የጥናት ርዕስ 7
መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!
የይሖዋ ይቅርታ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“በአንተ ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ አለ።”—መዝ. 130:4
ዓላማ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘይቤያዊ አገላለጾችን በመመርመር ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሚያሳየን እውነተኛ ይቅርታ ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንችላለን።
1. ሰዎች “ይቅር ብዬሃለሁ” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ መረዳት ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?
“ይቅር ብዬሃለሁ።” በተለይ በንግግራችን ወይም በድርጊታችን አንድን ሰው ጎድተን ከሆነ እነዚህን ቃላት ስንሰማ ትልቅ እፎይታ ይሰማናል። ይሁንና አንድ ሰው “ይቅር ብዬሃለሁ” ሲል ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል? ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞው እንደተመለሰ መግለጹ ነው? ወይስ ከዚህ በኋላ ስለ ጉዳዩ ማንሳት እንደማይፈልግ መናገሩ ነው? ሰዎች “ይቅር ብዬሃለሁ” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ መረዳት ቀላል ላይሆን ይችላል።
2. ቅዱሳን መጻሕፍት የይሖዋን ይቅርታ የሚገልጹት እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
2 ይሖዋ እኛን ፍጽምና የጎደለንን ሰዎች ይቅር የሚልበት መንገድ አንዳችን ሌላውን ይቅር ከምንልበት መንገድ በእጅጉ የተለየ ነው። ይሖዋ የሚያሳየን ይቅርታ በዓይነቱ ልዩ ነው። መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “በአንተ ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ አለና፤ ይህም ሰዎች አንተን እንዲፈሩ ያደርጋል” ብሏል። a (መዝ. 130:4) አዎ፣ የይሖዋ ይቅርታ እውነተኛ ይቅርታ ነው። የይቅርታን ትክክለኛ ትርጉም መረዳት የምንችለው ከእሱ ነው። በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የይሖዋን ይቅርታ ለመግለጽ የተጠቀሙበት የዕብራይስጥ ቃል ሰዎች የሚያሳዩትን ይቅርታ ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም።
3. የይሖዋ ይቅርታ ከእኛ ይቅርታ የሚለየው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 55:6, 7)
3 ይሖዋ አንድን ሰው ይቅር ሲል ኃጢአቱን ይደመስስለታል። ከእሱ ጋር የነበረው ዝምድናም ሙሉ በሙሉ ይታደሳል። የይሖዋ ይቅርታ አስደናቂ በሆነ መንገድ የተሟላና የተትረፈረፈ ነው።—ኢሳይያስ 55:6, 7ን አንብብ።
4. ይሖዋ የይቅርታን ትክክለኛ ትርጉም እንድንረዳ የሚያግዘን እንዴት ነው?
4 የይሖዋ ይቅርታ ከእኛ ይቅርታ የሚለይ ከሆነ፣ እኛ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች የይቅርታን ትክክለኛ ትርጉም መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የተለያዩ ዘይቤያዊ አገላለጾችን በመጠቀም ይቅርታውን እንድንረዳ ያግዘናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች አንዳንዶቹን እንመረምራለን። እነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች ይሖዋ ኃጢአትን የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም በኃጢአቱ ሳቢያ የተበላሸውን ዝምድና የሚያድሰው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። እነዚህን ምሳሌዎች መመርመራችን በተለያዩ መንገዶች ይቅርታውን ለሚያሳየን ሩኅሩኅ አባታችን ያለንን አድናቆት ያሳድግልናል።
ይሖዋ ኃጢአትን ያስወግዳል
5. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ይላል ሲባል ምን ማለት ነው?
5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአት ከከባድ ሸክም ጋር ተመሳስሏል። ንጉሥ ዳዊት፣ የሠራቸውን ኃጢአቶች አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉና፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል።” (መዝ. 38:4) ሆኖም ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ይላል። (መዝ. 25:18፤ 32:5) በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “ይቅር ማለት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ “ማንሳት” ወይም “መሸከም” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የኃጢአታችንን ሸክም ከትከሻችን ላይ እንደሚያነሳና ተሸክሞ እንደሚወስድልን ሊቆጠር ይችላል።
6. ይሖዋ ኃጢአታችንን ከእኛ ምን ያህል አርቆ ይወስደዋል?
6 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ምን ያህል ከእኛ አርቆ እንደሚወስደው የሚያሳይ ሌላ ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። መዝሙር 103:12 “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ” ይላል። ምሥራቅና ምዕራብ በተለያዩ ጽንፎች የሚገኙ አቅጣጫዎች ናቸው። ፈጽሞ ሊገናኙም አይችሉም። በሌላ አባባል፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ከምንገምተው በላይ ከእኛ አርቆ ይወስደዋል ማለት ነው። የይሖዋን ይቅርታ የሚያሳይ እንዴት ያለ የሚያጽናና አገላለጽ ነው!
7. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን የሚያስወግድበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው? (ሚክያስ 7:18, 19)
7 ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ኃጢአታችንን ከእኛ አርቆ ይወስደዋል ሲባል ኃጢአታችንን ይዞት ይኖራል ማለት ነው? በፍጹም። ንጉሥ ሕዝቅያስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ” ብሏል። የግርጌ ማስታወሻው ደግሞ “ኃጢአቴን ሁሉ ከእይታህ አስወገድክ” ይላል። (ኢሳ. 38:9, 17 ግርጌ) ይህ ዘይቤያዊ አገላለጽ፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት አንስቶ ከእይታ አርቆ እንደሚጥለው ያመለክታል። ይህ አገላለጽ “[ኃጢአቴን] ያልነበረ ያህል አደረግከው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚክያስ 7:18, 19 ላይ ይህን ነጥብ ይበልጥ የሚያጎላ ሌላ ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጥቅሱ፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ወደ ጥልቅ ባሕር እንደሚጥለው ይናገራል። በጥንት ዘመን፣ ወደ ጥልቅ ባሕር የተጣለን ነገር መልሶ ማግኘት የሚቻልበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረም።
8. እስካሁን ምን ተምረናል?
8 ከእነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች እንደተማርነው ይሖዋ ይቅር ሲለን ከኃጢአት ሸክም ይገላግለናል። በእርግጥም ዳዊት እንደተናገረው “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤ ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።” (ሮም 4:7, 8) እውነተኛ ይቅርታ ማለት ይህ ነው!
ይሖዋ ኃጢአትን ይደመስሳል
9. ይሖዋ የይቅርታውን ጥልቀት ለመግለጽ የትኛውን ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል?
9 ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት በቤዛው አማካኝነት የሚደመስሰው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ለመርዳት ሌሎች ዘይቤያዊ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ኃጢአትን አጥቦ እንደሚያስወግድ ተገልጿል። በውጤቱም ኃጢአተኛው መንጻት ይችላል። (መዝ. 51:7፤ ኢሳ. 4:4፤ ኤር. 33:8) ይሖዋ የእሱ ይቅርታ የሚያስገኘውን ውጤት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላም እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል።” (ኢሳ. 1:18) ቀይ ቀለም ነክቶት የመነቸከን ጨርቅ ማስለቀቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ በዚህ ዘይቤያዊ አገላለጽ አማካኝነት ኃጢአታችን ጨርሶ የማይታይበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ታጥቦ እንደሚነጻ ዋስትና ሰጥቶናል።
10. ይሖዋ የይቅርታውን ታላቅነት ለመግለጽ የትኛውን ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል?
