በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመምረጥ ነፃነታችሁን ታደንቃላችሁ?

የመምረጥ ነፃነታችሁን ታደንቃላችሁ?

“የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ።”—2 ቆሮ. 3:17

መዝሙሮች፦ 40, 54

1, 2. (ሀ) የመምረጥ ነፃነትን በተመለከተ ሰዎች ምን የተለያየ አመለካከት አላቸው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መምረጥ ነፃነት ምን ይላል? የትኞቹን ጥያቄዎችስ እንመረምራለን?

አንዲት ሴት የግል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ባጋጠማት ወቅት ለጓደኛዋ እንዲህ ብላዋለች፦ “ራሴ አስቤ እንድወስን ከምትጠብቅብኝ ይልቅ ‘እንዲህ አድርጊ’ ብትለኝ ይቀለኛል።” ይህች ሴት ፈጣሪዋ የሰጣትን ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነቷን ከመጠቀም ይልቅ፣ ማድረግ ያለባትን ሌላ ሰው እንዲነግራት ፈልጋለች። አንተስ የራስህን ውሳኔ ታደርጋለህ ወይስ ሌሎች እንዲወስኑልህ ትፈልጋለህ? የመምረጥ ነፃነትን የምትመለከተው እንዴት ነው?

2 ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ለዘመናት ሲወዛገቡ ቆይተዋል። አንዳንዶች፣ አምላክ የምናደርገውን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስለወሰነው የመምረጥ ነፃነት የሚባል ነገር እንደሌለን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘የመምረጥ ነፃነት አለን ሊባል የሚችለው ነፃነታችን ምንም ገደብ የሌለው ከሆነ ብቻ ነው’ ይላሉ። ስለዚህ ጉዳይ ትክክለኛ ግንዛቤ ልናገኝ የምንችለው የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሲፈጥረን የመምረጥ ነፃነት ይኸውም የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ችሎታና ነፃነት እንደሰጠን ይናገራል። (ኢያሱ 24:15ን አንብብ።) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ ውሳኔ የማድረግ ነፃነታችንን ልንጠቀምበት የሚገባው እንዴት ነው? የመምረጥ ነፃነታችን ገደብ አለው? የመምረጥ ነፃነታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የሚያሳየው እንዴት ነው? የሌሎችን ውሳኔ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ከይሖዋና ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

3. ይሖዋ የመምረጥ ነፃነቱን የተጠቀመበት መንገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

3 ገደብ የለሽ ነፃነት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ይሁንና ይህን ነፃነቱን የተጠቀመበት መንገድ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤልን ብሔር ለስሙ የሚሆን ‘ልዩ ንብረት’ አድርጎ መርጦታል። (ዘዳ. 7:6-8) ይህን ምርጫ ያደረገው እንዲሁ ደስ ስላለው አይደለም። ይሖዋ ይህን ውሳኔ ያደረገው ከብዙ ዘመናት በፊት ለወዳጁ ለአብርሃም የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነው። (ዘፍ. 22:15-18) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ምንጊዜም ነፃነቱን የሚጠቀመው ከፍቅሩና ከፍትሑ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። በተደጋጋሚ ከእውነተኛው አምልኮ ዘወር ይሉ ለነበሩት እስራኤላውያን እርማት የሰጠበት መንገድ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። እስራኤላውያን ከልባቸው ንስሐ ገብተው ወደ እሱ እስከተመለሱ ድረስ ፍቅሩንና ምሕረቱን ሊያሳያቸው ፈቃደኛ ነበር፤ “ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ። በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ” ብሏል። (ሆሴዕ 14:4) ይሖዋ፣ የመምረጥ ነፃነቱን ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ተጠቅሞበታል፤ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል!

4, 5. (ሀ) የመምረጥ ነፃነት መጀመሪያ የተሰጠው ለማን ነው? ይህን ነፃነቱን የተጠቀመበትስ እንዴት ነው? (ለ) ሁላችንንም ሊያሳስበን የሚገባው የትኛው ጥያቄ ነው?

