ንድፍ አውጪ አለው?
ንብ የምትፈልገው ቦታ ላይ ለማረፍ የምትጠቀምበት ዘዴ
ንቦች በፈለጉት አቅጣጫ እየበረሩ መጥተው ያለምንም ችግር ማረፍ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ችሎታ ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንዲት ንብ ያለምንም ችግር የፈለገችበት ቦታ ላይ ማረፍ እንድትችል ወደምታርፍበት ቦታ የምትበርበትን ፍጥነት እየቀነሰች ሄዳ ዜሮ ማድረስ አለባት። ይህን ለማድረግ ደግሞ የምትበርበትን ፍጥነትና ከምታርፍበት ቦታ ያላትን ርቀት ማወቅ ይኖርባታል፤ ከዚያም እነዚህን ሁለት ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብታ ፍጥነቷን እየቀነሰች መሄድ ያስፈልጋታል። ነገር ግን ንቦችን ጨምሮ አብዛኞቹ ነፍሳት ዓይኖቻቸው በጣም የተቀራረቡ ስለሆኑና ከርቀት አንጻር እይታቸውን ማስተካከል ስለማይችሉ በዓይኖቻቸው ርቀትን መለካት አይችሉም።
የሰው ልጆች ሁለት ዓይኖቻቸውን አቀናጅተው ስለሚጠቀሙ ከአንድ ነገር ያላቸውን ርቀት ማወቅ ይችላሉ፤ የንቦች እይታ ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። ሆኖም ንቦች ወደ አንድ ነገር እየቀረቡ ሲሄዱ የዚያ ነገር መጠን እየጨመረ እንደሚመጣ ያውቃሉ። ወደ አንድ ነገር ይበልጥ በቀረቡ ቁጥር የዚያ ነገር መጠን የሚጨምርበት ፍጥነትም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። በአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንዲት ንብ፣ የምታርፍበት ነገር መጠኑን የሚጨምርበት ፍጥነት ቋሚ ሆኖ እስኪታያት ድረስ የበረራ ፍጥነቷን እየቀነሰች ትሄዳለች። በመሆኑም የምታርፍበት ቦታ ጋ ስትደርስ ፍጥነቷ እየቀነሰ ሄዶ ዜሮ ይደርሳል፤ ይህም ያለምንም ችግር እንድታርፍ ያስችላታል።
ፕሮሲዲንግስ ኦቭ ዘ ናሽናል አካደሚ ኦቭ ሳይንስስ የተባለው መጽሔት እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “[ንቦች] የሚፈልጉበት ቦታ ላይ ለማረፍ የሚጠቀሙበት ይህ ዘዴ ቀላል ስለሆነ . . . በራሪ ሮቦቶችን የሚቆጣጠሩ ፕሮግራሞችን ለመሥራት ጥቅም ላይ ሊውል ይቻላል።”
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ንቦች የፈለጉበት ቦታ ላይ ያለምንም ችግር ለማረፍ የሚጠቀሙበት ዘዴ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?