ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?
ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት የኖሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳዩ ሥዕሎችንና ቅርጾችን ሠርተዋል። ሆኖም ኢየሱስን ፊት ለፊቱ አስቀምጦ ሥዕል የሳለ ወይም ሐውልት የቀረጸ ሰው የለም።
ኢየሱስን ለመሳል የሞከሩት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበረ በትክክል የሚያውቁበት ምንም መንገድ የለም። የሥነ ጥበብ ባለሙያዎቹ የኖሩበት አካባቢ ባሕል፣ ሃይማኖታዊ እምነታቸው እንዲሁም ሥዕሉን እንዲስሉ የጠየቋቸው ሰዎች ፍላጎት ኢየሱስን በሚስሉበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ያም ሆኖ የሠሯቸው ምስሎች ሰዎች ስለ ኢየሱስና ስላስተማራቸው ነገሮች በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ፣ አልፎ ተርፎም የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ።
አንዳንድ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ኢየሱስን የሳሉት ረጅም ፀጉርና የሳሳ ጢም ያለው እንዲሁም ከሲታና ደካማ ወይም የሚተክዝ ሰው አድርገው ነው። በሌሎች ሥዕሎች ላይ ደግሞ ኢየሱስ ከሰው በላይ ኃይል ያለውና በአክሊለ ብርሃን ያጌጠ ወይም የማይቀረብ ዓይነት ሰው ተደርጎ ተስሏል። እንደነዚህ ያሉት ሥዕሎች ኢየሱስን በትክክል ይገልጹታል? ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበር ፍንጭ የሚሰጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመር ነው። እነዚህ ዘገባዎች ስለ ኢየሱስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባም ይገልጹልናል።
“አካል አዘጋጀህልኝ”
እነዚህ ቃላት ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ የተናገራቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። (ዕብራውያን 10:5፤ ማቴዎስ 3:13-17) ታዲያ ለኢየሱስ የተዘጋጀለት አካል ምን ይመስል ነበር? ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ ከ30 ዓመታት ገደማ በፊት መልአኩ ገብርኤል ለማርያም እንዲህ ብሏት ነበር፦ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ . . . [እሱም] የአምላክ ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 1:31, 35) በመሆኑም አዳም በተፈጠረበት ጊዜ ፍጹም ሰው እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስም ፍጹም ሰው ነበር። (ሉቃስ 3:38፤ 1 ቆሮንቶስ 15:45) ስለዚህ ኢየሱስ ጥሩ ቁመና የነበረው ሰው መሆን አለበት፤ እንዲሁም አይሁዳዊ ከሆነችው ከእናቱ ከማርያም ጋር የሚመሳሰል መልክ ሳይኖረው አይቀርም።
አይሁዳውያን ከሮማውያን በተለየ ጢማቸውን የማሳደግ ልማድ ነበራቸው፤ ኢየሱስም አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ጢሙን ያሳድግ ነበር። በአይሁዳውያን ባሕል ጢም ማሳደግ የሥርዓታማነት ምልክት ነበር፤ እንዲሁም ጢማቸው በጣም ረጅምና የተንጨባረረ አልነበረም። የኢየሱስ ጢም በደንብ የተከረከመ ፀጉሩም በአጭሩ የተቆረጠ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ፀጉራቸውን የማይቆረጡት እንደ ሳምሶን ያሉ ናዝራዊ የሆኑ ሰዎች ብቻ ነበሩ።—ዘኁልቁ 6:5፤ መሳፍንት 13:5
ኢየሱስ እስከ 30 ዓመቱ ድረስ በአናጺነት ሙያ ተሠማርቶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያዎች አልነበሩም። (ማርቆስ 6:3) በመሆኑም የኢየሱስ ሰውነት ፈርጣማ የነበረ መሆን አለበት። በአገልግሎቱ መጀመሪያ አካባቢ፣ ያለማንም እገዛ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚነግዱትን ሰዎች “ከበጎቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋር አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ።” (ዮሐንስ 2:14-17) እንዲህ ያለውን እርምጃ ሊወስድ የሚችለው ጠንካራ የሆነ ሰው ብቻ ነው። ኢየሱስ አምላክ ያዘጋጀለትን አካል በመጠቀም እሱ የሰጠውን ተልእኮም ፈጽሟል፤ ይህ ተልእኮ ምን እንደሆነ ሲገልጽ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:43) በመላው ፓለስቲና በእግር እየተጓዙ ይህን መልእክት ማወጅ ለየት ያለ ጥንካሬ ይጠይቃል።
“ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ”
ኢየሱስ ሞቅ ያለ ስሜት ያለውና ተቀራቢ ሰው መሆኑ፣ ያቀረበውን ግብዣ በተለይ ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው ሰዎች’ ይበልጥ ማራኪ አድርጎት መሆን አለበት። (ማቴዎስ 11:28-30) ወዳጃዊ ስሜት ያለውና ደግ መሆኑ፣ ከእሱ መማር እረፍት እንደሚሰጥ የገባው ቃል ኃይል እንዲኖረው አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆቹንም አቀፋቸው” የሚል መሆኑ ትንንሽ ልጆችም እንኳ ወደ ኢየሱስ መቅረብ ይፈልጉ እንደነበር ያሳያል።—ማርቆስ 10:13-16