4 ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ሲጀምር የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጥረታቱ በፍቅር ተነሳስቶ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ስጦታ መጀመሪያ የተሰጠው “የማይታየው አምላክ አምሳል” ለሆነው ለይሖዋ የበኩር ልጅ ነው። (ቆላ. 1:15) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም እንኳ ምንጊዜም ለአባቱ ታማኝ ለመሆን እንዲሁም ሰይጣን ባስነሳው ዓመፅ ላለመተባበር መርጧል። ወደ ምድር ከመጣ በኋላም ቢሆን የመምረጥ ነፃነቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል፤ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት እሱን ለመፈተን ሲል ያቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም። (ማቴ. 4:10) ኢየሱስ፣ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ ያቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እንዳልተቀየረ የሚያረጋግጥ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” (ሉቃስ 22:42) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል፣ የመምረጥ ነፃነታችንን ለይሖዋ ክብር ለማምጣትና የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም እንጠቀምበት። ይሁንና እንዲህ ማድረግ ይቻላል?

5 አዎ፣ የክርስቶስን ምሳሌ መከተል እንችላለን፤ ምክንያቱም ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የተሠራነው በአምላክ መልክና አምሳል ነው። (ዘፍ. 1:26) ይህ ሲባል ግን እንደ ይሖዋ ገደብ የለሽ ነፃነት አለን ማለት አይደለም። የአምላክ ቃል፣ ነፃነታችን ገደብ እንዳለው እንዲሁም ይሖዋ ይህን ምክንያታዊ ገደብ አክብረን እንድንኖር እንደሚጠብቅብን ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ ሚስቶች ለባሎቻቸው፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው መገዛት አለባቸው። (ኤፌ. 5:22፤ 6:1) ታዲያ እንዲህ ያሉ ገደቦች ያሉብን መሆኑ የመምረጥ ነፃነታችንን በምንጠቀምበት መንገድ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ የዘላለም ሕይወት ማግኘት አለማግኘታችንን የሚወስን ሊሆን ይችላል።

የመምረጥ ነፃነታችንን የምንጠቀምበት መንገድ

6. ነፃነታችን ገደብ ያለው መሆኑ ተገቢ የሆነበትን ምክንያት በምሳሌ አስረዳ።

6 የመምረጥ ነፃነታችን ገደብ ያለው ከሆነ እውነተኛ ነፃነት አለን ሊባል ይችላል? አዎ፣ ሊባል ይችላል! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች ባላቸው ነፃነት ላይ ገደብ መደረጉ እነሱን ከአደጋ ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ርቆ ወደሚገኝ አንድ ከተማ መኪና እየነዳህ መሄድ ፈለግክ እንበል። ሆኖም የምትሄድበት መንገድ ምንም ዓይነት የትራፊክ ሕግ የሌለበት እንዲሁም ሁሉም ሰው በፈለገው ፍጥነትና አቅጣጫ የሚነዳበት ቢሆን ምን ይሰማሃል? መቼም የደህንነት ስሜት እንደማይሰማህ የታወቀ ነው። ሁሉም ሰው እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘውን ጥቅም ማጣጣም እንዲችል ከተፈለገ ገደብ ሊኖር ይገባል። የመምረጥ ነፃነታችን ይሖዋ ባወጣቸው መመሪያዎች መገደቡ ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

7. (ሀ) አዳምን በኤደን ገነት ውስጥ ከነበሩት ሌሎች ፍጥረታት የተለየ እንዲሆን ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ምንድን ነው? (ለ) አዳም የመምረጥ ነፃነቱን የተጠቀመበትን አንድ መንገድ ግለጽ።

7 አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ሲፈጥር በሰማይ እንዳሉት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ ሁሉ ለእሱም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶታል። ይህም አዳምን በደመ ነፍስ ከሚመሩት እንስሳት የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። አዳም የመምረጥ ነፃነቱን እንዴት እንደተጠቀመበት የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት። እንስሳት የተፈጠሩት ከሰው በፊት ነበር። ይሁንና ይሖዋ ለእነዚህ ፍጥረታት ስም አላወጣላቸውም፤ ይህን መብት የሰጠው ለመጀመሪያው ሰብዓዊ ልጁ ለአዳም ነው። አምላክ “ሰውየው እያንዳንዳቸውን ምን ብሎ እንደሚጠራቸው ለማየት ሁሉንም ወደ እሱ አመጣቸው።” አዳም እያንዳንዱን እንስሳ በጥንቃቄ በመመልከት ተስማሚ ስም ካወጣላቸው በኋላ ይሖዋ ጣልቃ በመግባት አዳም ያወጣላቸውን ስም አልቀየረም። ከዚህ ይልቅ “ሰውየው ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር የሰጠው [መጠሪያ] የዚያ ፍጡር ስም ሆነ።”—ዘፍ. 2:19

8. አዳም የመምረጥ ነፃነቱን አላግባብ የተጠቀመበት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?

