በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕድልህ አስቀድሞ ተወስኗል?

ዕድልህ አስቀድሞ ተወስኗል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ዕድልህ አስቀድሞ ተወስኗል?

አንድ ቀን ጠዋት ሁለት ሰዎች በመኪና ወደ ሥራ እየሄዱ ሳለ አንደኛው ሰውዬ ይኖርበት በነበረው ቤት በኩል በሚያልፍ አቋራጭ መንገድ ለመሄድ አሰቡ። በዚህ መንገድ ላይ እየተጓዙ እያለ በአንድ ቤት መስኮት ውስጥ የእሳት ነበልባል ተመለከቱ። መኪናቸውን ካቆሙ በኋላ ይዘውት የነበረውን መሰላል በመጠቀም የእናትየዋንና የአምስት ልጆቿን ሕይወት አተረፉ። ይህን ሁኔታ አስመልክቶ አንድ ጋዜጣ “የዕድል ጉዳይ ይሆናል” በማለት ዘግቧል።

ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸው ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገር ከእነርሱ በላይ በሆነ ኃይል አስቀድሞ የተወሰነ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የ16ኛው መቶ ዘመን የተሃድሶ አራማጅ የነበረው ጆን ካልቪን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዕድል ለሚለው ቃል አምላክ እያንዳንዱ ሰው ሊከተለው ስለሚገባው የሕይወት አቅጣጫ አስቀድሞ የወሰነው ዘላለማዊ ንድፍ የሚል ፍቺ እንሰጠዋለን። እርሱ ሁሉንም ሰዎች አንድ ዓይነት ሁኔታ እንዲኖራቸው አድርጎ አልፈጠራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶቹ ዘላለማዊ ሕይወት እንዲያገኙ ሌሎቹ ደግሞ ዘላለማዊ ኩነኔ እንዲቀበሉ አስቀድሞ ወስኗል።”

በእርግጥ አምላክ በሕይወታችን ውስጥ ምን እንደምናደርግ እንዲሁም የመጨረሻው ዕጣ ፈንታችን ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ወስኗል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል?

ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው እምነት ምክንያታዊ አይደለም

የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ‘አምላክ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ጨምሮ ሁሉንም ነገሮች ያውቃል፤ እያንዳንዱ ሰው ሕይወቱን እንዴት እንደሚጠቀምበት እንዲሁም አሟሟቱን ጨምሮ የሚሞትበትን ትክክለኛ ቀን አስቀድሞ ያውቃል’ ብለው ያስባሉ። ከዚህ በመነሳት አንድ ሰው ውሳኔ ሲያደርግ፣ ውሳኔው አምላክ ከሚያውቀውና አስቀድሞ ከወሰነለት ውጪ አይሆንም ብለው ያምናሉ። እንደዚያ ካልሆነ አምላክ ሁሉን ያውቃል ማለት አይቻልም። ታዲያ እንዲህ ያለው አመለካከት ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብሎ ማሰብ ምን መደምደሚያ ላይ እንደሚያደርስ እስቲ ተመልከት።

ከአንተ በላይ የሆነ አንድ ኃይል የወደፊት ሁኔታህን አስቀድሞ ከወሰነ ራስህን ከአደጋ ለመጠበቅ የምታደርገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ይሆናል ማለት ነው። ሲጋራ ማጨስህ ወይም አለማጨስህ በጤንነትህም ሆነ በልጆችህ ላይ የሚያስከትለው ችግር አይኖርም፤ እንዲሁም መኪና በምታሽከረክርበት ጊዜ የወንበሩን ቀበቶ ማሰርህ በደኅንነትህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ማለት ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቅድመ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሰዎች ሞት ለሚያስከትል አደጋ የመጋለጣቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። ግዴለሽነት ግን አሳዛኝ ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል።

እስቲ ይህን ሁኔታ ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው። አምላክ ሁሉን ነገር አስቀድሞ የሚያውቅ ከሆነ አዳምንና ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊት እንደማይታዘዙት ያውቅ ነበር ማለት ነው። ይሁንና፣ አምላክ ለአዳም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” መብላት እንደሌለበት አለዚያ ግን እንደሚሞት ሲነግረው ከፍሬው እንደሚበላ አስቀድሞ ያውቅ ነበር ማለት ነው? (ዘፍጥረት 2:16, 17) አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ጥንዶች “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” በማለት ነግሯቸዋል። ታዲያ አምላክ ይህን ሲል አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ እንደሚኖሩ የሚገልጸው አስደናቂ ተስፋ ፍጻሜውን እንደማያገኝ አስቀድሞ አውቆ ነበር? በጭራሽ።—ዘፍጥረት 1:28

አምላክ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች ሁሉ አስቀድሞ ያውቃል ካልን ጦርነትን፣ የፍትሕ መጓደልንና ሌሎች መከራዎችን ጨምሮ በዓለም ላይ ለሚከሰቱት ችግሮች ሁሉ በኃላፊነት የሚጠየቀው እሱ ነው ማለታችን ነው። ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አምላክ ስለ ራሱ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጠናል።

“ምረጥ”

ቅዱሳን መጻሕፍት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እንዲሁም “ፍትሕን ይወዳል” በማለት ይገልጻሉ። በተጨማሪም አምላክ “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ” በማለት ሁልጊዜ ሕዝቦቹን ያሳስባል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ መዝሙር 37:28፤ አሞጽ 5:15) አምላክ፣ ታማኝ ሕዝቦቹ ትክክለኛውን የሕይወት መንገድ እንዲመርጡ ብዙ ጊዜ አበረታቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ወቅት በሙሴ አማካኝነት ለሕዝቡ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳግም 30:19) እዚህ ላይ አምላክ እያንዳንዳቸው ምን ምርጫ እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ወስኖ ነበር? እንዲህ እንዳላደረገ ግልጽ ነው።

ጥንት የአምላክ ሕዝቦች መሪ የነበረው ኢያሱ የአገሩን ሰዎች “የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እናመልካለን” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (ኢያሱ 24:15) የአምላክ ነቢይ የነበረው ኤርምያስም “የምነግርህን የእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ትተርፋለች” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 38:20) ፍትሐዊና አፍቃሪ የሆነ አምላክ ሰዎች ፈጽሞ እንደማይሳካላቸው እያወቀ ገና ለገና በረከት እናገኛለን በሚል ተስፋ ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉ ያበረታታል? በፍጹም። ይህ ዓይነቱ ማበረታቻ ግብዝ የሚያሰኝ ነው።

ስለዚህ ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገር በሕይወትህ የሚገጥምህ ይህ ሁኔታ አስቀድሞ ስለተወሰነብህ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ‘የሚያጋጥሙህ’ ነገሮች ሰዎች በሚያደርጓቸው ጥሩም ሆኑ መጥፎ ውሳኔዎች ምክንያት የሚመጡ ናቸው። (መክብብ 9:11 NW) በመሆኑም ዕድልህ አስቀድሞ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ አንተ ራስህ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ የተመካ ነው።

ምን ይመስልሃል?

▪ አምላክ፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሚሠሩ አስቀድሞ ወስኖ ነበር?—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:16, 17

▪ አምላክ የሰውን ዕድል አስቀድሞ እንዳይወስን የሚያደርጉት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?—መዝሙር 37:28፤ 1 ዮሐንስ 4:8

▪ ምን የማድረግ ኃላፊነት አለብህ?—ኢያሱ 24:15

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቅድመ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሰዎች ሞት ለሚያስከትል አደጋ የመጋለጣቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው