በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕላኔታችን ትተርፍ ይሆን?

ደኖች

ደኖች

ደኖች የምድር ሳንባ እንደሆኑ ይነገራል፤ ደግሞም እንዲህ መባላቸው አያስገርምም። ዛፎች ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ውስጣቸው ያስገባሉ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የካርቦንዳይኦክሳይድ ክምችት ጉዳት ያስከትልብን ነበር። ከዚህም ሌላ፣ የምንተነፍሰው አየር ወሳኝ ክፍል የሆነውን ኦክስጅንን ይለቃሉ። በምድር ላይ ካሉት የየብስ ዕፀዋትና እንስሳት መካከል 80 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የሚኖሩት ደኖች ውስጥ ነው። ደኖች ባይኖሩ ኖሮ በሕይወት መቀጠል አንችልም ነበር።

ደኖች የተደቀነባቸው አደጋ

በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች ይቆረጣሉ፤ አብዛኞቹ የሚቆረጡት ለእርሻ የሚሆን መሬት ለማግኘት ነው። ከ1940ዎቹ መገባደጃ አንስቶ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ካሉት የተፈጥሮ ደኖች መካከል ግማሽ ያህሉ ተጨፍጭፈዋል።

ደኖች ሲጨፈጨፉ በውስጣቸው የሚኖሩት ተክሎችና እንስሳትም ይጠፋሉ።

ፕላኔታችን የተፈጠረችው ለዘላለም እንድትኖር ነው

ተጨፍጭፈው የነበሩ አንዳንድ ደኖች መልሰው የማንሰራራት አስደናቂ ችሎታ አሳይተዋል። የሥነ ምህዳር ተመራማሪዎች ተጨፍጭፈው የነበሩ ደኖች በተፈጥሯዊ መንገድ ተመልሰው ያደጉበትና ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው የተመለሱበት ፍጥነት በጣም አስደንቋቸዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

  • ተመራማሪዎች የእርሻ መሬት ለማግኘት ሲባል ከተመነጠሩ በኋላ በተተዉ መሬቶች ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ 2,200 መሬቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው አፈሩ በአሥር ዓመት ውስጥ ደን ለማብቀል ተስማሚ ወደሆነ ደረጃ ሊመለስ ይችላል።

  • ሳይንስ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚገልጸው እንዲህ ያለው መሬት በ100 ዓመት ገደማ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ዕፀዋትንና ሌሎች የደን ፍጥረታትን የያዘ ጤናማ ደን እንደሚሆን ተመራማሪዎች ይገምታሉ።

  • በብራዚል የሚኖሩ ሳይንቲስቶች በቅርቡ፣ ዝም ተብለው በተተዉ መሬቶችና አዳዲስ ዛፎችን ለመትከል ከፍተኛ ርብርብ በተደረገባቸው መሬቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወዳደር ሞክረው ነበር።

  • ናሽናል ጂኦግራፊክ በዚህ ጥናት ስለተሳተፉት ተመራማሪዎች ሲናገር “ዛፎችን መትከል አስፈላጊ እንዳልሆነ በመገንዘባቸው በጣም ተደስተዋል” ብሏል። ጥናት የተካሄደባቸው መሬቶች ምንም ዓይነት ዛፍ ሳይተከልባቸው በአምስት ዓመት ውስጥ በአገር በቀል ዛፎች ተሞሉ።

እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች

በዓለም ዙሪያ ደኖችን ለመንከባከብና የተመናመኑ ደኖችን መልሶ ለማልማት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህም የተነሳ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደሚገልጸው ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ “የደን ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ50 በመቶ ቀንሷል።”

ሆኖም እነዚህ ጥረቶች ደኖችን ለመታደግ በቂ አይደሉም። ግሎባል ፎረስት ዎች የተባለው ድርጅት ያወጣው አንድ ሪፖርት እንደሚገልጸው “በተፈጥሮ ደኖች ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እምብዛም አልቀነሰም።”

ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ዛፍ የሚቆርጡ ጣውላ አምራቾች ከዚህ ሥራ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያገኛሉ። የተፈጥሮ ደኖች እንዲመናመኑ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት እንዲህ ያለው ስግብግብነት ነው።

የደን ጥበቃ ባለሙያዎች ዕድሜ ጠገብ ዛፎች በብዛት እንዳይቆረጡ በመከላከል እንዲሁም አዳዲስ ዛፎችን በመትከል ደኖችን ይንከባከባሉ

ተስፋ ለማድረግ የሚያበቁ ምክንያቶች—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ይሖዋ a አምላክ ለማየት የሚያስደስተውንና ለምግብነት መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከመሬት አበቀለ።”—ዘፍጥረት 2:9

የደኖች ፈጣሪ የሆነው አምላክ ደኖችን የሠራቸው ሰዎች ለዘላለም እንዲጠቀሙባቸው በሚያስችል መንገድ ራሳቸውን እንዲያድሱ አድርጎ ነው። ደኖችና በውስጣቸው ያለው አስደናቂ ብዝሃ ሕይወት እንዳይጠፉ መጠበቅ ይፈልጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ ፕላኔታችን እና በውስጧ ያለው ሕይወት መትረፍ እንዲችል የሰው ልጆች እያደረሱ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛ ያስቆማል። በገጽ 15 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ፕላኔታችን እንደምትተርፍ ቃል ገብቷል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18