በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርማትያሱ ዮሴፍ ከእውነት ጎን ቆመ

የአርማትያሱ ዮሴፍ ከእውነት ጎን ቆመ

የአርማትያሱ ዮሴፍ በሮማዊው ገዥ ፊት ለመቅረብ እንዴት ድፍረት እንዳገኘ ለራሱም እንግዳ ሆኖበታል። ጳንጥዮስ ጲላጦስ በግትርነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ክብር ባለው መንገድ እንዲቀበር ከተፈለገ አንድ ሰው የግድ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው መጠየቅ ነበረበት። ዮሴፍ፣ ጲላጦስን ፊት ለፊት ቀርቦ ማናገር በጣም ከባድ እንደሚሆን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፤ በኋላ ላይ እንደታየው ግን ጲላጦስን ማናገር ያን ያህል ከባድ አልነበረም። ጲላጦስ የኢየሱስን መሞት የመቶ አለቃውን ጠይቆ ካረጋገጠ በኋላ አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት። በዚህ ጊዜ በኢየሱስ ሞት ሐዘን ክፉኛ የተደቆሰው ዮሴፍ እየተጣደፈ ኢየሱስ ወደተገደለበት ቦታ ተመልሶ ሄደ። —ማር. 15:42-45

  • ለመሆኑ የአርማትያሱ ዮሴፍ ማን ነው?

  • ከኢየሱስ ጋር ምን ግንኙነት ነበረው?

  • ደግሞስ የእሱን ታሪክ ማወቅህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል

በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈው የማርቆስ ወንጌል ዮሴፍን “የተከበረ የሸንጎ አባል” በማለት ይጠራዋል። ሸንጎ የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ የአስተዳደር አካል የነበረውን ሳንሄድሪንን እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማር. 15:1, 43) በመሆኑም ዮሴፍ ከሕዝቡ መሪዎች መካከል አንዱ ነበር ማለት ነው፤ ሮማዊውን ገዥ ፊት ለፊት ቀርቦ ማነጋገር የቻለው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ አንጻር ዮሴፍ ሀብታም የነበረ መሆኑም የሚያስገርም አይደለም።—ማቴ. 27:57

ክርስቲያን መሆንህን ለሌሎች በይፋ የመናገር ድፍረት አለህ?

የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በቡድን ደረጃ ለኢየሱስ ጥላቻ ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማስገደል ሴራ ጠንስሰው ነበር። በአንጻሩ ግን ዮሴፍ “ጥሩና ጻድቅ ሰው” ተብሎ ተጠርቷል። (ሉቃስ 23:50) ዮሴፍ ከአብዛኞቹ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በተለየ ሐቀኛና ጥሩ ሥነ ምግባር የነበረው ሰው ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ትእዛዛት ለመጠበቅ የተቻለውን ያህል ጥረት ያደርግ ነበር። በተጨማሪም ይህ ሰው “የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ [እንደነበር]” ተገልጿል፤ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነውም በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። (ማር. 15:43፤ ማቴ. 27:57) የኢየሱስን መልእክት እንዲቀበል ያነሳሳው ለእውነትና ለፍትሕ ያለው ልባዊ ፍላጎት ሊሆን ይችላል።

ስውር ደቀ መዝሙር

ዮሐንስ 19:38 ስለ ዮሴፍ ሲናገር “የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን ይፈራ ስለነበር ይህን ለማንም አልተናገረም” ይላል። ለመሆኑ ዮሴፍን ያስፈራው ምን ሊሆን ይችላል? ዮሴፍ አይሁዳውያን ለኢየሱስ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸውና በእሱ እንደሚያምን የሚናገርን ማንኛውንም ሰው ከምኩራብ ለማባረር ቆርጠው እንደተነሱ ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 7:45-49፤ 9:22) አንድ ሰው ከምኩራብ መባረሩ ደግሞ በአይሁዳውያን ወገኖቹ እንዲናቅ፣ እንዲወገዝና እንዲገለል ያደርገዋል። በመሆኑም ዮሴፍ በኢየሱስ እንደሚያምን በይፋ መናገር አስፈርቶት ነበር። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ ሥልጣኑንና ክብሩን ሊያሳጣው ይችል ነበር።

እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ የገጠመው ዮሴፍ ብቻ አልነበረም። ዮሐንስ 12:42 እንዲህ ይላል፦ “ከገዢዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች [በኢየሱስ] አመኑ፤ ይሁንና ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር።” ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠመው ሌላ ግለሰብ ደግሞ ኒቆዲሞስ ነበር፤ እሱም እንደ አርማትያሱ ዮሴፍ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል ነው።—ዮሐ. 3:1-10፤ 7:50-52

ዮሴፍ ግን ደቀ መዝሙር ነበር፤ ይሁን እንጂ ደቀ መዝሙር መሆኑን በይፋ ለመናገር ድፍረት አላገኘም። ይህ ደግሞ ከባድ ችግር ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “በሰዎች ፊት ለሚመሠክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሠክርለታለሁ። በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” ብሎ ተናግሯል። (ማቴ. 10:32, 33) ዮሴፍ ኢየሱስን በቀጥታ ባይክደውም በእሱ እንደሚያምን በይፋ ለመመሥከር ድፍረት አልነበረውም። አንተስ ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ድፍረት አለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ አንድ ጥሩ ነገር እንዳደረገ ይኸውም የሳንሄድሪን ሸንጎ በኢየሱስ ላይ የጠነሰሰውን ሴራ እንዳልደገፈ ይናገራል። (ሉቃስ 23:51) ምናልባትም አንዳንዶች እንደሚሉት ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ዮሴፍ በቦታው አልነበረ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ዮሴፍ በተፈጸመው አሰቃቂ የፍትሕ መዛባት በጣም አዝኖ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ይህን ኢፍትሐዊ ድርጊት ለማስቆም ማድረግ የሚችለው ምንም ነገር አልነበረም!

ፍርሃቱን አሸነፈ

ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ዮሴፍ ፍርሃቱን አሸንፎና ከኢየሱስ ተከታዮች ጎን ለመቆም ወስኖ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ማርቆስ 15:43 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ይህን በግልጽ ያሳያል፤ ጥቅሱ “ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ” ይላል።

ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ዮሴፍ በስፍራው የነበረ ይመስላል። ደግሞም የኢየሱስን መሞት ከጲላጦስ ቀድሞ ያወቀው እሱ ነበር። ምክንያቱም ዮሴፍ አስከሬኑን ለመውሰድ ሲጠይቅ ጲላጦስ “ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ ለማወቅ” ማጣራት አስፈልጎት ነበር። (ማር. 15:44) ዮሴፍ፣ ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ተሠቃይቶ ሲሞት ተመልክቶ ከሆነ ይህ አሰቃቂ ሁኔታ የራሱን ሕሊና እንዲመረምርና በመጨረሻም ከእውነት ጎን ለመቆም እንዲወስን አነሳስቶት ይሆን? ሊሆን ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ ዮሴፍ በዚያን ወቅት እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስቷል። ከዚህ በኋላ ስውር ደቀ መዝሙር ሆኖ አይቀጥልም።

ዮሴፍ ኢየሱስን ቀበረው

የአይሁዳውያን ሕግ ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንዲቀበሩ ያዛል። (ዘዳ. 21:22, 23) ሮማውያን ግን በሞት የተቀጡ ወንጀለኞች አስከሬን፣ እዚያው እንጨቱ ላይ እንዲተውና እንዲበሰብስ አሊያም ከዚያ ተወስዶ በጋራ መቃብር ውስጥ እንዲጣል ያደርጉ ነበር። ዮሴፍ ይህ በኢየሱስ ላይ እንዲደርስ አልፈለገም። ዮሴፍ፣ ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ከዓለት አስፈልፍሎ ያሠራው መቃብር ነበረው። ይህ መቃብር ከዚህ በፊት ማንም ተቀብሮበት የማያውቅ መሆኑ ዮሴፍ ከአርማትያስ * ወደ ኢየሩሳሌም የተዛወረው በቅርቡ እንደነበርና ይህን ቦታ የቤተሰቡ መቃብር አድርጎ ሊጠቀምበት እንዳዘጋጀው ይጠቁማል። (ሉቃስ 23:53፤ ዮሐ. 19:41) ዮሴፍ ለራሱ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ ኢየሱስ እንዲቀበር ማድረጉ ታላቅ የደግነት መግለጫ ከመሆኑም ሌላ መሲሑ “ከሀብታሞች ጋር” እንደሚቀበር የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ኢሳ. 53:5, 8, 9

ከይሖዋ ጋር ከመሠረትከው ዝምድና አስበልጠህ የምታየው ነገር ይኖራል?

