በምዕራፍና በቁጥር መጽሐፍ ቅዱስን የከፋፈለው ማን ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የምትኖር ክርስቲያን እንደሆንክ አድርገህ አስብ። ያለህበት ጉባኤ ከሐዋርያው ጳውሎስ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው እንበል። ደብዳቤው ሲነበብ በምትሰማበት ጊዜ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት’ ማለትም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንደጠቀሰ አስተዋልክ። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) በዚህ ጊዜ ‘ከየት እየጠቀሰ እንዳለ ማየት ብችል ደስ ይለኝ ነበር’ ብለህ ታስባለህ። ይህን ማድረግ ግን ቀላል አልነበረም። ለምን?
ምዕራፍም ሆነ ቁጥር አልነበረውም
በጳውሎስ ዘመን የነበሩት በእጅ የተገለበጡ “ቅዱሳን መጻሕፍት” ምን ይመስሉ እንደነበረ ለማሰብ ሞክር። በዚህ ገጽ ላይ ያለውን ቅጂ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ከሙት ባሕር ጥቅልሎች መካከል ከሚገኘው ከኢሳይያስ መጽሐፍ የተወሰደ ነው። በሥዕሉ ላይ ምን አስተዋልክ? ከዳር እስከ ዳር ግጥም ብሎ የሰፈረ ወጥ ጽሑፍ ነው! ሥርዓተ ነጥብ የሚባል ነገር የለም። እንዲሁም በዛሬው ጊዜ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጽሑፉ በምዕራፍና በቁጥር አልተከፋፈለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መልእክታቸውን በምዕራፍና በቁጥር አልከፋፈሉትም። አምላክ የሰጣቸውን ሙሉውን መልእክት በጽሑፍ ያሰፈሩ ሲሆን አንባቢዎቹም ቁንጽል የሆነ ሐሳብ ሳይሆን ሙሉውን መልእክት እንዲረዱት ይፈልጉ ነበር። አንተስ ብትሆን ከምትወደው ሰው አስፈላጊ ደብዳቤ ሲደርስህ የምትፈልገው ይህን አይደለም? የምታነበው ሙሉውን ደብዳቤ እንጂ አለፍ አለፍ እያልክ የተወሰኑ ክፍሎችን ብቻ አይደለም።
ይሁን እንጂ ምዕራፎችና ቁጥሮች አለመኖራቸው ችግር ይፈጥር ነበር። ጳውሎስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የወሰዳቸው ጥቅሶች የት እንደሚገኙ ሲገልጽ “እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው” ወይም “ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው” ከማለት ባለፈ ሐሳቡ የት እንደሚገኝ ለይቶ መናገር አይችልም ነበር። (ሮም 3:10፤ 9:29) ደግሞም ሁሉንም “ቅዱሳን መጻሕፍት” በሚገባ ካላወቅክ በቀር ጳውሎስ የጠቀሳቸውን ሐሳቦች ማግኘት ከባድ ይሆንብህ ነበር።
ከዚህም በላይ “ቅዱሳን መጻሕፍት” ስንል አምላክ ስለላከው አንድ መልእክት መናገራችን አይደለም። “ቅዱሳን መጻሕፍት” የሚለው አገላለጽ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ 66 የተለያዩ መጻሕፍትን ስብስብ ያመለክት ነበር! ዛሬ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች፣ ጽሑፉ በምዕራፍና በቁጥር በመከፋፈሉ አንድ ሐሳብ የት እንደሚገኝ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ላይ የጠቀሳቸውን ብዙ ጥቅሶች ማግኘት ከባድ አይሆንም።
‘ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን በምዕራፍና በቁጥር የከፋፈለው ማን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
በምዕራፍ የከፋፈለው ማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን በምዕራፎች የከፋፈለው፣ ከጊዜ በኋላ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳሳት የሆነው እንግሊዛዊው ቄስ ስቲቨን ላንግተን ነው። ይህን ያደረገው በ13ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በፓሪስ፣ ፈረንሳይ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አስተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው።
ከላንግተን በፊት ሌሎች ምሁራንም፣ መጽሐፍ ቅዱስን አነስ ባሉ ክፍሎች ወይም ምዕራፎች መከፋፈል የሚቻልባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ሞክረው ነበር፤ ይህን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ከመጽሐፉ ለመጥቀስ እንዲቀላቸው ሳይሆን አይቀርም። አንድን ጥቅስ ለማግኘት አንድን መጽሐፍ ሙሉ (ለምሳሌ፣ 66 ምዕራፎች ያሉትን የኢሳይያስ መጽሐፍ) ከማገላበጥ ይልቅ አንድ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ መፈለግ ምን ያህል ቀላል ይሆንላቸው እንደነበር ማሰብ ትችላለህ።
ይሁንና ምሁራኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለመከፋፈል የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ችግር ፈጥረው ነበር። ምክንያቱም የተለያዩና እርስ በርስ የማይጣጣሙ በርካታ ዘዴዎችን ተጠቅመው ነበር። ከተጠቀሙባቸው ዘዴዎች በአንዱ ላይ፣ የማርቆስ ወንጌል ዛሬ በምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባሉት 16 ምዕራፎች ሳይሆን ወደ 50 በሚጠጉ ምዕራፎች ተከፋፍሎ ነበር። በላንግተን ዘመን ፓሪስ ውስጥ ከብዙ አገሮች የመጡ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን እነሱም ከየአገራቸው መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውን ይዘው መጥተው ነበር። ይሁን እንጂ አስተማሪዎቹም ሆኑ
ተማሪዎቹ፣ የሚጠቅሱት ሐሳብ ከየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደተወሰደ መግባባት አልቻሉም። ለምን? ምክንያቱም በያዟቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ ጽሑፉ በምዕራፍ የተከፋፈለበት መንገድ የተለያየ ነበር።በመሆኑም ላንግተን አዲስ የምዕራፍ አከፋፈል በሥራ ላይ አዋለ። ዘ ቡክ—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ላንግተን የተጠቀመበት ዘዴ “በአንባቢያንም ሆነ በጸሐፍት ዘንድ ተወዳጅነት አትርፏል።” እንዲሁም ይህ አሠራር “በመላው አውሮፓ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት አግኝቷል።” ላንግተን በምዕራፎች ለመከፋፈል የተጠቀመበት ዘዴ በዛሬው ጊዜ ባሉት አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ይሠራበታል።
በቁጥር የከፋፈለው ማን ነው?
ወደ 300 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ይኸውም በ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሮበርት ኤትዬን የተባለ ታዋቂ ፈረንሳዊ አታሚና ምሁር፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር በተያያዘ ነገሮች ይበልጥ ቀላል እንዲሆኑ አደረገ። ዓላማው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በብዙዎች ዘንድ እንዲለመድ ማድረግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ወጥነት ባለው መልኩ በምዕራፎች እና በቁጥሮች መከፋፈሉ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስን በቁጥሮች የመከፋፈሉን ሐሳብ ያፈለቀው ኤትዬን አይደለም። ከዚያ ቀደም ብሎ ይህን ያደረጉ ሌሎች ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል አይሁዳውያን ገልባጮች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት፣ ሙሉውን የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ (በተለምዶ ብሉይ ኪዳን የሚባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል) በቁጥሮች ከፋፍለውት ነበር፤ በምዕራፎች ግን አልከፋፈሉትም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍ ሲከፋፈል አንድ ዓይነት አሠራር እንዳልነበረ ሁሉ በቁጥሮች ሲከፋፈልም ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ ነበር።
ኤትዬን የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን (አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን) በአዲስ መንገድ በቁጥር ከከፋፈለ በኋላ፣ ቀደም ብሎ በቁጥር ከተከፋፈለው የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በአንድነት አጠናቀረው። በ1553 የመጀመሪያውን ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ በፈረንሳይኛ አሳተመ፤ መጽሐፍ ቅዱስን በምዕራፍና በቁጥር የከፋፈለበት ዘዴ በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ከሚጠቀሙበት ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በቁጥሮች መከፋፈሉ፣ ‘ሐሳቡ ወጥ እንዳይሆን ስለሚያደርገው እርስ በርስ የማይገናኙና የማይያያዙ ዓረፍተ ነገሮችን የያዘ ያስመስለዋል’ የሚል ትችት የሰነዘሩ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኤትዬን የተጠቀመበትን ዘዴ ሌሎች አታሚዎችም ብዙም ሳይቆይ በሥራ ላይ አዋሉት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚጠቅም ስጦታ
መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር መከፋፈሉ ቀላል ነገር ይመስል ይሆናል። ሆኖም ይህ ዘዴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ጥቅስ፣ ልክ እንደ ፖስታ ሣጥን ቁጥር የራሱ “አድራሻ” እንዲኖረው ያደርጋል። እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር የተከፋፈለው በአምላክ መንፈስ መሪነት አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜም ሐሳቡ የሚከፈለው አጉል በሆነ ቦታ ላይ ነው። በአንድ ሰነድ ወይም መጽሐፍ ውስጥ ልናስታውሳቸው የምንፈልጋቸውን አገላለጾች ወይም ሐረጎች በቀላሉ ማግኘት እንድንችል እናሰምርባቸዋለን፤ በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር መከፋፈሉ፣ ጥቅሶችን ለመጥቀስ እንዲሁም ለእኛ ልዩ ትርጉም የሚሰጡንን ቁጥሮች በቀላሉ ለማግኘት ወይም ለሌሎች ለማካፈል ያስችለናል።
መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር መከፋፈሉ አመቺ ቢሆንም አምላክ የሰጠውን ሙሉውን መልእክት መረዳትህ አስፈላጊ መሆኑን ምንጊዜም አትዘንጋ። ጥቅሶችን በተናጠል ብቻ ከማንበብ ይልቅ በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ጭምር የማንበብ ልማድ አዳብር። እንዲህ ማድረግ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት” በሙሉ በደንብ እንድታውቅ ይረዳሃል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15.