8 የሚያሳዝነው ግን አዳም ገነትን እንዲያለማና እንዲንከባከብ አምላክ በሰጠው ሥራ አልረካም። አምላክ አዳምንና ሔዋንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም። እንዲሁም . . . ዓሣዎችን፣ . . . የሚበርሩ ፍጥረታትንና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው።” (ዘፍ. 1:28) ይህን ኃላፊነት መወጣት በራሱ ሰፊ ነፃነት የሚሰጥ ነበር። ሆኖም አዳም ይህ በቂ እንደሆነ አልተሰማውም። በመሆኑም እንዳይበላ ከተከለከለው ፍሬ በመብላት አምላክ ያስቀመጠለትን ገደብ አልፎ መሄድ መረጠ። አዳም የመምረጥ ነፃነቱን እንዲህ ባለ ተገቢ ያልሆነ መንገድ መጠቀሙ በዘሮቹ ላይ ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቀ ሥቃይና መከራ አስከትሏል። (ሮም 5:12) አዳም እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረጉ ያስከተለውን ውጤት መገንዘባችን፣ የመምረጥ ነፃነታችንን ይሖዋ ካስቀመጠልን ገደብ ሳናልፍ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊያነሳሳን ይገባል።

9. ይሖዋ ሕዝቡ ለሆኑት እስራኤላውያን ምን ምርጫ አቅርቦላቸው ነበር? ሕዝቡስ ምን ምላሽ ሰጠ?

9 የአዳምና የሔዋን ዘሮች ታዛዥ ሳይሆኑ ከቀሩት ወላጆቻቸው አለፍጽምናንና ሞትን ወርሰዋል። ሆኖም የመምረጥ ነፃነታቸውን አላጡም። አምላክ የእስራኤልን ብሔር የያዘበት መንገድ ይህን ያሳያል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን የእሱ ልዩ ንብረት ለመሆን ወይም ላለመሆን መምረጥ እንደሚችሉ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት ገልጾላቸው ነበር። (ዘፀ. 19:3-6) ታዲያ እስራኤላውያን ምን ምላሽ ሰጡ? በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን” በማለት ለስሙ የተመረጠ ሕዝብ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመቀበል መረጡ። (ዘፀ. 19:8) ከጊዜ በኋላ ግን፣ የመምረጥ ነፃነታቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የገቡትን ቃል አፈረሱ። ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን በመኖርና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በመታዘዝ የመምረጥ ነፃነታችንን ምንጊዜም በአድናቆት እንደምንመለከት እናሳይ።—1 ቆሮ. 10:11

10. ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነታቸውን ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

10 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ፣ የመምረጥ ነፃነታቸውን ይሖዋ ካስቀመጠላቸው ገደብ ሳያልፉ የተጠቀሙ 16 ሰዎች ስም ተጠቅሶ እናገኛለን። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ ምርጫ በማድረጋቸው የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል፤ እንዲሁም አስተማማኝ ተስፋ ሊኖራቸው ችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ ጠንካራ እምነት እንዳለው ያሳየ ከመሆኑም ሌላ አምላክ መርከብ እንዲሠራ የሰጠውን መመሪያ ለመከተል መርጧል፤ ይህም ቤተሰቡ ከጥፋት እንዲድንና የሰው ዘር ሕልውና እንዲቀጥል አስችሏል። (ዕብ. 11:7) አብርሃም እና ሣራ፣ አምላክ ቃል ወደገባላቸው ምድር እንዲሄዱ የተሰጣቸውን መመሪያ በፈቃደኝነት ታዘዋል። ይህን ረጅም ጉዞ ከጀመሩ በኋላም እንኳ፣ የበለጸገች ከተማ ወደሆነችው ወደ ዑር “መመለስ የሚችሉበት አጋጣሚ” ነበራቸው። ሆኖም በእምነት ዓይናቸው “የተስፋውን ቃል ፍጻሜ” በትኩረት ተመልክተዋል፤ እንዲሁም ‘የተሻለውን ስፍራ ለማግኘት ይጣጣሩ’ ነበር። (ዕብ. 11:8, 13, 15, 16) ሙሴ “በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን” በመምረጥ ‘በግብፅ የሚገኘውን ውድ ሀብት’ ለመተው ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብ. 11:24-26) እኛም የመምረጥ ነፃነታችንን በአድናቆት በመመልከት እንዲሁም ይህን ነፃነታችንን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በመጠቀም በጥንት ዘመን የኖሩ እንዲህ ያሉ የእምነት ሰዎች የተዉትን ምሳሌ እንከተል።

