በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር የሚረዳ መመሪያ

ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር የሚረዳ መመሪያ

ፈጣሪያችን፣ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር የምንችልበትን መንገድ ነግሮናል፤ ይህ ምክር፣ ቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ ወይም ከጓደኞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ይጠቅመናል። እሱ ከሰጠን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች መካከል ብዙዎች ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸውን አንዳንድ ምክሮች እንመልከት።

ይቅር ባይ ሁን

“አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ . . . በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13

ስህተት የማይሠራ የለም። ሌሎች እኛን ሊያስቀይሙን፣ እኛም ሌሎችን ልናስቀይም እንችላለን። ያም ሆነ ይህ፣ ሁላችንም ይቅር ማለት ወይም ይቅር መባል የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። ይቅር እንላለን ሲባል፣ በበደለን ሰው ላይ ያለንን ቅያሜ እንተወዋለን ማለት ነው። “በክፉ ፋንታ ክፉ” አንመልስም፤ እንዲሁም ግለሰቡ ያደረሰብንን በደል አሥር ጊዜ አናነሳበትም። (ሮም 12:17) ሆኖም ስሜታችን በጣም ከተጎዳና ጉዳዩን ከአእምሯችን ማውጣት ከተቸገርንስ? እንዲህ ከሆነ፣ ግለሰቡን ብቻውን በአክብሮት ልናነጋግረው ይገባል። ግባችን ሰላም መፍጠር እንጂ እሱ ጥፋተኛ መሆኑን ማሳመን መሆን የለበትም።—ሮም 12:18

ትሑትና ሰው አክባሪ ሁን

“ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3

ትሑትና ሰው አክባሪ ከሆንን፣ ሰዎች ከእኛ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። በደግነትና በአሳቢነት እንደምንይዛቸው እንዲሁም ሆን ብለን እነሱን የሚያስቀይም ነገር እንደማናደርግ ያውቃሉ። ከሌሎች እንደምንበልጥ የምናስብ ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለን ድርቅ የምንል ከሆነ ከሌሎች ጋር መጋጨታችን አይቀርም። ሰዎች ስለሚርቁን ጓደኛ ማግኘት እንቸገራለን።

አታዳላ

“አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ፈጣሪያችን የሰዎችን ዘር፣ ቋንቋ፣ የኑሮ ደረጃ ወይም የቆዳ ቀለም አይቶ አያዳላም። እሱ “የሰውን ወገኖች በሙሉ” የፈጠረው “ከአንድ ሰው” ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) በሌላ አባባል፣ ሰዎች ሁሉ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ናቸው። ሰዎችን ሁሉ በአክብሮትና በደግነት የምንይዝ ከሆነ ደስተኛ እንዲሆኑ እናደርጋለን፤ እኛ ራሳችን እንደሰታለን፣ ፈጣሪያችንንም እናስደስታለን።

ገር ሁን

“ገርነትን . . . ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12

ገር ከሆንን ሰዎች ከእኛ ጋር መሆን ይቀላቸዋል። እኛን ማናገር፣ ሌላው ቀርቶ ስህተት ስንሠራ ማረም አይከብዳቸውም፤ ምክንያቱም እንዲህ በማድረጋቸው እንደማንቆጣ ያውቃሉ። አንድ ሰው በእኛ ላይ በሚቆጣበት ጊዜ ደግሞ በገርነት ካናገርነው ቁጣው ሊበርድለት ይችላል። ምሳሌ 15:1 “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል” ይላል።

ለጋስና አመስጋኝ ሁን

“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስስታም ናቸው፤ የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ነው። እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ግን ለጋስ በመሆን ነው። (ሉቃስ 6:38) በልግስና የሚሰጡ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምክንያቱም ከቁሳቁስ ይልቅ ሰዎችን ይወዳሉ። ለሰዎች እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስላላቸው እነሱም የሆነ ነገር ሲደረግላቸው አድናቂ ናቸው፤ ላደረገላቸው ሰው ምስጋናቸውን ይገልጻሉ። (ቆላስይስ 3:15) እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ከምን ዓይነት ሰው ጋር መሆን ነው የሚያስደስተኝ? ስስታምና ምስጋና ቢስ ከሆነ ሰው ጋር ነው ወይስ ለጋስና አመስጋኝ ከሆነ ሰው ጋር?’ ይህ ምን ያሳያል? ሌሎች እንዲሆኑ የምትፈልገውን አንተ ራስህ ሆነህ መገኘት አለብህ።—ማቴዎስ 7:12