የሐዋርያት ሥራ 18:1-28
18 ከዚህ በኋላ ከአቴንስ ተነስቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።
2 በዚያም የጳንጦስ ተወላጅ የሆነ አቂላ+ የተባለ አይሁዳዊ አገኘ፤ ይህ ሰው ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ባዘዘው መሠረት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር በቅርቡ ከጣሊያን የመጣ ነበር። ጳውሎስም ወደ እነሱ ሄደ፤
3 ሙያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ እነሱ ቤት ተቀምጦ አብሯቸው ይሠራ ነበር፤+ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር።
4 በየሰንበቱ+ በምኩራብ+ ንግግር እየሰጠ* አይሁዳውያንንና ግሪካውያንን ያሳምን ነበር።
5 ሲላስና+ ጢሞቴዎስ+ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስ ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ፤ ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ መሆኑን እያስረዳ ለአይሁዳውያን ይመሠክር ነበር።+
6 አይሁዳውያኑ እሱን መቃወማቸውንና መሳደባቸውን በቀጠሉ ጊዜ ግን ልብሱን አራግፎ*+ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን።+ እኔ ንጹሕ ነኝ።+ ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።+
7 ከዚያም* ተነስቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደሚባል አምላክን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህ ሰው ቤት ምኩራቡ አጠገብ ነበር።
8 የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ+ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ። መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር።
9 ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤
10 እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ+ ማንም አንተን ሊያጠቃና ሊጎዳህ አይችልም፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።”
11 ስለዚህ በመካከላቸው የአምላክን ቃል እያስተማረ ለአንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቆየ።
12 የሮም አገረ ገዢ* የሆነው ጋልዮስ አካይያን ያስተዳድር በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን ግንባር ፈጥረው በጳውሎስ ላይ ተነሱበት፤ በፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም
13 እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ሕጉን በሚጻረር መንገድ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ እያሳመነ ነው።”
14 ይሁንና ጳውሎስ ሊናገር ሲል ጋልዮስ አይሁዳውያንን እንዲህ አላቸው፦ “አይሁዳውያን ሆይ፣ አንድ ዓይነት በደል ወይም ከባድ ወንጀል ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ በትዕግሥት ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር።
15 ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ+ ከሆነ እናንተው ጨርሱት። እኔ እንዲህ ላለ ነገር ፈራጅ መሆን አልፈልግም።”
16 ከዚያም ከፍርድ ወንበሩ ፊት አስወጣቸው።
17 በዚህ ጊዜ የምኩራብ አለቃ የሆነውን ሶስቴንስን+ ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ይደበድቡት ጀመር። ጋልዮስ ግን እንዲህ ባሉ ጉዳዮች እጁን አያስገባም ነበር።
18 ይሁንና ጳውሎስ በዚያ ለተወሰኑ ቀናት ከቆየ በኋላ ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለት ስለነበረበትም ክንክራኦስ+ በተባለ ቦታ ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ።
19 ኤፌሶን በደረሱም ጊዜ እነሱን እዚያው ተዋቸው፤ እሱ ግን ወደ ምኩራብ ገብቶ ከአይሁዳውያን ጋር ይወያይ ነበር።+
20 ምንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሰነብት አጥብቀው ቢለምኑትም ፈቃደኛ አልሆነም፤
21 ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ከፈቀደ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሎ ተሰናበታቸው። ከዚያም ከኤፌሶን መርከብ ተሳፍሮ
22 ወደ ቂሳርያ ወረደ። ወጥቶም * ለጉባኤው ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።+
23 በዚያም የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ከዚያ ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ+ አገሮች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ አበረታታ።+
24 በዚህ ጊዜ የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ+ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እሱም ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ያለውና ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።
25 ይህ ሰው የይሖዋን* መንገድ የተማረ* ሲሆን በመንፈስ* እየተቃጠለ ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እሱ የሚያውቀው ዮሐንስ ይሰብከው ስለነበረው ጥምቀት ብቻ ነበር።
26 እሱም በምኩራብ ውስጥ በድፍረት መናገር ጀመረ፤ ጵርስቅላና አቂላም+ በሰሙት ጊዜ ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት።
27 በተጨማሪም ወደ አካይያ መሄድ ፈልጎ ስለነበር ወንድሞች በዚያ የሚገኙት ደቀ መዛሙርት ጥሩ አቀባበል እንዲያደርጉለት የሚያሳስብ ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያ በደረሰ ጊዜም በአምላክ ጸጋ አማኞች የሆኑትን ሰዎች በእጅጉ ረዳቸው፤
28 ከአይሁዳውያን ጋር በይፋ በመወያየት ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እያሳያቸው ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመግለጽ ትክክል እንዳልሆኑ በጋለ ስሜት ያስረዳቸው ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “እያስረዳ።”
^ ልብስን ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።
^ ምኩራቡን ያመለክታል።
^ የሮም የአንድ አውራጃ ገዢ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወደ ኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም።
^ ወይም “በቃል የተማረ።”
^ የአምላክን መንፈስ ያመለክታል።