ኢየሱስ ሊሞት ሲል በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ የነበረ ቢሆንም ሁልጊዜ የሚተክዝ ሰው አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ በቃና በተደረገ አንድ የሠርግ ድግስ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ ሠርጉ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አድርጓል። (ዮሐንስ 2:1-11) በሌሎች ድግሶችም ላይ በመገኘት መቼም ቢሆን የማይረሱ ትምህርቶች ሰጥቷል።—ማቴዎስ 9:9-13፤ ዮሐንስ 12:1-8
ከሁሉም በላይ፣ የኢየሱስ ስብከት ሰሚዎቹ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደሳች ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። (ዮሐንስ 11:25, 26፤ 17:3) ለስብከት የላካቸው ሰባ ደቀ መዛሙርት ከሄዱበት ተመልሰው ያገኙትን ተሞክሮ ሲነግሩት ‘ሐሴት ያደረገ’ ሲሆን “ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 10:20, 21
“እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ”
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ራሳቸው ትኩረት ይስቡና ሥልጣናቸውን ለማሳየት ይሞክሩ ነበር። (ዘኁልቁ 15:38-40፤ ማቴዎስ 23:5-7) በአንጻሩ ግን ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን በሌሎች ላይ ‘ሥልጣናቸውን እንዳያሳዩ’ አዟቸዋል። (ሉቃስ 22:25, 26) እንዲያውም ኢየሱስ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ይወዳሉ፤ በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ” በማለት አስጠንቅቋል።—ማርቆስ 12:38
ከእነዚህ ሰዎች በተለየ መልኩ፣ ኢየሱስ ከሰዎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ እሱን ከሌሎች መለየት የሚቻልበት ለየት ያለ ነገር አልነበረውም፤ እንዲያውም ሰዎች እሱ መሆኑን እንኳ ያላወቁባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዮሐንስ 7:10, 11) ኢየሱስ ከ11ዱ ታማኝ ሐዋርያቱ እንኳ የተለየ አካላዊ ገጽታ አልነበረውም። ከሃዲው ይሁዳ ኢየሱስን ሊያስሩ የመጡት ሰዎች ኢየሱስ የትኛው እንደሆነ መለየት እንዲችሉ “የምስመው ሰው እሱ ነው” በማለት “አስቀድሞ ምልክት” መስጠት ያስፈለገውም ለዚህ ነው።—ማርቆስ 14:44, 45
ስለዚህ ስለ ኢየሱስ መልክ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ማወቅ ባይቻልም፣ የኢየሱስ መልክ በብዙ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የሚታየውን እንደማይመስል በግልጽ መመልከት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር የሚለው ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለእሱ ምን አመለካከት አለን የሚለው ነው።
“ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም”
ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከተናገረ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሞቶ ተቀበረ። (ዮሐንስ 14:19) ሕይወቱን “በብዙ ሰዎች ምትክ” ቤዛ አድርጎ ሰጠ። (ማቴዎስ 20:28) ከዚያም አምላክ በሦስተኛው ቀን ኢየሱስ “መንፈስ ሆኖ” እንዲነሳና ለአንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ “እንዲገለጥ አደረገ።” (1 ጴጥሮስ 3:18፤ የሐዋርያት ሥራ 10:40) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ምን ዓይነት መልክ ነበረው? ከመሞቱ በፊት ከነበረው የተለየ መልክ እንደነበረው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም የቅርብ ወዳጆቹ እንኳ ወዲያውኑ ለይተው አላወቁትም። ለምሳሌ መግደላዊቷ ማርያም አትክልተኛ መስሏት ነበር፤ ወደ ኤማሁስ ይሄዱ የነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት ደግሞ እንግዳ ሰው መስሏቸው ነበር።—ሉቃስ 24:13-18፤ ዮሐንስ 20:1, 14, 15
በዛሬው ጊዜ ስለ ኢየሱስ ስናስብ ወደ አእምሯችን ሊመጣ የሚገባው ምን ዓይነት ምስል ነው? ኢየሱስ ከሞተ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ፣ የተወደደው ሐዋርያ ዮሐንስ ኢየሱስን በራእይ አይቶት ነበር። ዮሐንስ በራእይ ያየው፣ በመስቀል ላይ ሆኖ ሊሞት የሚያጣጥር ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዮሐንስ የተመለከተው በቅርቡ አጋንንትንና መጥፎ ሰዎችን ጨምሮ የአምላክን ጠላቶች በሙሉ የሚደመስሰውና ለሰው ዘር ዘላለማዊ በረከቶችን የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ገዢ የሆነውን “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ነው።—ራእይ 19:16፤ 21:3, 4