የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ምትሃታዊ ድርጊቶች ምን ጉዳት አላቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ መናፍስታዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ምን ያስተምራል?
ብዙ ሰዎች ምትሃታዊ ወይም መናፍስታዊ ድርጊት የሚባል ነገር እንደሌለ አሊያም የፊልም ደራሲዎች ፈጠራ እንደሆነ ያስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይዟል። የአምላክ ቃል መናፍስታዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘዳግም 18:10-13 እንዲህ ይላል፦ “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።” መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ለምንድን ነው? የጥቅሱ ቀጣይ ሐሳብ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው። . . . በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንከን የለሽ ሆነህ መገኘት አለብህ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት አጥብቆ የሚያወግዘው ለምንድን ነው?
ከበስተጀርባው ያሉት አጋንንት ናቸው
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ምድርን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ወይም መላእክትን እንደፈጠረ ይናገራል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ራእይ 5:11) አምላክ ለሁሉም መላእክት ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ሆኖም አንዳንዶቹ መላእክት የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው በአምላክ ላይ ዓመፁ፤ ከዚያም በሰማይ ላይ የነበራቸውን ቦታ ትተው ወደ ምድር በመምጣት በምድር ላይ ችግር መፍጠር ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ምድር ‘በዓመፅ ተሞላች።’—ዘፍጥረት 6:2-5, 11፤ ይሁዳ 6
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ክፉ መላእክት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደሚያሳስቱ ይናገራል። (ራእይ 12:9) ሌላው ቀርቶ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ያላቸውን ተፈጥሯዊ ጉጉት በመጠቀም ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ።—1 ሳሙኤል 28:5, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1
2 ቆሮንቶስ 11:14) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የክፉ መላእክት ዓላማ ሰዎችን መርዳት ሳይሆን የሰዎችን አእምሮ በማሳወር ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ ማድረግ ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:4
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ መናፍስታዊ ድርጊቶች ሰዎችን የሚረዱ ሊመስሉ ይችላሉ። (ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከክፉ መናፍስት ጋር ንክኪ ባላቸው ድርጊቶች መካፈል ምንም ጉዳት የሌለው መዝናኛ አይደለም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ፍላጎት የነበራቸው በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎችም ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች እውነቱን ሲማሩ ቆራጥ እርምጃ የወሰዱት ለዚህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች ስለወሰዱት እርምጃ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት . . . አቃጠሉ።” እነዚህ ሰዎች ይህን እርምጃ መውሰዳቸው ትልቅ የገንዘብ ኪሳራ ቢያስከትልባቸውም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላሉም።—የሐዋርያት ሥራ 19:19
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ካለው ማንኛውም ድርጊት ወይም መዝናኛ ለመራቅ ወስነዋል። ለምሳሌ ማሪያ * የ12 ዓመት ልጅ በነበረችበት ወቅት፣ ወደፊት ስለሚፈጸሙ አንዳንድ ክስተቶች ወይም አደጋዎች የማወቅ ችሎታ እንዳላት ይሰማት ነበር። አብረዋት ለሚማሩ ልጆች የጥንቆላ ካርዶችን (ታሮት ካርድ) ታነብላቸው የነበረ ሲሆን የምትተነብየው ነገር እንደሚፈጸም ስታይ ደግሞ በዚህ ድርጊት መካፈሉን ይበልጥ እየወደደችው መጣች።
ማሪያ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችላትን ይህን ስጦታ ያገኘችው ከአምላክ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የሚረብሸኝ ነገር ግን ነበር። ካርዶቹን ለሌሎች ሰዎች ብቻ እንጂ ለራሴ ማንበብ አልችልም ነበር። ስለ ራሴ የወደፊት ሕይወት ማወቅ እፈልግ የነበረ ቢሆንም ይህን ማድረግ አልቻልኩም።”
ወደ አምላክ ጸለየች፤ በኋላም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘች ሲሆን እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምሯት ጀመር። ማሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ስትማር፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታዋን ያገኘችው ከአምላክ እንዳልሆነ ተረዳች። እንዲሁም የአምላክ ወዳጅ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎች በሙሉ ማስወገድ እንዳለባቸው ተገነዘበች። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ማሪያ የአስማት ዕቃዎቿንና መጻሕፍቷን በሙሉ አስወገደች። በአሁኑ ጊዜ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረችውን እውነት ለሌሎች በመናገሩ ሥራ ትካፈላለች።
ማሪያ ለነበሯት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘቷ ግራ ስለተጋባችማይክል በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ፣ ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ገጸ ባሕርያት የሚናገሩ ልብ ወለዶችን ማንበብ በጣም ያስደስተው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በገሃዱ ዓለም በማይገኙ ቦታዎች ስለሚኖሩ በእኔ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጀብደኛ ሰዎች ማንበብ ያስደስተኝ ነበር።” ቀስ በቀስ ማይክል ስለ አስማትና ከሰይጣን ጋር ተያያዥነት ስላላቸው የአምልኮ ሥርዓቶች የማንበብ ልማድ ተጠናወተው። እንዲህ በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “የነበረኝ የማወቅ ጉጉት እንዲህ ስላሉ ነገሮች የሚያወሱ መጽሐፎችን ለማንበብና ፊልሞችን ለማየት አነሳሳኝ።”
ሆኖም ማይክል መጽሐፍ ቅዱስን መማሩ የሚያነበውን ነገር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለበት አስገነዘበው። እንዲህ ብሏል፦ “ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ጻፍኩ፤ ከዚያም ሁሉንም አስወገድኳቸው። አንድ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 10:31 ላይ ‘ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ’ በማለት ይናገራል። በመሆኑም ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦ ‘ይህ መጽሐፍ አምላክን የማያስደስት ነገር ይዟል?’ ከሆነ ለአምላክ ክብር ስለማያመጣ መጽሐፉን አላነበውም።”
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መብራት ተደርጎ መገለጹ ተገቢ ነው። የመናፍስታዊ ድርጊትን ትክክለኛ ምንነት የሚያጋልጠው ብቸኛው የብርሃን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (መዝሙር 119:105) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በማድረግ ብቻ አይወሰንም። ከክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ዓለም እንደሚመጣ የሚናገር ግሩም ተስፋም ይሰጣል። ይህም ለሰው ልጆች ትልቅ እፎይታ ያስገኛል። መዝሙር 37:10, 11 እንዲህ ይላል፦ “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም። የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”
^ አን.10 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።