በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በዘመናችን ጠቃሚ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በዘመናችን ጠቃሚ ነው?

አንዳንዶች ‘አይደለም’ ይላሉ። አንድ ሐኪም፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለማግኘት መሞከር በ1920ዎቹ በተዘጋጀ የኬሚስትሪ መጽሐፍ ከማስተማር ተለይቶ እንደማይታይ ተናግረዋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ‘አዲስና ዘመናዊ የሆነ ኮምፒውተርን አጠቃቀም ለማወቅ ለአንድ የቆየና ከአገልግሎት ውጭ የሆነ ኮምፒዩተር የተዘጋጀን መመሪያ ትጠቀማለህ?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። በሌላ አነጋገር እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ጨርሶ ጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል መግለጻቸው ነው።

ለነገሩ ዘመናዊ በሆነውና በቴክኖሎጂ በመጠቀው በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ባለ ጥንታዊ መመሪያ የምንጠቀምበት ምን ምክንያት ይኖራል? ደግሞም እኮ ወቅታዊ የሆኑ ምክሮችንና መመሪያዎችን ስፍር ቁጥር በሌላቸው ድረ ገጾችና ሰዎች አስተያየታቸውን በሚያሰፍሩባቸው የኢንተርኔት ገጾች (blogs) ላይ በማንኛውም ጊዜ ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም በቴሌቪዥን በሚቀርቡ የውይይት መድረኮች ላይ የሥነ አእምሮ ምሁራን፣ የአኗኗር ዘይቤ አማካሪዎች (lifestyle gurus) እና ደራሲዎች ሙያዊ ትንተና ይሰጣሉ። የመጻሕፍት መደብሮች በስፋት የሚያሰራጯቸውና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስገኙት ራስ አገዝ መጻሕፍትም አሉ።

ከዘመኑ ሥልጣኔ ጋር የሚሄድ ይህ ሁሉ መረጃ እያለ ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት መመሪያ እንሻለን? ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች፣ ‘እንደዚህ ያለውን ጥንታዊ መጽሐፍ ለመመሪያነት መጠቀም ጊዜው ያለፈበት የኬሚስትሪ መጽሐፍ ወይም የኮምፒውተር አጠቃቀም መመሪያ እንደመጠቀም ነው’ ማለታቸው ትክክል ይሆን? እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ንጽጽር አሳሳች ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በፍጥነት የሚለዋወጡ መሆኑ አይካድም፤ ይሁንና መሠረታዊ የሆነው የሰው ልጆች ፍላጎት ተለውጧል? በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሰዎች የሕይወትን ዓላማ ማወቅ፣ ደስተኛ ሆነውና ተረጋግተው መኖር፣ ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት መምራት እንዲሁም መልካም ወዳጆች ማግኘት ይፈልጋሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንም ስለ እነዚህና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ፣ ፈጣሪ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈው እንደሆነ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች የሚሆኑ መመሪያዎች እንደሚሰጥ እንዲሁም ማንኛውንም ተፈታታኝ ችግር ለመወጣት እንደሚረዳን ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከዚህም በላይ ዘመን የማይሽረው ምክር ይኸውም ፈጽሞ ጊዜ የማያልፍበት መመሪያ እንደያዘ ይገልጻል! መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የአምላክ ቃል ሕያው . . . ነው” በማለት ይናገራል።—ዕብራውያን 4:12

ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩት እነዚህ ሐሳቦች እውነት ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ያለፈበት መጽሐፍ ነው? ወይስ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ ጠቃሚ ምክር የያዘ ሕያው መጽሐፍ? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በዚህ የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ታገኛለህ፤ ይህ መጽሔት በተከታታይ ከሚወጡ ልዩ እትሞች የመጀመሪያው ነው።