ደስታ የሚያስገኝ መንገድ
ባለን መርካትና ለጋስ መሆን
ብዙዎች የአንድ ሰው ደስታና ስኬት የሚለካው በሀብቱ ወይም በንብረቱ ብዛት እንደሆነ ይናገራሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ አመለካከት ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለረጅም ሰዓታት አድካሚ የሆነ ሥራ ይሠራሉ። ሆኖም ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ንብረት ዘላቂ ደስታ ያስገኛል? ማስረጃዎቹ ምን ይጠቁማሉ?
ጆርናል ኦቭ ሀፒነስ ስተዲስ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው አንድ ሰው መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚበቃ ገቢ እስካለው ድረስ የገቢው መጠን መጨመሩ ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆን ወይም አስተማማኝ ሕይወት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ያን ያህል አስተዋጽኦ አይኖረውም። እርግጥ ነው፣ ገንዘብ በራሱ አንድ ሰው ደስታውን እንዲያጣ አያደርግም። ሞኒተር ኦን ሳይኮሎጂ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደገለጸው “ደስታ ወደማጣት የሚመራው [ገንዘብ] ለማግኘት የሚደረገው ጥረት” ነው። ይህ ሐሳብ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፈውን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያስታውሰናል፦ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው . . . ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) እዚህ ላይ የተገለጸው ሥቃይ ምን ነገሮችን ሊያካትት ይችላል?
ሀብትን ላለማጣት የሚደረገው ጥረት የሚያስከትለው ጭንቀትና እንቅልፍ ማጣት። “የሚበላው ጥቂትም ሆነ ብዙ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ ባለጸጋ ሰው ያለው ብዙ ሀብት ግን እንቅልፍ ይነሳዋል።”—መክብብ 5:12
የተጠበቀው ደስታ ሳይገኝ መቅረቱ የሚያስከትለው ተስፋ መቁረጥ። አንድ ሰው እንዲህ ላለው ሐዘን የሚዳረግበት አንዱ ምክንያት የገንዘብ ጥማት ፈጽሞ ሊረካ ስለማይችል ነው። “ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም።” (መክብብ 5:10) በተጨማሪም አንድ ሰው ገንዘብ ለማግኘት ያለው ጉጉት፣ ደስታ የሚያስገኙ አስፈላጊ ነገሮችን መሥዋዕት እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል፤ ለምሳሌ ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ ጋር አብሮ እንደመሆን ወይም በመንፈሳዊ ነገሮች እንደመካፈል ያሉ ነገሮችን ችላ ማለት ይጀምር ይሆናል።
ገንዘብ ዋጋውን ማጣቱ ወይም ኢንቨስት የተደረገበት ነገር መክሰሩ የሚያስከትለው ሐዘንና ብስጭት። “ሀብት ለማግኘት አትልፋ። ይህን ትተህ በማስተዋል ተመላለስ። ዓይንህን ስትጥልበት በዚያ አታገኘውም፤ የንስር ዓይነት ክንፎች አውጥቶ . . . ይበርራልና።”—ምሳሌ 23:4, 5
ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች
ባለን መርካት። “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለምና፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ስለዚህ ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ባላቸው የሚረኩ ሰዎች የማማረር ወይም የማጉረምረም ዝንባሌ አይኖራቸውም፤ ይህም በሌሎች እንዳይቀኑ ይረዳቸዋል። ደግሞም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ለማግኘት ስለማይመኙ አላስፈላጊ ከሆነ ጭንቀትና ውጥረት ይድናሉ።
ለጋስ መሆን። “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ለጋስ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ሌሎችን ለመርዳት የሚያውሉት ጊዜና ጉልበት ትንሽ ቢሆንም እንኳ ሰዎችን ማስደሰት በመቻላቸው ይደሰታሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ሰዎች በገንዘብ ሊገዙ የማይችሉ የተትረፈረፉ በረከቶችን ያገኛሉ፤ ለምሳሌ ፍቅርና አክብሮት የሚያተርፉ ከመሆኑም ሌላ መልሰው በልግስና የሚሰጧቸው እውነተኛ ጓደኞች ይኖሯቸዋል!—ሉቃስ 6:38
ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለሰዎች ቅድሚያ መስጠት። “ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይልቅ ፍቅር ባለበት አትክልት መብላት ይሻላል።” (ምሳሌ 15:17) ይህ ጥቅስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ከሌሎች ጋር ያለን ወዳጅነት ከቁሳዊ ሀብት የበለጠ ዋጋ አለው። ደግሞም በኋላ ላይ እንደምንመለከተው እንዲህ ባለው ወዳጅነት ውስጥ የሚንጸባረቀው ፍቅር ለደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ሳቢና የምትባል በደቡብ አሜሪካ የምትኖር አንዲት ሴት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም ተመልክታለች። ሳቢና ባለቤቷ ጥሏት ከሄደ በኋላ ለራሷና ለሁለት ሴት ልጆቿ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት ትታገል ነበር። ሁለት ሥራዎችን የምትሠራ ሲሆን በየቀኑ ከእንቅልፏ የምትነሳው ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ ነበር። ሳቢና ጊዜዋ በጣም የተጣበበ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ወሰነች። ውጤቱስ ምን ሆነ?
የኑሮ ሁኔታዋ እምብዛም አልተለወጠም። ለሕይወት ያላት አመለካከት ግን በእጅጉ ተቀይሯል! ለምሳሌ ያህል፣ መንፈሳዊ ፍላጎቷን ማሟላት በመቻሏ ደስታ አግኝታለች። (ማቴዎስ 5:3) በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቿ መካከል እውነተኛ ወዳጆችን ማፍራት ችላለች። እንዲሁም የተማረችውን ነገር ለሌሎች በማካፈል መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ በገዛ ሕይወቷ ተመልክታለች።
መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ ትክክል መሆኗ በውጤቷ ተረጋግጧል” ይላል። (ማቴዎስ 11:19 የግርጌ ማስታወሻ) ከዚህ አንጻር ባለን መርካት፣ ለጋስ መሆን እንዲሁም ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለሰዎች ቅድሚያ መስጠት የጥበብ አካሄድ እንደሆነ በውጤቱ ተረጋግጧል!