ሁሉም ሰው ጥሩ ጤና የሚያገኝበት ጊዜ ቀርቧል!
ሁሉም ሰው ጥሩ ጤና የሚያገኝበት ጊዜ ቀርቧል!
“በአሁኑ ጊዜ ከበሽታ ሙሉ በሙሉ ነፃ የመሆን ጽንሰ ሐሳብ . . . በእጅጉ እየተስፋፋ መጥቷል” ሲል ፎከስ የተሰኘው የጀርመን የዜና መጽሔት ዘግቧል። ሆኖም ይህ ሐሳብ አዲስ አይደለም። ፈጣሪ መጀመሪያ ላይ ሰብዓዊ ሕይወት ሲፈጥር የሰው ልጆች እንዲታመሙ ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። ለሰው ልጆች የነበረው ዓላማ “የዓለም ሕዝብ ሁሉ ጥሩ ጤና እንዲኖረው” ማድረግ ብቻ አልነበረም። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ፈጣሪያችን ዓላማው እያንዳንዱ ሰው ፍጹም ጤና እንዲያገኝ ነበር!
ታዲያ ሁላችንም በሕመምና በበሽታ የምንሠቃየው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ የሰው ዘር ሁሉ ወላጆች የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን ፍጹም አድርጎ እንደፈጠራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የፍጥረት ሥራውን ከጨረሰ በኋላ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።” አፍቃሪው ፈጣሪያችን ሰብዓዊ ሕይወት በበሽታና በሞት እንዲጠቃ ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። ሆኖም አዳምና ሔዋን በተሰጣቸው የሕይወት ጎዳና ለመመላለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ በቀሩ ጊዜ ኃጢአት ሠሩ። የአዳም ኃጢአት ያስከተለው ውጤት ሞት ሲሆን ይህም ለሰው ልጆች ሁሉ ተላልፏል።—ዘፍጥረት 1:31፤ ሮሜ 5:12
ይሖዋ የሰው ልጆችን እንዲሁ አልተዋቸውም። በተጨማሪም ለእነሱም ሆነ ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ አልተወም። ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ ቀድሞው ጤናማ ሁኔታ ለመመለስ ያለውን ዓላማ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ አሳውቋል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክ በሽታን የመፈወስ ኃይል እንዳለው በተግባር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ዓይነ ሥውርነትን፣ የሥጋ ደዌን፣ የመስማት ችግርን፣ ድሮፕሲ የተሰኘን የሰውነት ሕብረ ሕዋሳትን የሚያሳብጥ በሽታን፣ የሚጥል በሽታንና ሽባነትን ፈውሷል።—ማቴዎስ 4:23, 24፤ ሉቃስ 5:12, 13፤ 7:22፤ 14:1-4፤ ዮሐንስ 9:1-7
አምላክ በቅርቡ መሲሐዊ ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ዓለም ጉዳዮች በቁጥጥሩ ሥር እንዲያደርግ መመሪያ ይሰጠዋል። በእሱ አስተዳደር ሥር የሚከተለው የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል:- “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም፣ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።” (ኢሳይያስ 33:24) ይህ የሚፈጸመው እንዴት ነው?
ነቢዩ “በደላቸው ይቅር” ስለሚባልላቸው ሰዎች እንደጻፈ እንመለከታለን። በመሆኑም ለበሽታ ዋነኛ መንስኤ የሆነው የሰው ልጅ የወረሰው ኃጢአት ይወገዳል። እንዴት? የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ ለታዛዥ የሰው ልጆች ጥቅም ላይ ስለሚውል ለበሽታና ለሞት ምክንያት የሆነው ራእይ 21:3, 4፤ ማቴዎስ ምዕራፍ 24፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ነገር ይወገዳል። በመላዋ ምድር ላይ ገነታዊ ሁኔታ ይሰፍናል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ዮሐንስ “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ሲል ጽፏል። ይህ የሚፈጸምበት ጊዜ በጣም ቀርቧል!—ሚዛን መጠበቅ
እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ሕመምና በሽታ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ሆነው መቀጠላቸው አይቀርም። በመሆኑም ሰዎች ስለ ራሳቸው ጤናም ሆነ ስለሚወዷቸው ሰዎች ጤና ማሰባቸው አግባብነት ያለው ነው።
በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች በሕክምናው ሙያ መስክ የሚደረጉትን ጥረቶች በእጅጉ ያደንቃሉ። ጤናማ ለመሆን ወይም ጤንነታቸውን ጠብቀው ለመቀጠል ምክንያታዊ የሆኑ እርምጃዎች ይወስዳሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ከበሽታ ነፃ የሆነ ጊዜ እንደሚመጣ የሚሰጠው ተስፋ በዚህ ረገድ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። መሲሐዊው ንጉሥ የሰው ልጆችን ጉዳዮች መቆጣጠር እስኪጀምር ድረስ ፍጹም ጤና ማግኘት የማይታሰብ ነገር ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው እጅግ አስደናቂ የሆኑት ግኝቶች እንኳ የሕክምና ሳይንስ በዛፉ ጫፍ ላይ ወዳሉት በደንብ የበሰሉ እንጆሪዎች እንዲደርስ ማለትም ለእያንዳንዱ ሰው ጥሩ ጤና እንዲያጎናጽፍ አላስቻሉትም።
“የዓለም ሕዝብ ሁሉ ጥሩ ጤና እንዲኖረው” ለማድረግ የታለመው ግብ በቅርቡ ዳር ይደርሳል። ይህ የሚሆነው ግን በተመድ ወይም በዓለም የጤና ድርጅት፣ በአካባቢ ጥበቃ ፕላን አውጪዎች፣ በማኅበራዊ ለውጥ አራማጆች ወይም በሐኪሞች አይደለም። ይህን የሚያከናውነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የሰው ልጅ በመጨረሻ “ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” በሚደርስበት ጊዜ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል!—ሮሜ 8:21
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሁሉም ሰው የተሟላ ጤንነት ይኖረዋል