11. (ሀ) የመምረጥ ነፃነት ከሚያስገኛቸው በረከቶች አንዱ ምንድን ነው? (ለ) የመምረጥ ነፃነትህን በአግባቡ እንድትጠቀምበት የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

11 ሌላ ሰው እንዲወስንልን ማድረግ ቀላል ሊመስል ቢችልም እንዲህ ማድረግ የመምረጥ ነፃነታችንን መጠቀም ከሚያስገኝልን በረከቶች መካከል አንዱን ያሳጣናል። ይህ በረከት በዘዳግም 30:19, 20 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ ተገልጿል። ቁጥር 19፣ አምላክ ለእስራኤላውያን ምርጫ እንደሰጣቸው ይናገራል። ቁጥር 20 ደግሞ እስራኤላውያን በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ማሳየት የሚችሉበት ግሩም አጋጣሚ ይሖዋ እንደሰጣቸው ይገልጻል። እኛም ይሖዋን ለማምለክ መምረጥ እንችላለን። የመምረጥ ነፃነታችንን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየትና ለእሱ ክብር ለማምጣት ልንጠቀምበት እንችላለን፤ ደግሞም አምላክ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ እንድንጠቀምበት የሚያነሳሳ ከዚህ የተሻለ ምክንያት ሊኖር አይችልም!

የመምረጥ ነፃነታችሁን ያለአግባብ አትጠቀሙበት

12. አምላክ ከሰጠን የመምረጥ ነፃነት ጋር በተያያዘ ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?

12 ለአንድ ጓደኛህ ውድ ስጦታ ሰጠኸው እንበል። ሆኖም ጓደኛህ ስጦታውን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ እንደጣለው ወይም ሌሎችን ለመጉዳት እንደተጠቀመበት ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምታዝን የታወቀ ነው! ይሖዋ ብዙ ሰዎች የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ሲጠቀሙበት አልፎ ተርፎም ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሲያደርጉበት ሲያይ ምን ሊሰማው እንደሚችል እስቲ አስበው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች “የማያመሰግኑ” ሆነዋል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) እኛም ይሖዋ የሰጠንን ይህን ውድ ስጦታ አላግባብ እንዳንጠቀምበት እንዲሁም ለዚህ ስጦታ አድናቆት እንዳናጣ እንጠንቀቅ። ይሁንና የመምረጥ ነፃነታችንን አላግባብ እንዳንጠቀምበት ምን ሊረዳን ይችላል?

13. ክርስቲያናዊ ነፃነታችንን አላግባብ ከመጠቀም እንደምንርቅ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

13 ሁላችንም ከጓደኛ፣ ከአለባበስ፣ ከአጋጌጥ እንዲሁም ከመዝናኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ የግላችንን ውሳኔ የማድረግ ነፃነት አለን። ይሁንና ለራሳችን ምኞት ባሪያ ከሆንን ወይም በዓለም ውስጥ ያለውን ቅጥ ያጣ ፋሽን መከተል ከጀመርን የመምረጥ ነፃነታችንን ‘የክፋት መሸፈኛ’ እያደረግነው ነው ሊባል ይችላል። (1 ጴጥሮስ 2:16ን አንብብ።) ነፃነታችንን ‘የሥጋን ፍላጎት ለማርካት መጠቀም’ አንፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ የምናደርጋቸው ምርጫዎች “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱን መሆን ይኖርባቸዋል።—ገላ. 5:13፤ 1 ቆሮ. 10:31

14. በይሖዋ መታመን፣ ከመምረጥ ነፃነታችን ጋር ምን ግንኙት አለው?

