በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል ወይስ ስህተት? ውጤታማ የሆነ መመሪያ

ትክክል ወይስ ስህተት? ውጤታማ የሆነ መመሪያ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሚከተሉት አራት አቅጣጫዎች ውጤታማና እምነት የሚጣልበት መመሪያ እንደሚሰጥ ተገንዝበዋል።

1. ትዳር

ሰዎች ስለ ትዳር እንዲሁም የሰመረ ትዳር መመሥረት ስለሚቻልበት መንገድ የተለያየ አመለካከት አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌሶን 5:33

ምን ማለት ነው? የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ ነው፤ በመሆኑም ባለትዳሮች ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃል። (ማርቆስ 10:6-9) ባልም ሆነ ሚስት ከትዳራቸው በሚያገኙት ጥቅም ላይ ሳይሆን ትዳራቸውን ለማጠናከር ሊያበረክቱ በሚችሉት አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት ካደረጉ ደስተኞች መሆን ይችላሉ። ሚስቱን የሚወድ ባል እሷን በሚይዝበትና በሚንከባከብበት መንገድ ፍቅሩን ያሳያል። ባሏን የምታከብር ሚስት ደግሞ በንግግሯና በምግባሯ አክብሮቷን ታሳያለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ውጤታማ ነው፦ በቬትናም የሚኖሩት ኳንግ እና ቲ በትዳራቸው ደስተኛ አልነበሩም። ኳንግ ብዙ ጊዜ ደግነት በጎደለው መንገድ ይይዛት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ቲ ስሜት ምንም ግድ አልነበረኝም፤ ብዙ ጊዜ አዋርዳት ነበር።” ቲ ፍቺ መፈጸም ትፈልግ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን ላምነውም ሆነ ላከብረው እንደምችል አልተሰማኝም።”

ከጊዜ በኋላ ኳንግ እና ቲ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲሁም ኤፌሶን 5:33⁠ን በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ተማሩ። ኳንግ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ጥቅስ ደግነት ማሳየት እንዲሁም ቲ እንደምትወደድ እንዲሰማት ማድረግና እሷን በቁሳዊ፣ በአካላዊና በመንፈሳዊ መንከባከብ ያለውን አስፈላጊነት እንድገነዘብ ረዳኝ። በዚህ መልኩ ስይዛት የእሷን ፍቅርና አክብሮት ማትረፍ ቻልኩ።” ቲ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ኤፌሶን 5:33⁠ን ተግባራዊ በማድረግ ለባለቤቴ አክብሮት ባሳየሁት መጠን የእሱን ፍቅርና እንክብካቤ ስላገኘሁ ውስጣዊ ሰላም ተሰማኝ።”

ትዳርን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ቤተሰብ ስኬታማ እንዲሆን የሚረዱ 12 ወሳኝ ነገሮች” የሚል ርዕስ ያለውን ንቁ! ቁጥር 2 2018⁠ን jw.org ላይ አንብብ።

2. ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ

ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሌሎችን በዘራቸው፣ በብሔራቸው፣ በመልካቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በፆታዊ ሥነ ምግባራቸው የተነሳ ይጠላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17

ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን በዘራቸው፣ በፆታዊ ሥነ ምግባራቸው ወይም በዜግነታቸው የተነሳ መጥላትን አይደግፍም። ከዚህ ይልቅ ዘራቸው፣ ብሔራቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ሰዎች በአክብሮት እንድንይዝ ያበረታታናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34) ሌሎች በሚያምኑበት ነገር ወይም በምግባራቸው ባንስማማም እንኳ እነሱን በደግነትና በአክብሮት መያዝ እንችላለን።—ማቴዎስ 7:12

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ውጤታማ ነው፦ ዳንኤል በዙሪያው ያሉ ሰዎች ከእስያ የመጡ ሰዎችን ለአገሩ ጠንቅ አድርጎ እንዲመለከት ተጽዕኖ አሳድረውበታል። ከእስያ የመጡ ሰዎችን በሙሉ መጥላት የጀመረ ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ በሕዝብ ፊት ይሰድባቸው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ድርጊቴ የአገር ፍቅር መገለጫ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አስተሳሰቤም ሆነ ድርጊቴ ስህተት እንደሆነ ጨርሶ ተሰምቶኝ አያውቅም።”

