ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 5:1-28
5 እንግዲህ ወንድሞች፣ ጊዜያትንና ወቅቶችን በተመለከተ ምንም ነገር እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም።
2 የይሖዋ* ቀን+ የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ+ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁና።
3 “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ሲሉ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤+ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።
4 እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤
5 እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁና።+ እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ልጆች አይደለንም።+
6 ስለዚህ ነቅተን እንኑር+ እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ+ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።+
7 የሚያንቀላፉ ሰዎች፣ የሚያንቀላፉት በሌሊት ነው፤ የሚሰክሩም ቢሆኑ የሚሰክሩት በሌሊት ነው።+
8 የቀን ልጆች የሆንነው እኛ ግን የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ ደግሞም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ፤+
9 ምክንያቱም አምላክ የመረጠን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን እንድናገኝ+ ነው እንጂ ለቁጣ አይደለም።
10 እሱ በሕይወት ብንኖርም ሆነ ብናንቀላፋ* አብረነው እንድንኖር+ ለእኛ ሞቶልናል።+
11 ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ* እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።+
12 እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤
13 በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን።+ እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።+
14 በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤*+ የተጨነቁትን* አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።+
15 ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።+
16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።+
17 ዘወትር ጸልዩ።+
18 ለሁሉም ነገር አመስግኑ።+ አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው።
19 የመንፈስን እሳት አታጥፉ።+
20 ትንቢቶችን አትናቁ።+
21 ሁሉንም ነገር መርምሩ፤+ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።
22 ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ።+
23 የሰላም አምላክ ራሱ ሙሉ በሙሉ ይቀድሳችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና* አካላችሁ በማንኛውም ረገድ ጤናማ ይሁን፤ ደግሞም ነቀፋ አይገኝበት።+
24 የጠራችሁ ታማኝ ነው፤ ይህን በእርግጥ ያደርገዋል።
25 ወንድሞች፣ ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ።+
26 ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው።
27 ይህ ደብዳቤ ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ።+
28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሞት ብናንቀላፋ።”
^ ወይም “ተጽናኑ።”
^ ወይም “ምከሯቸው።”
^ ወይም “ተስፋ የቆረጡትን።” ቃል በቃል “ትንሽ ነፍስ ያላቸውን።”
^ ወይም “ሕይወታችሁና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።