10 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ኃጢአት ‘ከዕዳ’ ጋርም ተመሳስሏል። (ማቴ. 6:12 ግርጌ፤ ሉቃስ 11:4 ግርጌ) ስለዚህ በይሖዋ ላይ ኃጢአት በሠራን ቁጥር ዕዳ ውስጥ ይበልጥ እየተዘፈቅን እንደምንሄድ ሊቆጠር ይችላል። ለይሖዋ መክፈል የሚጠበቅብን ዕዳ በጣም ከፍተኛ ነው! ሆኖም ይሖዋ ይቅር ሲለን መክፈል የሚጠበቅብንን ዕዳ ሙሉ በሙሉ እንደሚሰርዝልን ሊቆጠር ይችላል። አንድን ኃጢአት ይቅር ካለን በኋላ ዕዳውን እንድንከፍል አይጠብቅብንም። ይሖዋ ይቅር ሲለን የሚሰማንን እፎይታ የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
11. መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኃጢአታችን ይደመሰሳል’ ሲል ምን ማለቱ ነው? (የሐዋርያት ሥራ 3:19)
11 ይሖዋ ዕዳችንን ወይም ኃጢአታችንን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ይደመስሰዋል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።) አንድን ዕዳ ለመሰረዝ ከመዝገቡ ላይ ቁጥሩን መሰረዝ ይቻላል። ሆኖም የተሰረዘው ቁጥር አሁንም ከሥር ሊታይ ይችላል። መደምሰስ የሚለው ቃል ግን ከዚህ ያለፈ ነገርን ያመለክታል። ይህን ዘይቤያዊ አገላለጽ ለመረዳት፣ በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ከካርቦን፣ ከሙጫ እና ከውኃ የተሠራ እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። አንድ ሰው በእርጥብ ስፖንጅ ጽሑፉን ሙልጭ አድርጎ ሊያጠፋው ይችላል። ስለዚህ ዕዳ “ተደምስሷል” ሲባል ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ነው። ቀደም ሲል ተጽፎ የነበረውን ጽሑፍ ጨርሶ ማየት አይቻልም። መዝገቡ ያልነበረ ያህል ይሆናል። ይሖዋ ኃጢአታችንን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንደሚደመስሰው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!—መዝ. 51:9
12. ኃጢአታችን ጥቅጥቅ ባለ ደመና ይሸፈናል ሲባል ምን ማለት ነው?
12 ይሖዋ ኃጢአታችንን የሚደመስሰው እንዴት እንደሆነ ለመግለጽ ተመሳሳይ ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፦ “በደልህን በደመና፣ ኃጢአትህንም ጥቅጥቅ ባለ ደመና እሸፍነዋለሁ።” (ኢሳ. 44:22) ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል በደላችንን ጥቅጥቅ ባለ ደመና የመሸፈን ያህል ከእይታ ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው።
13. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲለን ምን ይሰማናል?
13 ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በኋላ የኃጢአቱን ቆሻሻ ዕድሜ ልካችንን ይዘነው እንደምንኖር ሊሰማን አይገባም። በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት ዕዳችን ሙሉ በሙሉ ተሰርዞልናል። የዕዳችን መዝገብ እንኳ ሊታይ አይችልም። ለኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ እንዲህ ያለውን እውነተኛ ይቅርታ ከይሖዋ እናገኛለን።
ይሖዋ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያድስልናል
14. ይሖዋ “ይቅር ብያችኋለሁ” ሲለን በእርግጥ ይቅር እንዳለን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
14 ከይሖዋ የምናገኘው እውነተኛ ይቅርታ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። በጥፋተኝነት ስሜት እንዳንዋጥም ይረዳናል። ይሖዋ በልቡ ቂም እንደያዘብንና እኛን የሚቀጣበትን መንገድ እየፈለገ እንዳለ በማሰብ መስጋት አይኖርብንም። ይሖዋ ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም። ይሖዋ “ይቅር ብያችኋለሁ” ሲለን በእርግጥ ይቅር እንዳለን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? ነቢዩ ኤርምያስ፣ ይሖዋ እንዲህ እንዳለ ጽፏል፦ “በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም።” (ኤር. 31:34) ሐዋርያው ጳውሎስም ይህን ሐሳብ በመጥቀስ “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 8:12) ይሁንና ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
15. ይሖዋ ኃጢአታችንን አያስታውስም ሲባል ምን ማለት ነው?
15 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማስታወስ” ወይም “ማሰብ” የሚለው ቃል አንድን ነገር ወደ አእምሮ ማምጣትን ብቻ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ እርምጃ መውሰድንም ያካትታል። ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀለው ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ጠይቆታል። (ሉቃስ 23:42, 43) ይህን ሲል፣ ኢየሱስ በዚያ ወቅት ስለ እሱ እንዲያስብ መጠየቁ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ፣ ወንጀለኛውን በማስነሳት እርምጃ እንደሚወስድ ይጠቁማል። ስለዚህ ይሖዋ ኃጢአታችንን አያስታውስም ሲባል በኃጢአታችን ምክንያት እርምጃ አይወስድብንም ማለት ነው። አንድን ኃጢአት ይቅር ካለን በኋላ ወደፊት በዚያ ኃጢአት የተነሳ አይቀጣንም።
16. መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ ይቅርታ የሚያስገኘውን ነፃነት የሚገልጸው እንዴት ነው?
16 መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ ይቅርታ የሚያስገኘውን ነፃነት ለመግለጽ ሌላ ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። ባለብን የኃጢአት ዝንባሌ የተነሳ “የኃጢአት ባሪያዎች” እንደሆንን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሆኖም ለይሖዋ ይቅርታ ምስጋና ይግባውና ከኃጢአት ባርነት ‘ነፃ ወጥተናል።’ (ሮም 6:17, 18፤ ራእይ 1:5) አዎ፣ የይሖዋ ይቅርታ ከባርነት ነፃ መውጣት የሚያስገኘውን ዓይነት ደስታ ያስገኝልናል።
17. የይሖዋ ይቅርታ ፈውስ የሚያስገኝልን እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 53:5)
17 ኢሳይያስ 53:5ን አንብብ። አሁን ደግሞ የመጨረሻውን ዘይቤያዊ አገላለጽ እንመልከት። ኃጢአተኞች በመሆናችን መጽሐፍ ቅዱስ በሚገድል በሽታ ከተያዙ ሰዎች ጋር ያመሳስለናል። ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ባዘጋጀው ቤዛዊ መሥዋዕት የተነሳ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተፈወስን ተገልጿል። (1 ጴጥ. 2:24) ቤዛው፣ በመንፈሳዊ ሕመማችን ምክንያት የተበላሸው ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ሙሉ በሙሉ እንዲታደስ ያስችላል። ከከባድ ሕመም የተፈወሰ ሰው ታላቅ ደስታ እንደሚሰማው ሁሉ እኛም በይሖዋ ይቅርታ ምክንያት በመንፈሳዊ በመፈወሳችንና የይሖዋን ሞገስ መልሰን በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን።
የይሖዋ ይቅርታ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
18. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ከይሖዋ ይቅርታ ጋር የተያያዙ ዘይቤያዊ አገላለጾች በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል? (“ይሖዋ ይቅር የሚለን እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
18 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ከይሖዋ ይቅርታ ጋር የተያያዙ ዘይቤያዊ አገላለጾች በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል? ይሖዋ ይቅር የሚለው በተሟላ ሁኔታና በዘላቂነት ነው። ይህም ከሰማዩ አባታችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ይቅርታ ስጦታ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ይቅርታ የሚያደርግልን ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ባለው ፍቅርና በጸጋው ተነሳስቶ ነው። እንዲህ ያለው ይቅርታ ማንም ሰው ይገባኛል የሚለው መብት አይደለም።—ሮም 3:24
19. (ሀ) ለምን ነገር አመስጋኝ ልንሆን ይገባል? (ሮም 4:8) (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 ሮም 4:8ን አንብብ። ይሖዋ እውነተኛ ይቅርታ የሚያሳይ አምላክ በመሆኑ ሁላችንም በጣም አመስጋኞች ነን! (መዝ. 130:4) ይሁንና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘታችን የተመካው በአንድ አስፈላጊ ነገር ላይ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ. 6:14, 15) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የይሖዋን ይቅርታ መኮረጃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች ያብራራል።
መዝሙር 46 ይሖዋ እናመሰግንሃለን
a የዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ እዚህ ላይ የሚጠቀምበት አገላለጽ ለየት ያለ ይቅርታን የሚያመለክት ነው። ይህም ሌሎች የይቅርታ ዓይነቶች ቢኖሩም ይሄኛው ይቅርታ ብቸኛው እውነተኛ ይቅርታ እንደሆነ የሚጠቁም ነው። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ወሳኝ ነጥብ በግልጽ አያስተላልፉም። አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ግን መዝሙር 130:4ን ያስቀመጠው ለየት ባለ መንገድ ነው።