በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂዋ አርክቲክ ተርን

አስደናቂዋ አርክቲክ ተርን

አርክቲክ ተርን የተባሉት ወፎች ከአርክቲክ አካባቢ ተነስተው እስከ አንታርክቲካ በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጉዞ 35,200 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት ይበራሉ ተብሎ ይታመን ነበር። በቅርብ በተደረጉ ጥናቶች ግን ወፎቹ ከዚህ የበለጠ ርቀት እንደሚጓዙ ተረጋግጧል።

ሥዕላዊ መግለጫው ላይ እንደሚታየው ተርኖች የሚበርሩት ጠመዝማዛ የሆነ አቅጣጫ ተከትለው ነው

ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት ጂዮሎኬተር የሚባሉ ትናንሽ መሣሪያዎች በበርካታ ወፎች ላይ ታሰሩ። እነዚህ ከእስክሪብቶ ክዳን ያነሰ ክብደት ያላቸው አስደናቂ መሣሪያዎች እንዳመለከቱት አንዳንድ ተርኖች ከአርክቲክ እስከ አንታርክቲካ ደርሶ መልስ በአማካይ 90,000 ኪሎ ሜትር ይበርራሉ፤ ይህም ማንኛውም እንስሳ ከሚያደርገው የፍልሰት ጉዞ ረጅሙ እንደሆነ ይታመናል። እንዲያውም አንዲት ወፍ 96,000 ኪሎ ሜትር ያህል በርራለች። ለመሆኑ የሚጓዙትን ርቀት በተመለከተ ቀደም ሲል በነበረው ግምታዊ አኃዝ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

እነዚህ ወፎች ጉዟቸውን የሚጀምሩት ከየትኛውም ቦታ ቢሆን የሚበርሩት ጠመዝማዛ የሆነ አቅጣጫ ተከትለው ነው። በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው አብዛኛውን ጊዜ አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው የሚበርሩት የኤስ ቅርጽ ተከትለው ነው። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ወፎቹ የሚበርሩት የነፋስን አቅጣጫ ተከትለው ስለሆነ ነው።

ተርኖች 30 ዓመት ገደማ በሚሆነው የሕይወት ዘመናቸው ከ2.4 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛሉ። ይህ ደግሞ ወደ ጨረቃ ሦስት ወይም አራት ጊዜ የደርሶ መልስ ጉዞ የማድረግ ያህል ነው! አንድ ተመራማሪ “ከ100 ግራም የማይበልጥ ክብደት ያላት ወፍ ይህን ያህል ርቀት መጓዝ መቻሏ በጣም አስደናቂ ነው” ብሏል። ከዚህም በላይ አርክቲክ ተርኖች በሁለቱም ዋልታዎች ላይ የሚያሳልፉት የበጋ ወቅት በመሆኑ ላይፍ ኦን ኧርዝ፣ ኤ ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ “ከማንኛውም ፍጥረት የበለጠ የቀን ብርሃን ያያሉ” ሲል ገልጿል።