14 የመምረጥ ነፃነታችንን በአግባቡ እንደምንጠቀም የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ በይሖዋ በመታመን እንዲሁም እሱ ለእኛ ጥቅም ሲል ባወጣቸው መሥፈርቶች ለመመራት ፈቃደኛ በመሆን ነው። ‘የሚጠቅመንን ነገር የሚያስተምረንና ልንሄድበት በሚገባን መንገድ የሚመራን’ ይሖዋ ብቻ ነው። (ኢሳ. 48:17) “የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” የሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እውነት መሆኑን በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ኤር. 10:23) እንደ አዳምና ዓመፀኛ እንደነበሩት እስራኤላውያን በራሳችን ማስተዋል መመካት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ‘በሙሉ ልባችን በይሖዋ እንታመን።’—ምሳሌ 3:5

የሌሎችን የመምረጥ ነፃነት አክብሩ

15. በገላትያ 6:5 ላይ ከሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 ሌሎችም የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው አምነን መቀበል አለብን። ለምን? እያንዳንዱ ክርስቲያን የመምረጥ ነፃነት ስለተሰጠው፣ ሁለት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ፍጹም አንድ ዓይነት ውሳኔ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ይህ ደግሞ በምናሳየው ምግባርና በምናቀርበው አምልኮ ላይም እንኳ ሊንጸባረቅ ይችላል። በገላትያ 6:5 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወስ ያስፈልገናል። እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም እንዳለበት ከተገነዘብን ሌሎች የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው አምነን እንቀበላለን።

ሌሎች የእኛን የግል አመለካከት እንዲቀበሉ ሳናስገድድ የራሳችንን ውሳኔ ማድረግ እንችላለን (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

16, 17. (ሀ) የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት የመምረጥ ነፃነታቸውን የተጠቀሙበት መንገድ በጉባኤው ውስጥ ምን ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጎ ነበር? (ለ) ጳውሎስ የተፈጠረውን ችግር የፈታው እንዴት ነው? ይህስ የሌሎችን መብት በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

16 ለሕሊና ከተተዉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ወንድሞቻችን የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው አምነን መቀበል ያለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እስቲ እንመልከት። በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ለጣዖት ከተሠዋ በኋላ በሥጋ ገበያ ላይ የሚቀርብ ሥጋን ከመብላት ጋር በተያያዘ በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። አንዳንዶች ‘ጣዖታት ከንቱ ስለሆኑ ይህን ሥጋ መብላት ምንም ችግር የለውም’ የሚል አመለካከት ነበራቸው። ከዚህ በፊት እነዚህን ጣዖታት ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ግን እንዲህ ያለውን ሥጋ መብላት አምልኮ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። (1 ቆሮ. 8:4, 7) ይህ ጉባኤውን ሊከፋፍል የሚችል አደገኛ ሁኔታ ነበር። ታዲያ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዲይዙ የረዳቸው እንዴት ነው?

17 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለቱም ወገኖች ምግብ ከአምላክ ጋር ባላቸው ዝምድና ረገድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እንዲያስተውሉ ረዳቸው። (1 ቆሮ. 8:8) ቀጥሎም ‘የመምረጥ መብታቸው ደካማ የሆኑትን እንዳያሰናክል መጠንቀቅ’ እንዳለባቸው ነገራቸው። (1 ቆሮ. 8:9) ከዚያም ደካማ ሕሊና ያላቸው ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሥጋ በሚበሉት ክርስቲያኖች ላይ እንዳይፈርዱ መመሪያ ሰጣቸው። (1 ቆሮ. 10:25, 29, 30) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው አምልኮን በሚነካ እንዲህ ያለ ትልቅ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን ሕሊናውን ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። ታዲያ እኛስ ወንድሞቻችን የዚህን ያህል ትልቅ ቦታ በማይሰጣቸው ጉዳዮች ረገድ የራሳቸውን ውሳኔ ሲያደርጉ ውሳኔያቸውን ልናከብርላቸው አይገባም?—1 ቆሮ. 10:32, 33

18. የመምረጥ ነፃነትህን እንደምታደንቅ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

18 ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ይህም እውነተኛ ነፃነት ያስገኝልናል። (2 ቆሮ. 3:17) የመምረጥ ነፃነታችን ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ስለሚያስችለን ለዚህ ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት አለን። ይህን ውድ ስጦታ ለአምላክ ክብር በሚያመጣና ሌሎች ያላቸውን የመምረጥ ነፃነት እንደምናከብር በሚያሳይ መንገድ በመጠቀም ስጦታውን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል።