የመፍትሔ እርምጃ
የሥነ ምግባር ትምህርት
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ወንዶች ልጆች፣ ትምህርት ቤታቸው የሽርሽር ጉዞ ባዘጋጀበት ወቅት በአንድ ሌላ ተማሪ ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው ተከሰው ነበር። ሁሉም ካናዳ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ስመ ጥር የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ። ይህ ሁኔታ ከተከሰተ በኋላ ሌነርድ ስተርን፣ ኦታዋ ሲቲዝን በተሰኘ ጋዜጣ ላይ “ወጣቶች ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ያላቸውና የተማሩ መሆናቸው እንዲሁም የተደላደለ ኑሮ ያላቸው መሆኑ መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም አያግዳቸውም” በማለት ጽፏል።
ስተርን አክሎም እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የወላጆች ዋነኛ ግብ ልጃቸውን በሥነ ምግባር አንጸው ማሳደግ ነው ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ብዙ ወላጆች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ልጃቸው ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቆ ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ጥሩ ሥራ መያዝ መቻሉ ሳይሆን አይቀርም።”
ልጆችን ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ከሁሉ የተሻለ የሚባለው የቀለም ትምህርትም እንኳ አንድን ሰው መጥፎ ምኞቶችን ወይም ዝንባሌዎችን እንዲያሸንፍ ሊረዳው አይችልም። ታዲያ እነዚህን መጥፎ ምኞቶች ወይም ዝንባሌዎች ለማሸነፍ የሚረዳ የሥነ ምግባር ትምህርት ከየት ማግኘት እንችላለን?
ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ የሚሰጥ ትምህርት
መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መስታወት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ራሳችንን ስንመለከት አቅማችን ውስን እንደሆነና ድክመቶች እንዳሉብን በግልጽ ማስተዋል እንችላለን። (ያዕቆብ 1:23-25) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም የበለጠ ጥቅም ያስገኝልናል። አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን እንድናደርግ ይኸውም እውነተኛ ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን የሚያደርጉ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ጥሩነት፣ ደግነት፣ ትዕግሥት፣ ራስን መግዛት እንዲሁም ፍቅር ይገኙበታል። እንዲያውም ፍቅር “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” ተብሎ ተጠርቷል። (ቆላስይስ 3:14) ፍቅር በጣም ልዩ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ባሕርይ አስመልክቶ ምን እንደሚል ልብ በል።
-
“ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ [በክፋት] አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ . . . ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4-8
-
“ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።”—ሮም 13:10
-
“ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።”—1 ጴጥሮስ 4:8
ከሚወዱህ ሰዎች ጋር ስትሆን ምን ይሰማሃል? ስጋት እንደማያድርብህ የታወቀ ነው። አዎ፣ የሚወዱህ ሰዎች ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚመኙልህና ሆን ብለው እንደማይጎዱህ ታውቃለህ።
በተጨማሪም ፍቅር፣ ሰዎችን ለሌሎች ጥቅም ሲሉ መሥዋዕት እንዲከፍሉ አልፎ ተርፎም የአኗኗር ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጆርጅ * የተባሉ አንድ ሰው ሴት ልጃቸው ስትወልድ ከልጅ ልጃቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ችግር ነበረባቸው። ጆርጅ ኃይለኛ አጫሽ ስለነበሩ የልጃቸው ባል፣ ሕፃኑ ባለበት ክፍል ውስጥ እንዲያጨሱ አይፈልግም ነበር። ታዲያ ጆርጅ ምን አደረጉ? ለ50 ዓመታት ያጨሱ ቢሆንም ለልጅ ልጃቸው ሲሉ ማጨሳቸውን ተዉ። በእርግጥም ፍቅር ታላቅ ኃይል አለው!
መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ጥሩነት፣ ደግነት እና ፍቅር ያሉትን መልካም ባሕርያት እንድናፈራ ይረዳናል
ፍቅር ሊዳብር የሚችል ባሕርይ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ፍቅር እንዲያሳዩ በማስተማር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን ይመግባሉ፣ ይንከባከባሉ እንዲሁም ጉዳት ሲደርስባቸው ወይም ሲታመሙ ይደርሱላቸዋል። ጥሩ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ይጫወታሉ እንዲሁም ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። በተጨማሪም ልጆቻቸውን የሚገሥጹ ሲሆን ይህም ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ጥሩ መመሪያዎችን ማስተማርን ያካትታል። ከዚህም ሌላ ለልጆቻቸው ጥሩ አርዓያ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።
የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ወላጆች ኃላፊነታቸውን አይወጡም። ታዲያ ይህ ሲባል ልጆቻቸው ጥሩ ሰዎች መሆን አይችሉም ማለት ነው? በጭራሽ! ሰላም በጠፋባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉትን ጨምሮ አንዳንድ ትላልቅ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አስገራሚ ለውጥ አድርገው አሳቢና እምነት የሚጣልባቸው ዜጎች ሆነዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ፈጽሞ ሊለወጡ የማይችሉ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር!
^ ስማቸው ተቀይሯል።