+
እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል።+
2 ሰው መንገዱ ሁሉ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤+ይሖዋ ግን ልብን ይመረምራል።*+
3 መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅትክክልና ፍትሐዊ የሆነ ነገር ማድረግ ይሖዋን ይበልጥ ደስ ያሰኘዋል።+
4 ትዕቢተኛ ዓይንና እብሪተኛ ልብየክፉዎች መብራት ናቸው፤ ደግሞም ኃጢአት ናቸው።+
5 የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤*+ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።+
6 በሐሰተኛ ምላስ የሚገኝ ውድ ሀብትወዲያው እንደሚጠፋ ጉም ነው፤ ገዳይ ወጥመድም ነው።*+
7 ክፉዎች ፍትሕን ማስፈን ስለማይፈልጉየሚፈጽሙት ግፍ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል።+
8 የበደለኛ ሰው መንገድ ጠማማ ነው፤የንጹሕ ሰው ሥራ ግን ቀና ነው።+
9 ከጨቅጫቃ* ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖርበጣሪያ ማዕዘን ላይ መኖር ይሻላል።+
10 ክፉ ሰው* መጥፎ ነገር ይመኛል፤+ለባልንጀራው ሞገስ አያሳይም።+
11 ፌዘኛ ሲቀጣ ተሞክሮ የሌለው ሰው ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ጥበበኛ ሰው ጥልቅ ማስተዋል ሲያገኝም እውቀት ይቀስማል።*+
12 ጻድቅ የሆነው አምላክ፣ የክፉውን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ክፉዎችንም ይጠፉ ዘንድ ይገለብጣቸዋል።+
13 ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን ሁሉ፣እሱ ራሱ ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።+
14 በድብቅ የተሰጠ ስጦታ ቁጣን ያበርዳል፤+በስውር የተሰጠ ጉቦም* ኃይለኛ ቁጣ እንዲከስም ያደርጋል።
15 ጻድቅ ፍትሐዊ ነገር ማድረግ ያስደስተዋል፤+ክፉ ድርጊት ለሚፈጽሙ ግን አስከፊ ነገር ነው።
16 ከማስተዋል መንገድ ወጥቶ የሚባዝን ሰው፣በሞት ከተረቱት ጋር ያርፋል።+
17 ፈንጠዝያ* የሚወድ ሰው ይደኸያል፤+የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድ ባለጸጋ አይሆንም።
18 ክፉ ሰው ለጻድቅ ቤዛ ነው፤ከዳተኛ የሆነ ሰውም በቅን ሰው ፋንታ ይወሰዳል።+
19 ጨቅጫቃና* ቁጡ ከሆነች ሚስት ጋር ከመኖርበምድረ በዳ መኖር ይሻላል።+
20 ውድ ሀብትና ምርጥ ዘይት በጥበበኛ ሰው ቤት ይገኛል፤+ሞኝ ሰው ግን ያለውን ያባክናል።*+
21 ጽድቅንና ታማኝ ፍቅርን የሚከታተል ሰው ሁሉሕይወትን፣ ጽድቅንና ክብርን ያገኛል።+
22 ጥበበኛ ሰው የኃያላን ሰዎች ከተማ ላይ ይወጣል፤*የሚታመኑበትንም ብርታት ያዳክማል።+
23 አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ፣ራሱን ከችግር ይጠብቃል።*+
24 በእብሪት የመሰለውን የሚያደርግ ሰውእብሪተኛና ጉረኛ ይባላል።+
25 ሰነፍ ሰው ምኞቱ ይገድለዋል፤እጆቹ መሥራት አይፈልጉምና።+
26 ቀኑን ሙሉ በስግብግብነት ሲመኝ ይውላል፤ጻድቅ ግን ምንም ሳይሰስት ይሰጣል።+
27 የክፉ ሰው መሥዋዕት አስጸያፊ ነው።+
በክፉ ዓላማ ተነሳስቶ* ሲያቀርብማ ምንኛ የከፋ ይሆናል!
28 ውሸታም ምሥክር ይጠፋል፤+በጥሞና የሚያዳምጥ ሰው ግን የምሥክርነት ቃሉ ተቀባይነት ያገኛል።*
29 ክፉ ሰው ኀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም፤+የቅን ሰው አካሄድ ግን አስተማማኝ ነው።*+
30 ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ፣ ማስተዋልም ሆነ ምክር ከንቱ ነው።+
31 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤+መዳን ግን ከይሖዋ ዘንድ ነው።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ውስጣዊ ዓላማን ይመረምራል።”
^ ወይም “ጥቅም ያስገኝለታል።”
^ “ሞትን ለሚሹ ወዲያው እንደሚጠፋ ጉም ነው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ከነዝናዛ።”
^ ወይም “የክፉ ሰው ነፍስ።”
^ ወይም “ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል።”
^ ቃል በቃል “በጉያ የተሸጎጠ ጉቦም።”
^ ወይም “ደስታ።”
^ ወይም “ነዝናዛና።”
^ ቃል በቃል “ያለውን ይውጣል።”
^ ወይም “ከተማን ድል ያደርጋል።”
^ ወይም “ነፍሱን ከችግር ይጠብቃል።”
^ ወይም “አሳፋሪ ምግባር እያለው።”
^ ቃል በቃል “ለዘላለም ይናገራል።”
^ ወይም “ቅን ሰው ግን መንገዱን አስተማማኝ ያደርጋል።”