አራቱም የወንጌል ዘገባዎች የኢየሱስ አስከሬን ከእንጨቱ ላይ ከወረደ በኋላ ዮሴፍ በጥሩ በፍታ እንደገነዘውና በራሱ መቃብር ውስጥ እንዳኖረው ይገልጻሉ። (ማቴ. 27:59-61፤ ማር. 15:46, 47፤ ሉቃስ 23:53, 55፤ ዮሐ. 19:38-40) በዚህ ወቅት ዮሴፍን እንደረዳው በቀጥታ የተገለጸው አስከሬኑን ለመቀባት የሚውሉ ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችን ያመጣው ኒቆዲሞስ ብቻ ነው። ሆኖም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከነበራቸው ሥልጣንና ክብር አንጻር እነሱ ራሳቸው አስከሬኑን ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሰውታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ከዚህ ይልቅ አስከሬኑን የተሸከሙትና የቀበሩት አገልጋዮቻቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ያም ቢሆን ሁለቱ ሰዎች ያከናወኑት ሥራ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። አስከሬን የነካ ማንኛውም ሰው፣ የነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ለሰባት ቀናት የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ይጠበቅበታል። (ዘኁ. 19:11፤ ሐጌ 2:13) በዚህ መንገድ የረከሰ ሰው ደግሞ የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ሳምንት ከሰው እንዲገለል የሚደረግ ከመሆኑም ሌላ በዓሉን ማክበርም ሆነ በበዓሉ ሥነ ሥርዓት ተካፋይ መሆን አይችልም። (ዘኁ. 9:6) በተጨማሪም ዮሴፍ የወሰደው እርምጃ በሥራ ባልደረቦቹ ዘንድ መሳለቂያ ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም በዚህ ወቅት ዮሴፍ፣ ኢየሱስ ክብር ባለው መንገድ እንዲቀበር ማድረጉም ሆነ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን በይፋ ማሳወቁ የሚያስከትልበትን መዘዝ ለመቀበል ዝግጁ ሆኖ ነበር።

የዮሴፍ ታሪክ መጨረሻ

ስለ ኢየሱስ አቀባበር ከሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች ውጭ ስለ አርማትያሱ ዮሴፍ የሚናገር ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፤ ይህ ደግሞ ‘የዮሴፍ መጨረሻ ምን ሆነ?’ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል። የዚህን ጥያቄ መልስ በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች አንጻር ዮሴፍ ክርስቲያን መሆኑን በይፋ ተናግሮ መሆን አለበት ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ደግሞም ፈተና በገጠመውና አስጊ ሁኔታ ላይ በወደቀበት በዚያ ወቅት እምነቱና ድፍረቱ እንዳልቀነሰ ከዚህ ይልቅ እየጨመረ እንደሄደ ተመልክተናል። ይህ ደግሞ ዮሴፍ ከዚያ በኋላም ጠንካራ ሆኖ ቀጥሏል ብሎ ለመገመት የሚያስችል ፍንጭ ይሰጠናል።

የዮሴፍ ታሪክ ሁላችንም ልናስብበት የሚገባ አንድ ጥያቄ ያስነሳል፦ ሥልጣንን፣ ሥራን፣ ቁሳዊ ሀብትን፣ ቤተሰብን ሌላው ቀርቶ ነፃነታችንን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው ዝምድና አስበልጠን እንመለከታለን?

^ አን.18 አርማትያስ በዘመናችን ሬንቲስ (ራንቲስ) ተብላ ከምትጠራው ከራማ ጋር አንድ ሳትሆን አትቀርም። ራማ የነቢዩ ሳሙኤል የትውልድ ከተማ ስትሆን ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ምዕራብ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።—1 ሳሙ. 1:19, 20