ውሎ አድሮ ዳንኤል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማረ። እንዲህ ብሏል፦ “አስተሳሰቤን ሙሉ በሙሉ መቀየር ነበረብኝ። ለሰዎች የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ማለትም የመጣነው ከየትም ይሁን ከየት ሁላችንም አንድ ዓይነት እንደሆንን መገንዘብ አስፈልጎኛል።” ዳንኤል በአሁኑ ወቅት ከሰዎች ጋር ሲገናኝ ምን እንደሚሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ ከየት አካባቢ የመጡ ሰዎች እንደሆኑ እንኳ ልብ አልልም። አሁን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እወዳለሁ፤ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የቅርብ ጓደኞች አሉኝ።”

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ጭፍን ጥላቻ ፍቱን መድኃኒት ይገኝለት ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለውን ንቁ! ቁጥር 3 2020⁠ን jw.org ላይ አንብብ።

3. ገንዘብ

ብዙ ሰዎች ደስተኛ ለመሆንና የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ሲሉ ሀብት ያሳድዳሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው።”—መክብብ 7:12

ምን ማለት ነው? ገንዘብ ያስፈልገናል፤ ሆኖም ለደስታም ሆነ ለአስተማማኝ ሕይወት ዋስትና አይሆንም። (ምሳሌ 18:11፤ 23:4, 5) ከዚህ ይልቅ፣ እውነተኛ ደስታና አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የአምላክን ጥበብ በሥራ ላይ በማዋል ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ውጤታማ ነው፦ በኢንዶኔዥያ የሚኖር ካርዶ የተባለ ሰው ሀብት በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች የሚመኙት ነገር ነበረኝ። ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ እንዲሁም የቅንጦት ዕቃዎችን፣ መኪኖችንና ቤቶችን መግዛት ችዬ ነበር።” ይሁንና ሀብቱ አልዘለቀም። እንዲህ ብሏል፦ “በአጭበርባሪዎች ምክንያት ለዓመታት የለፋሁበት ገንዘብ በቅጽበት ጠፋ። ሕይወቴን ያዋልኩት ሀብት ለማሳደድ ነበር። በመጨረሻ ግን ያተረፍኩት የባዶነትና የከንቱነት ስሜት እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ ብቻ ነው።”

ካርዶ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። አሁን ጉልበቱን በሙሉ ሀብት ለማካበት አያውልም። ከዚህ ይልቅ ቀለል ያለ ሕይወት ለመምራት መርጧል። እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛውና ዘላቂው ሀብት መንፈሳዊነት ነው። አሁን ጣፋጭ እንቅልፍ ተኝቼ አድራለሁ፤ እውነተኛ ደስታ አለኝ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ ምን እንደሚል ለማወቅ መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 3 2021 ላይ የወጣውን “ትምህርትና ገንዘብ ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳሉ?” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ አንብብ።

4. የፆታ ሥነ ምግባር

ሰዎች ተቀባይነት ካለው የፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከፆታ ብልግና [ራቁ]። ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።”—1 ተሰሎንቄ 4:3-5

ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ፍላጎታችንን ማርካት ከምንችልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ገደብ ያስቀምጣል። “የፆታ ብልግና” የሚለው አገላለጽ ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት፣ ግብረ ሰዶምን እንዲሁም ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ያካትታል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የፆታ ግንኙነት የአምላክ ስጦታ ነው፤ ሆኖም አምላክ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጸም የሚፈቅደው በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ነው።—ምሳሌ 5:18, 19

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ውጤታማ ነው፦ በአውስትራሊያ የምትኖር ካይሊ የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “የፆታ ግንኙነት መፈጸሜ ትዳር ባልመሠርትም እንኳ እንደምወደድና እንደምፈለግ እንዲሰማኝ ያደርገኛል ብዬ አስቤ ነበር። ግን ውጤቱ ከዚህ ተቃራኒ ሆነ። እንደማልፈለግ ተሰማኝ፤ ልቤ ተሰበረ።”

ከጊዜ በኋላ ካይሊ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሚያስተምረውን ነገር ተማረች፤ እንዲሁም የተማረችውን ነገር በሥራ ላይ ማዋል ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ እነዚህን መሥፈርቶች የሰጠን ከሥቃይና ከጉዳት ሊጠብቀን ብሎ እንደሆነ አሁን ገብቶኛል። አሁን ሕይወቴን የምመራው ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ በመሆኑ እንደምወደድና እንደምፈለግ ይሰማኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋሌ ከብዙ የስሜት ቁስል ጠብቆኛል!”

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን በተመለከተ ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ አንብብ።

ፈጣሪያችን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። እሱ የሰጠንን የሥነ ምግባር መመሪያዎች አክብሮ መኖር ቀላል የማይሆንበት ጊዜ ቢኖርም የምናደርገው ጥረት ይክሰናል። የአምላክን መመሪያዎች መከተል ምንጊዜም ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።