የችግሩ ክብደት ምን ያህል ነው?
የችግሩ ክብደት ምን ያህል ነው?
ኸሊ መሊን የተባለች የሦስት ሳምንት ሕፃን በጥቅምት ወር 1997 ጆሮዋ ቆሰለባት። ቁስሉ ቶሎ ባለመዳኑ ዶክተሯ ዘመናዊ የሆነ አንቲባዮቲክ መድኃኒት አዘዘላት። በቀላሉ የሚድን ዓይነት ቁስል ነበር። ሆኖም ቶሎ አልድን አለ። የተለያዩ መድኃኒቶች ቢሰጧትም ቁስሉ ተመላለሰባት።
ኸሊ ገና አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላት የተለያዩ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ለ17 ዙር ወሰደች። ከዚያም 1 ዓመት ከ9 ወር እንደሞላት ከወትሮው የከፋ ቁስል ወጣባት። የመጨረሻ አማራጭ ነው የተባለ አንቲባዮቲክ ለ14 ቀናት በመርፌ ከተሰጣት በኋላ ቁስሉ ሙሉ በሙሉ ዳነ።
እንዲህ ያለ ሁኔታ በሕፃናትና በአረጋውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰው ላይ በብዛት እየታየ መጥቷል። በአንድ ወቅት በአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በቀላሉ ይድኑ የነበሩ በሽታዎች ዛሬ በተለያየ ዕድሜ ለሚገኙ ብዙ ሰዎች መታመም፣ እንዲያውም መሞት ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል። አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች የማይደፍሯቸው ጀርሞች ከ1950 ወዲህ በአንዳንድ ሆስፒታሎች ከባድ ችግር ፈጥረዋል። ከዚያም በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ዓመታት አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቀው ገቡ።
ውሎ አድሮ የሕክምና ተመራማሪዎች አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች የበዙት ሰዎችና እንስሳት ብዙ አንቲባዮቲኮችን አላግባብ በመውሰዳቸው ምክንያት እንደሆነ መግለጽ ጀመሩ። ከእነዚህ የሕክምና ባለሞያዎች መካከል አንዱ በ1978 አንቲባዮቲኮችን አላግባብ መውሰድ “ፈጽሞ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” ብለዋል። ስለሆነም በ1990ዎቹ ዓመታት እንደሚከተሉት ያሉ የዜና አምድ ርዕሶች በመላው ዓለም ብቅ ብለዋል:- “መድኃኒት የማይደፍራቸው ጀርሞች መጡ፣” “አይበገሬ ጀርሞች ሥር ሰደዱ” እና “አደገኛ መድኃኒቶች—አንቲባዮቲኮችን አላግባብ መጠቀም ለአይበገሬ ጀርሞች መቀፍቀፍ ምክንያት ሆኗል።”
እነዚህ ዘገባዎች የተጋነኑ ናቸው? የታወቁ የሕክምና ድርጅቶች እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ዘገባዎች በፍጹም የተጋነኑ አይደሉም። የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላይ ዳይሬክተር ስለ ኢንፌክሽን በሽታዎች ባቀረቡት የ2000 ሪፖርት እንዲህ ብለዋል:- “በአዲሱ ሺህ ዓመት መባቻ ላይ የሰው ልጅ ሌላ ከባድ ችግር ተጋርጦበታል። ከዚህ በፊት በቀላሉ ይድኑ የነበሩ በሽታዎች . . . ዛሬ መድኃኒት የማይደፍራቸው እየሆኑ መጥተዋል።”
ችግሩ ምን ያህል ከባድ ነው? “መድኃኒት የማይደፍራቸው ጀርሞች እየበዙ መሄዳቸው የኢንፌክሽን በሽታዎችን ለማዳን የምናደርገውን ጥረት እያመከነብን ይገኛል” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ዘግቧል። እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ባልነበሩበት ዘመን ወደነበረው ሁኔታ እየተመለሰ ነው የሚሉ ሊቃውንት በርክተዋል።
መድኃኒት የማይደፍራቸው ረቂቅ ተሕዋሳት ሳይንሳዊ ጥረቶችን ሁሉ አሸንፈው ዓለማችንን በቁጥጥራቸው ሥር ሊያደርጉ የቻሉት እንዴት ነው? አንድ ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ለመጠበቅ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ይኖራል? አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸውን ጀርሞች ለማሸነፍ ምን ዓይነት መፍትሔዎች ይኖራሉ? በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክራለን።