ምሳሌ 23:1-35

  • ግብዣ ላይ ስትገኝ አስተዋይ ሁን (2)

  • ሀብት አታሳድ (4)

  • ሀብት በሮ ሊጠፋ ይችላል (5)

  • ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትሁን (20)

  • መጠጥ እንደ እባብ ይናደፋል (32)

23  ከንጉሥ ጋር ለመመገብ ስትቀመጥ፣በፊትህ ያለውን በሚገባ አስተውል፤  2  ለመብላት ብትቋምጥ* እንኳበጉሮሮህ ላይ ቢላ አስቀምጥ።*  3  የእሱ ጣፋጭ ምግብ አያስጎምጅህ፤ምግቡ አታላይ ነውና።  4  ሀብት ለማግኘት አትልፋ።+ ይህን ትተህ በማስተዋል ተመላለስ።*  5  ዓይንህን ስትጥልበት በዚያ አታገኘውም፤+የንስር ዓይነት ክንፎች አውጥቶ ወደ ሰማይ ይበርራልና።+  6  የስስታምን* ምግብ አትብላ፤ጣፋጭ ምግቡ አያስጎምጅህ፤  7  እሱ ሒሳብ እንደሚይዝ* ሰው ነውና። “ብላ፣ ጠጣ” ይልሃል፤ የሚናገረው ግን ከልቡ አይደለም።*  8  የበላሃትን ቁራሽ ምግብ ታስመልሳለህ፤የተናገርካቸው የምስጋና ቃላትም ከንቱ ይሆናሉ።  9  የምትናገራቸውን ጥበብ ያዘሉ ቃላት ስለሚንቅ+ለሞኝ ሰው ምንም አትናገር።+ 10  የጥንቱን የወሰን ምልክት ከቦታው አታንቀሳቅስ፤+ደግሞም አባት የሌላቸውን ልጆች መሬት አትያዝ። 11  የሚከራከርላቸው* ብርቱ ነውና፤እሱ ራሱ ከአንተ ጋር ይሟገትላቸዋል።+ 12  ልብህን ለተግሣጽ፣ጆሮህንም ለእውቀት ቃል ስጥ። 13  ልጅን* ከመገሠጽ ወደኋላ አትበል።+ በበትር ብትመታው አይሞትም። 14  ከመቃብር* ታድነው ዘንድ*በበትር ምታው። 15  ልጄ ሆይ፣ ልብህ ጥበበኛ ቢሆን፣የእኔ ልብ ሐሴት ያደርጋል።+ 16  ከንፈሮችህ ትክክል የሆነውን ሲናገሩውስጤ ደስ ይለዋል።* 17  ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤+ከዚህ ይልቅ ቀኑን ሙሉ ይሖዋን በመፍራት ተመላለስ፤+ 18  እንዲህ ብታደርግ የወደፊት ሕይወትህ የተሳካ ይሆናል፤+ተስፋህም ከንቱ አይሆንም። 19  ልጄ ሆይ፣ አዳምጥ፤ ጥበበኛም ሁን፤ልብህንም በትክክለኛው መንገድ ምራ። 20  ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ፣+ሥጋም ያለልክ እንደሚሰለቅጡ ሰዎች አትሁን፤*+ 21  ሰካራምና ሆዳም ይደኸያሉና፤+ድብታ ሰውን የተቦጫጨቀ ልብስ ያስለብሰዋል። 22  የወለደህን አባትህን ስማ፤እናትህንም ስላረጀች አትናቃት።+ 23  እውነትን ግዛ፤* ፈጽሞም አትሽጣት፤+ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን ገንዘብህ አድርግ።+ 24  የጻድቅ አባት ደስ ይለዋል፤ጥበበኛ ልጅ የወለደ ሁሉ በልጁ ሐሴት ያደርጋል። 25  አባትህና እናትህ ሐሴት ያደርጋሉ፤አንተን የወለደችም ደስ ይላታል። 26  ልጄ ሆይ፣ ልብህን ስጠኝ፤ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ።+ 27  ዝሙት አዳሪ ጥልቅ ጉድጓድ፣ባለጌ* ሴትም ጠባብ ጉድጓድ ናትና።+ 28  እንደ ዘራፊ ታደባለች፤+ታማኝ ያልሆኑ ወንዶችን ቁጥር ታበዛለች። 29  ዋይታ የማን ነው? ጭንቀት የማን ነው? ጠብ የማን ነው? እሮሮ የማን ነው? ያለምክንያት መቁሰል የማን ነው? የዓይን ቅላት* የማን ነው? 30  ይህ ሁሉ የሚደርሰው የወይን ጠጅ በመጠጣት ረጅም ጊዜ በሚያሳልፉ፣+የተደባለቀም ወይን ጠጅ ፍለጋ በሚዞሩ* ሰዎች ላይ ነው። 31  በብርጭቆ ውስጥ ሲያንጸባርቅ፣እየጣፈጠም ሲወርድ በወይን ጠጅ ቅላት ዓይንህ አይማረክ፤ 32  በመጨረሻ እንደ እባብ ይናደፋልና፤እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል። 33  ዓይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤ልብህም ጠማማ ነገር ይናገራል።+ 34  በባሕር መካከል እንደተኛ፣በመርከብ ምሰሶም ጫፍ ላይ እንደተጋደመ ሰው ትሆናለህ። 35  እንዲህ ትላለህ፦ “መቱኝ፤ ሆኖም አልተሰማኝም።* ደበደቡኝ፤ ሆኖም አልታወቀኝም። ተጨማሪ መጠጥ እጠጣ ዘንድ* የምነቃው መቼ ነው?”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በምኞት የተሞላች ነፍስ ብትኖርህ።”
ወይም “ራስህን ተቆጣጠር።”
“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመራ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ክፉ ዓይን ያለው ሰው የሚያቀርበውን።”
ወይም “በነፍሱ እንደሚያሰላ።”
ቃል በቃል “ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።”
ቃል በቃል “የሚዋጃቸው።”
ወይም “ሕፃንን፤ ወጣትን።”
ወይም “ከሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍሱን ከመቃብር ታድናት ዘንድ።”
ቃል በቃል “ኩላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል።”
ወይም “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋም ያለልክ ከሚሰለቅጡ ሰዎች ጋር አትወዳጅ።”
ወይም “አግኝ።”
ቃል በቃል “ባዕድ።” ምሳሌ 2:16ን ተመልከት።
ወይም “መፍዘዝ።”
ወይም “ለመቀማመስ በሚሰባሰቡ።”
ወይም “አላመመኝም።”
ወይም “መጠጡን ደግሜ እሻዋለሁ።”