የዮሐንስ ወንጌል 11:1-57

  • አልዓዛር ሞተ (1-16)

  • ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን አጽናናቸው (17-37)

  • ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው (38-44)

  • ኢየሱስን ለመግደል የተጠነሰሰ ሴራ (45-57)

11  ማርያምና እህቷ ማርታ+ በሚኖሩበት መንደር በቢታንያ አልዓዛር የተባለ ሰው ታሞ ነበር።  ማርያም በጌታ ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ያፈሰሰችውና በፀጉሯ እግሩን ያበሰችው+ ሴት ስትሆን የታመመውም፣ ወንድሟ አልዓዛር ነበር።  ስለዚህ እህቶቹ “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” ሲሉ መልእክት ላኩበት።  ኢየሱስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “ይህ ሕመም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነው+ እንጂ በሞት የሚያበቃ አይደለም፤ ይህም የአምላክ ልጅ በዚህ አማካኝነት ክብር ይጎናጸፍ ዘንድ ነው” አለ።  ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።  ይሁን እንጂ አልዓዛር መታመሙን ከሰማ በኋላ በዚያው በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቆየ።  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን “ተመልሰን ወደ ይሁዳ እንሂድ” አላቸው።  ደቀ መዛሙርቱ ግን “ረቢ፣+ በቅርቡ እኮ የይሁዳ ሰዎች በድንጋይ ሊወግሩህ ፈልገው ነበር፤+ ታዲያ ወደዚያ ተመልሰህ ልትሄድ ነው?” አሉት።  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ብርሃን የሚሆንበት 12 ሰዓት አለ አይደል?+ ማንም ሰው በቀን ብርሃን የሚሄድ ከሆነ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ ምንም ነገር አያደናቅፈውም። 10  ሆኖም በሌሊት የሚሄድ ሰው በእሱ ዘንድ ብርሃን ስለሌለ ይደናቀፋል።” 11  ይህን ከነገራቸው በኋላም “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤+ እኔም ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” አላቸው። 12  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶ ከሆነ ይሻለዋል” አሉት። 13  ይሁንና ኢየሱስ የተናገረው ስለመሞቱ ነበር። እነሱ ግን ለማረፍ ብሎ እንቅልፍ ስለመተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። 14  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቷል፤+ 15  ታምኑ ዘንድ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል። ያም ሆነ ይህ ወደ እሱ እንሂድ።” 16  በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት “ከእሱ ጋር እንድንሞት አብረነው እንሂድ” አላቸው።+ 17  ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር በመቃብር ውስጥ አራት ቀን እንደሆነው አወቀ። 18  ቢታንያ ለኢየሩሳሌም ቅርብ የነበረች ሲሆን ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል* ርቀት ላይ ትገኝ ነበር። 19  ወንድማቸውን በሞት ያጡትን ማርታንና ማርያምን ለማጽናናት ብዙ አይሁዳውያን መጥተው ነበር። 20  ማርታ፣ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም+ ግን እዚያው ቤት ቀረች። 21  ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። 22  አሁንም ቢሆን አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ።” 23  ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። 24  ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው።+ 25  ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ።+ በእኔ የሚያምን* ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል፤ 26  በሕይወት ያለና በእኔ የሚያምን ሁሉ ደግሞ ፈጽሞ አይሞትም።+ ይህን ታምኛለሽ?” 27  እሷም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። 28  ይህን ካለች በኋላም ሄዳ እህቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታት “መምህሩ+ መጥቷል፤ እየጠራሽ ነው” አለቻት። 29  ማርያምም ይህን ስትሰማ በፍጥነት ተነስታ ወደ እሱ ሄደች። 30  ይሁንና ኢየሱስ እዚያው ማርታ ያገኘችው ቦታ ነበር እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። 31  እሷን እያጽናኑ በቤት አብረዋት የነበሩ አይሁዳውያንም ማርያም ፈጥና ተነስታ ስትወጣ ሲያዩ ወደ መቃብሩ+ ሄዳ ልታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። 32  ማርያምም ኢየሱስ የነበረበት ቦታ ደርሳ ባየችው ጊዜ እግሩ ላይ ተደፋች፤ ከዚያም “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። 33  ኢየሱስ እሷ ስታለቅስና አብረዋት የመጡት አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ፤* ተረበሸም። 34  እሱም “የት ነው ያኖራችሁት?” አለ። እነሱም “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ” አሉት። 35  ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።+ 36  በዚህ ጊዜ አይሁዳውያኑ “እንዴት ይወደው እንደነበር ተመልከቱ!” አሉ። 37  ሆኖም ከእነሱ መካከል አንዳንዶች “የዓይነ ስውሩን ዓይን ያበራው ይህ ሰው+ ይሄኛውንም እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ። 38  ከዚያም ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ታውኮ ወደ መቃብሩ መጣ። መቃብሩ ዋሻ ሲሆን በድንጋይም ተዘግቶ ነበር። 39  ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። የሟቹ እህት ማርታም “ጌታ ሆይ፣ አራት ቀን ስለሆነው አሁን ይሸታል” አለችው። 40  ኢየሱስም “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት።+ 41  ስለዚህ ድንጋዩን አነሱት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልክቶ+ እንዲህ አለ፦ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42  እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ይህን ያልኩት ግን እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።”+ 43  ይህን ከተናገረ በኋላ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ።+ 44  የሞተው ሰው እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ ተጠምጥሞ ነበር። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ” አላቸው። 45  በመሆኑም ወደ ማርያም መጥተው ከነበሩትና ያደረገውን ነገር ካዩት አይሁዳውያን መካከል ብዙዎቹ በእሱ አመኑ፤+ 46  አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ነገሯቸው። 47  ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የሳንሄድሪንን ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?+ 48  እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና* ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” 49  ሆኖም ከመካከላቸው አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ+ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ 50  ደግሞም ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ፣ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት እንደሚሻል ማሰብ ተስኗችኋል።” 51  ይሁንና ይህን የተናገረው ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት ስለነበረ ኢየሱስ ለሕዝቡ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ 52  የሚሞተውም ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ተበታትነው ያሉትን የአምላክ ልጆችም አንድ ላይ መሰብሰብ ይችል ዘንድ ነው። 53   ስለዚህ ከዚያን ቀን አንስቶ ሊገድሉት አሴሩ። 54  በመሆኑም ኢየሱስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአይሁዳውያን መካከል በይፋ መንቀሳቀስ አቆመ፤ ከዚህ ይልቅ በምድረ በዳ አቅራቢያ ወዳለ ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ኤፍሬም+ ተብላ በምትጠራ ከተማ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 55  በዚህ ወቅት የአይሁዳውያን ፋሲካ+ ቀርቦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ከፋሲካ በፊት የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም ከገጠር ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56  ኢየሱስንም ይፈልጉት ጀመር፤ በቤተ መቅደሱም ቆመው እርስ በርሳቸው “ምን ይመስላችኋል? ጭራሽ ወደ በዓሉ አይመጣ ይሆን?” ይባባሉ ነበር። 57   የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን መያዝ* እንዲችሉ እሱ ያለበትን ቦታ የሚያውቅ ሁሉ እንዲጠቁማቸው አዘው ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መንትያ።”
ቃል በቃል “15 ስታዲዮን ገደማ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”
ቃል በቃል “በመንፈሱ ቃተተ።”
ቤተ መቅደሱን ያመለክታል።
ወይም “ማሰር።”