ኢሳይያስ 65:1-25
65 “እኔን ላልጠየቁ ሰዎች ተገለጥኩ፤ላልፈለጉኝ ሰዎች ተገኘሁ።+
ስሜን ላልጠራ ብሔር ‘እነሆኝ፤ እነሆኝ!’ አልኩ።+
2 የራሳቸውን ሐሳብ እየተከተሉ፣+መልካም ባልሆነ መንገድ ወደሚሄዱ+ግትር ሰዎች ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ፤+
3 እነሱ ዘወትር በፊቴ እኔን የሚያስከፋ ነገር ይፈጽማሉ፤+በአትክልት ቦታዎች ይሠዋሉ፤+ በጡቦችም ላይ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርባሉ።
4 በመቃብር መካከል ይቀመጣሉ፤+በተሰወሩ ቦታዎችም* ውስጥ ያድራሉ፤የአሳማ ሥጋ ይበላሉ፤+ዕቃዎቻቸው ጸያፍ* በሆኑ ነገሮች መረቅ የተሞሉ ናቸው።+
5 ‘እዚያው ባለህበት ሁን፤ አትጠጋኝ፤እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና’* ይላሉ።
እነዚህ ሰዎች በአፍንጫዬ እንዳለ ጭስ፣ ቀኑን ሙሉ እንደሚነድ እሳት ናቸው።
6 እነሆ፣ በፊቴ ተጽፏል፤እኔ ዝም አልልም፤ከዚህ ይልቅ እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤+ብድራቱን ሙሉ በሙሉ እመልስባቸዋለሁ፤*
7 ይህን የማደርገው እነሱ በሠሩት በደልና አባቶቻቸው በሠሩት በደል የተነሳ ነው”+ ይላል ይሖዋ።
“ምክንያቱም በተራሮች ላይ የሚጨስ መሥዋዕት አቅርበዋል፤በኮረብቶችም ላይ አዋርደውኛል፤+እኔም በመጀመሪያ፣ ዋጋቸውን ሙሉ በሙሉ እከፍላቸዋለሁ።”*
8 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“አዲስ ወይን፣ በወይን ዘለላ ውስጥ ሲገኝአንድ ሰው ‘በውስጡ ጥሩ ነገር* ስላለ አታጥፋው’ እንደሚል፣
እኔም ለአገልጋዮቼ ስል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ሁሉንም አላጠፋቸውም።+
9 ከያዕቆብ ዘርን፣ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤+የመረጥኳቸው ምድሪቱን ይወርሳሉ፤አገልጋዮቼም በዚያ ይኖራሉ።+
10 እኔን ለሚፈልገኝ ሕዝቤ፣ሳሮን+ የበጎች መሰማሪያ፣የአኮርም ሸለቆ*+ የከብቶች ማረፊያ ይሆናል።
11 እናንተ ግን ይሖዋን ከተዉት፣+ቅዱስ ተራራዬን ከረሱት፣+መልካም ዕድል ለተባለ አምላክ ማዕድ ካሰናዱት፣ዕጣ ለተባለም አምላክ የተደባለቀ ወይን ጠጅ በዋንጫ ከሞሉት ሰዎች መካከል ናችሁ።
12 በመሆኑም ዕጣችሁ በሰይፍ መውደቅ ይሆናል፤+ሁላችሁም ለመታረድ ታጎነብሳላችሁ፤+ምክንያቱም ስጣራ አልመለሳችሁም፤ስናገር አልሰማችሁም፤+በዓይኔ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ማድረጋችሁን ቀጠላችሁ፤እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጣችሁ።”+
13 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ።+
እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ፤+ እናንተ ግን ትጠማላችሁ።
እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤+ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ።+
14 እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ፤እናንተ ግን ከልባችሁ ሐዘን የተነሳ ትጮኻላችሁ፤መንፈሳችሁ ስለተሰበረም ዋይ ዋይ ትላላችሁ።
15 የተመረጡት አገልጋዮቼ ለእርግማን የሚጠቀሙበት ስም ትታችሁ ታልፋላችሁ፤ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋም እያንዳንዳችሁን ይገድላችኋል፤የራሱን አገልጋዮች ግን በሌላ ስም ይጠራቸዋል፤+
16 ስለዚህ በምድር ላይ በረከትን የሚሻ ሁሉበእውነት አምላክ* ይባረካል፤በምድር ላይ መሐላ የሚምልም ሁሉበእውነት አምላክ* ይምላል።+
ቀደም ሲል የነበሩት የሚያስጨንቁ ነገሮች* ይረሳሉና፤ከዓይኔ ይሰወራሉ።+
17 እነሆ፣ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነውና፤+የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤*ወደ ልብም አይገቡም።+
18 በመሆኑም በምፈጥረው ነገር ለዘላለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።
እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ሕዝቧንም ለሐሴት እፈጥራለሁና።+
19 እኔም በኢየሩሳሌም ደስ እሰኛለሁ፤ በሕዝቤም ሐሴት አደርጋለሁ፤+ከዚህ በኋላ በውስጧ የለቅሶ ድምፅም ሆነ የጭንቅ ጩኸት አይሰማም።”+
20 “ከእንግዲህ በዚያ፣ ለጥቂት ቀን ብቻ የሚኖር ሕፃንም ሆነዕድሜ የማይጠግብ አረጋዊ አይኖርም።
መቶ ዓመት ሞልቶት የሚሞት ማንኛውም ሰው ገና በልጅነቱ እንደተቀጨ ይቆጠራል፤ኃጢአተኛው መቶ ዓመት ቢሞላውም እንኳ ይረገማል።*
21 ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤+ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።+
22 እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም።
የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፤+የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።
23 በከንቱ አይለፉም፤+ወይም ለመከራ የሚዳረጉ ልጆች አይወልዱም፤ምክንያቱም እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው+ይሖዋ የባረከው ዘር ናቸው።+
24 ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤እየተናገሩ ሳሉ እሰማቸዋለሁ።
25 ተኩላና የበግ ግልገል በአንድነት ይበላሉ፤አንበሳ እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤+የእባብም መብል አፈር ይሆናል።
በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳትም ሆነ ጥፋት አያደርሱም”+ ይላል ይሖዋ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “በመጠበቂያ ጎጆዎችም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ርኩስ።”
^ “ቅድስናዬን ወደ አንተ አስተላልፋለሁና” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “በጉያቸው አስታቅፋቸዋለሁ።”
^ ቃል በቃል “በጉያቸው አስታቅፋቸዋለሁ።”
^ ቃል በቃል “በረከት።”
^ ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
^ ወይም “ታማኝ በሆነው አምላክ።” ቃል በቃል “በአሜን አምላክ።”
^ ወይም “ታማኝ በሆነው አምላክ።” ቃል በቃል “በአሜን አምላክ።”
^ ወይም “ችግሮች።”
^ ወይም “አይታወሱም።”
^ “አንድ ሰው መቶ ዓመት ባይሞላው እንደተረገመ ይቆጠራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።