በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በበለጸገ ዓለም ውስጥ ድሆች የበዙት ለምንድን ነው?

በበለጸገ ዓለም ውስጥ ድሆች የበዙት ለምንድን ነው?

በበለጸገ ዓለም ውስጥ ድሆች የበዙት ለምንድን ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ “ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 26:11) ኢየሱስ ከኖረበት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ በርካታ ሰዎች በድህነት ይሠቃያሉ። ከፍተኛ የሀብት ክምችት ባለበት በዚህ ዓለም ውስጥ ይህን ያህል ብዙ ሰዎች በድህነት የሚማቅቁት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች፣ ሰዎች ድሃ የሚሆኑት የተሳሳተ ውሳኔ ስለሚያደርጉ እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ሐሳብ በተወሰነ መጠን ትክክል ሊሆን ይችላል። የአልኮል መጠጥ፣ የአደገኛ ዕፅና የቁማር ሱስ ያለባቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ያባክናሉ። ይሁን እንጂ በድህነት የሚኖሩ ሁሉም ሰዎች ለዚህ ዓይነቱ ሕይወት የተዳረጉት የተሳሳተ እርምጃ ስለወሰዱ ነው ማለት አይቻልም።

በኢንዱስትሪው ዓለም በሚደረጉ ለውጦች ምክንያት በርካቶች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል። በፍጥነት እየጨመረ በሚሄደው የሕክምና ወጪ የተነሳ ዕድሜ ልካቸውን ያጠራቀሙት ገንዘብ የተሟጠጠባቸው ሠራተኞችም ብዙ ናቸው። ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደዚህ አዘቅት ውስጥ የገቡት በራሳቸው ጥፋት አይደለም። ቀጥለን እንደምንመለከተው በድህነት የሚማቅቁት ሰዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ ለችግሩ ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች ማስቀረት አይችሉም።

ከታሪክ የሚገኝ ትምህርት

በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ዓለም፣ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ተብሎ በሚታወቀው ከባድ የገንዘብ ችግር ውስጥ ገብታ ነበር። በአንድ አገር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥራ የተባረሩ ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። በርካታ ሰዎች እየተራቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ገበሬዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ወተት ሲደፉ መንግሥታትም ገበሬዎችን በማስገደድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች እንዲገደሉ አድርገዋል።

እንዲህ የሚያደርጉት ለምን ነበር? በወቅቱ የነበረው የኢኮኖሚ ሥርዓት የግብርና ውጤቶችም ሆኑ ሌሎች ምርቶች ትርፍ እስካላስገኙ ድረስ እንዳይሸጡ ይገድብ ስለነበር ነው። እንደ ወተት፣ ሥጋና ጥራጥሬ ያሉት ነገሮች ለድሆቹ ትልቅ ዋጋ ያላቸው ቢሆኑም እነዚህ ምግቦች በትርፍ መሸጥ ካልቻሉ ዋጋ እንደሌለው ነገር ስለሚቆጠሩ መወገድ ነበረባቸው።

በብዙ ከተሞች ሰዎች ምግብ በማጣታቸው ምክንያት የሕዝብ ዓመጽ ተቀስቅሶ ነበር። አንዳንድ ዜጎች ለቤተሰባቸው ምግብ መግዛት ባለመቻላቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር በጦር መሣሪያ በማስፈራራት ነጥቀው መውሰድ ጀመሩ። ሌሎቹ ግን በረሃብ አለንጋ ይገረፉ ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደርሰዋል። ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደጀመረ አካባቢ የዚህች አገር የኢኮኖሚ ሥርዓት አነስተኛ ገቢ ለነበራቸው ሰዎች ምንም የፈየደላቸው ነገር አልነበረም። ይህ ሥርዓት ለሁሉም ዜጎች ምግብና መጠለያ ከማቅረብ እንዲሁም ሥራ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከማመቻቸት ይልቅ ትርፍ ለማጋበስ ቅድሚያ የሚሰጥ ነበር።

ዛሬ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ

የዓለም ኢኮኖሚ ደርሶበት ከነበረው ቀውስ በማገገሙ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ሀብታም ከመሆናቸውም ሌላ በገንዘብ ረገድ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስተማማኝ አቅም ያላቸው ይመስላል። ዓለም የበለጸገ ቢሆንም ድሆች ሕይወታቸውን ለማሻሻል ያላቸው አጋጣሚ ግን በጣም ውስን ነው። በአንዳንድ አገሮች ስለ ረሃብና ስለ ድህነት የሚገልጹ ሪፖርቶችን መስማት በጣም የተለመደ በመሆኑ ብዙዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ዘገባዎች ማንበብ አሰልቺ ሆኖባቸዋል። ሆኖም በጦርነት ምክንያት ለስደት የተዳረጉ ሰዎች በረሃብ ሲሰቃዩ፣ ፖለቲከኞች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በሚፈጥሩት ውዝግብ ምክንያት በመጋዘን ያለው ምግብ ሲበላሽ እንዲሁም በገበያው ሁኔታ የተነሳ ድሃው ኅብረተሰብ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንኳ ማግኘት አስቸጋሪ እስኪሆንበት ድረስ የዕቃው ዋጋ ሲንር ስንመለከት የኢኮኖሚው ሥርዓት በድህነት የሚማቅቁ ዜጎቹን ፍላጎት ማሟላት እንዳቃተው እንገነዘባለን። የዓለም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የተዋቀረበት መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆችን ያላገናዘበ ነው።

