በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

ሐዘን የሚፈጥረው ሥቃይ

ሐዘን የሚፈጥረው ሥቃይ

“ባለቤቴ ሶፊያ * ለረጅም ጊዜ ታማ ከቆየች በኋላ በሞት አንቀላፋች፤ ከእሷ ጋር ከ39 የሚበልጡ ዓመታት በትዳር አሳልፈናል። ወዳጆቼ ከጎኔ ያልተለዩ ሲሆን እኔም ራሴን በሥራ ለማስጠመድ እጥር ነበር። ሆኖም እሷ ከሞተች በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል፣ ግማሽ አካሌ በድን እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ስሜቴ እየዋዠቀ ያስቸግረኝ ነበር። ሶፊያ ከሞተች ሦስት ዓመት ሊሞላት ነው፤ ያም ቢሆን አሁንም በሐዘን የምደቆስበት ጊዜ አለ። ደግሞም እንዲህ ያለው ስሜት የሚመጣብኝ በድንገት ነው።”—ኮስታስ

አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ የኮስታስን ስሜት ትጋራ ይሆናል። የትዳር ጓደኛን፣ የቤተሰብ አባልን ወይም የወዳጅን ሞት ያህል ሥቃይ የሚያስከትል ወይም ልብ የሚሰብር ነገር የለም ማለት ይቻላል። ሐዘን ስለሚያስከትለው ሥቃይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች በዚህ ይስማማሉ። ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሳይካያትሪ የተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ፣ ብዙዎች በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች ዳግም እንደማያገኟቸው ስለሚያስቡ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚሰማቸው ገልጿል። እንደዚህ ዓይነት ከባድ መከራ የደረሰበት ሰው ‘እንዲህ የሚሰማኝ እስከ መቼ ነው? ከዚህ በኋላ እንደገና ደስታ ማግኘት እችል ይሆን? ሐዘኑ ቀለል እንዲልልኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብሎ ያስብ ይሆናል።

ይህ የንቁ! እትም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይዟል። ሐዘን ሊያስከትላቸው የሚችላቸው አንዳንድ ነገሮች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ተገልጸዋል። በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ ደግሞ ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዱ ነጥቦች ተብራርተዋል። አንተም የምትወደውን ሰው በቅርቡ በሞት አጥተህ ከሆነ እነዚህን ርዕሶች ማንበብህ ሊጠቅምህ ይችላል።

በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ የቀረቡት ሐሳቦች መሪር ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች እንደሚያጽናኗቸውና እንደሚረዷቸው ተስፋ እናደርጋለን።

^ አን.3 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።