በመሠረቱ በሰዎች የተነደፈ የትኛውም የኢኮኖሚ ሥርዓት የሁሉንም የሰው ዘሮች ቁሳዊ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት አይችልም። ስለ ሕይወት በጥልቅ ያስብ የነበረ አንድ ሰው ከ3,000 ዓመታት በፊት እንዲህ ብሎ ነበር:- “እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።” (መክብብ 4:1) ዛሬም ዓለማችን በቁሳዊ ሀብት ረገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ብትደርስም በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግን ብዙዎች ግፍ ይፈጸምባቸዋል።

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለመውጣት ያላቸው አጋጣሚ በጣም ውስን ነው። ይሁን እንጂ በርካታ ሰዎች የኢኮኖሚ ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ ተምረዋል። እነዚህ ሰዎች ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚጠብቃቸውም ያውቃሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለመኖር የሚደረግ ትግል

ደራሲና ጋዜጠኛ የሆኑት ዴቪድ ሺፕለር ዘ ወርኪንግ ፑር—ኢንቪዝብል ኢን አሜሪካ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩት ሐሳብ፣ አንዳንድ የዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪዎች በኢኮኖሚ ረገድ በገደል አፋፍ ላይ ከመቆም ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል። መጽሐፉ እንዲህ ይላል:- “በጣም ያረጀው አፓርታማ በአስም የሚሠቃየውን ልጅ ሕመም ያባብስበታል፤ ልጁን በቶሎ ሆስፒታል ለማድረስ አምቡላንስ መጠራቱ የሚያስከትለው የሕክምና ወጪ ደግሞ ቤተሰቡ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደርገዋል፤ ይህም ብድር ማግኘት ከባድ እንዲሆንባቸው ስለሚያደርግ በዱቤ መኪና መግዛት ቢፈልጉ ከፍተኛ ወለድ ይጠየቃሉ፤ በዚህ የተነሳ አስተማማኝ ያልሆነ ያገለገለ መኪና ለመግዛት የሚገደዱ ሲሆን ይህ ደግሞ እናትየው በሰዓቷ ሥራ እንዳትገባ እንቅፋት ይፈጥራል፤ ይህም በሥራ ቦታዋ እድገትና የተሻለ ደሞዝ የማግኘት አጋጣሚ እንዳይኖራት ያደርጋል፤ በዚህም ምክንያት ይህች ሴት ከዚህ ያረጀ ቤት ወጥታ የተሻለ መኖሪያ ማግኘት አትችልም።” ይህ ልጅና እናቱ የሚገኙት በዓለም ላይ በጣም ከበለጸጉት አገሮች በአንዱ ውስጥ ቢሆንም ሁልጊዜ የሚኖሩት በስጋት ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጎ ለማድረግ ማሰብ ብቻ በቂ ነው?

በኅዳር ወር 1993 በዋሽንግተን፣ ዲሲ በሚገኝ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የተሰባሰቡ ባለ ሥልጣናት ለአንድ ከባድ ችግር መፍትሔ በመፈላለግ ላይ ነበሩ። እነዚህ ባለ ሥልጣናት ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በዚህች አገር የሚገኙ ቤት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ሊያውሉት ፈልገዋል። እነርሱ እዚያው ስብሰባው ላይ እንዳሉ ከመንገዱ ባሻገር ያለው የአውቶቡስ ማቆሚያ በፖሊሶች፣ በእሳት አደጋ ሠራተኞችና በሕክምና ባለሙያዎች ተጨናነቀ። በዚህ ወቅት የአምቡላንስ ሠራተኞች ቤት የሌላትን አንዲት ሴት አስከሬን እያነሱ ነበር። ይህች ሴት ሞታ የተገኘችው መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት በተቋቋመው በዩናይትድ ስቴትስ የቤቶችና የከተማ ልማት ቢሮ ፊት ለፊት ነበር።

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት ዘጋቢ የቤቶችና የከተማ ልማት ቢሮ ሠራተኛ ለሆኑ አንዲት ሴት ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር፤ እኚህ ሴት በቦታው የተገኙትን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና መኪኖች በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሰዎች ምን ያህል እንደሚረባረቡ መመልከት በጣም ያስገርማል፤ ግለሰቡ በሕይወት እያለ ግን ማንም ዞር ብሎ አያየውም።”

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዓለም በታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታ በነበረችባቸው በ1930ዎቹ ዓመታት አንዲት ስደተኛ እናት ከሦስት ልጆቿ ጋር

[ምንጭ]

Dorothea Lange, FSA Collection, Library of Congress

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንዲህ ባሉ አነስተኛ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች የወር ደሞዛቸው 14 የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በሳምንት 70 ሰዓት እንዲሠሩ ሊገደዱም ይችላሉ

[ምንጭ]

© Fernando Moleres/Panos Pictures