ባል የሚስት ራስ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ባል የሚስት ራስ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
በብዙ አገሮች ውስጥ በሚደረጉ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ተጋቢዎች ቃለ መሐላ በሚፈጸሙበት ጊዜ ሙሽራዋ ለባሏ ለመታዘዝ ቃል መግባቷ የተለመደ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሴቶች በጋብቻ ውስጥ ወንድ የሚስት ራስ ነው የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ያለው አቋም ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅበትና ተግባራዊ ለማድረግ የማይከብድ መሆኑን ትገነዘባለህ።
አምላክ በግልጽ ያስቀመጠው የራስነት ሥልጣን
መጽሐፍ ቅዱስ የራስነት ሥልጣንን በተመለከተ የሚሰጠው በጣም አስፈላጊ መግለጫ በኤፌሶን 5:22-24 ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ይላል:- “ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ ክርስቶስ፣ . . . [ለቤተ ክርስቲያን] ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል።” ባል “የሚስቱ ራስ” እንደመሆኑ መጠን በቤተሰብ ውስጥ አመራር የመስጠት ኃላፊነቱን የሚይዝ ሲሆን ሚስት ደግሞ አመራሩን በመከተልና የራስነት ሥልጣኑን በማክበር ትተባበረዋለች።—ኤፌሶን 5:33
አንድ ባል እሱ ራሱ ለአምላክና ለክርስቶስ የሚገዛ በመሆኑ ሥልጣኑ የተገደበ ነው። ሚስቱ የአምላክን ሕግጋት እንድታፈርስም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናዋን እንድትጥስ የማድረግ ሥልጣን አልተሰጠውም። ነገር ግን ይህን ገደብ ሳያልፍ ለቤተሰቡ የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን እንዲያደርግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።—ሮሜ 7:2፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባል የሚስቱን ፍላጎት ከራሱ በማስቀደም የራስነት ሥልጣኑን ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ እንዲጠቀምበት ያዘዋል። ኤፌሶን 5:25 እንዲህ ይላል:- “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” ወደር የማይገኝለትን የክርስቶስን የፍቅር ምሳሌ የሚከተል ባል ሥልጣኑን ራስ ወዳድነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መጠቀም አይፈልግም።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ወንድ ከሚስቱ ጋር “በማስተዋል” እንዲኖር መመሪያ ይሰጠዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7 የ1954 ትርጉም) ይህ በወንድና በሴት መካከል አካላዊና ስሜታዊ ልዩነቶች እንዳሉ ከማስተዋል የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። የሚስቱን ፍላጎቶች መረዳት ያስፈልገዋል።
‘የትዳር አጋርህ ናት’
አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት አለባት ሲባል ውሳኔ በማሳለፍ ረገድ ምንም ድርሻ የላትም ማለት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለባሏ ለአብርሃም ታዛዥ በመሆን በምሳሌነት የተጠቀሰችውን የሣራን ሁኔታ እንመልከት። (1 ጴጥሮስ 3:5, 6) ምቹ መኖሪያዋን በመተው በድንኳን ውስጥ ለመኖር ፈቃደኛ ከመሆን አንስቶ ባሏ ድንገት ለሚያመጣው እንግዳ ምግብ እስከማዘጋጀት ድረስ ከባድና ቀላል በሆኑ ጉዳዮች ለአብርሃም ተገዝታለች። (ዘፍጥረት 12:5-9፤ 18:6) ሆኖም ከበድ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከአብርሃም የተለየ አመለካከት አንጸባርቃለች። ቁባቱን አጋርንም ሆነ የመጀመሪያ ልጁን እስማኤልን ከቤት እንዲያስወጣቸው በፈለገች ጊዜ ይህ ሁኔታ ታይቷል። አምላክ ሣራን ከመገሠጽ ይልቅ “የምትልህን ሁሉ ስማ” በማለት ለአብርሃም ነግሮታል። ሣራ፣ እሷ ራሷ አጋርንና እስማኤልን ለማባረር ከመሞከር ይልቅ አብርሃም እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በመጠበቅ ለእሱ መገዛቷን ቀጥላለች።—ዘፍጥረት 21:8-14
የሣራ ምሳሌ፣ ሚስት ባሏ የሚላትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የባሏ ‘አጋር’ የመሆን ክቡር ቦታ እንዳላትም ይጠቁማል። (ሚልክያስ 2:14) አጋሩ እንደመሆኗ መጠን ከቤተሰቡ ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች አስመልክቶ ጠቃሚ ሐሳቦችን ታቀርባለች፤ እንዲሁም ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ጨምሮ ከቤተሰቡ ጋር የተያያዙ ሌሎች በርካታ ነገሮችን የማስተዳደር የተወሰነ ሥልጣን ተሰጥቷታል። እርግጥ ነው፣ ባል የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ መጠን የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ ያለበት እሱ ነው።—ምሳሌ 31:10-31፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:14
ለጋብቻ መሥራች አክብሮት ማሳየት
ይሖዋ አምላክ ወንድና ሴትን ከፈጠረ በኋላ በመካከላቸው እንደ ቅዱስ ጥምረት የሚታየውን ጋብቻን መሠረተ። (ዘፍጥረት 2:18-24) በተጨማሪም አምላክ ባልም ሆነ ሚስት በቤተሰቡ ውስጥ ምን ቦታ እንዳላቸው በግልጽ የተናገረ ሲሆን ይህን ቦታቸውን ጠብቀው መኖራቸው ከፍተኛ ደስታ ያመጣላቸዋል።—ዘዳግም 24:5፤ ምሳሌ 5:18
ይሖዋ የጋብቻ መሥራች እንደመሆኑ መጠን ትዳሩ የሚመራበትን መንገድ በሚመለከት መመሪያ የማውጣት መብትም ሆነ ችሎታው አለው። የትዳር ጓደኛሞች፣ ጥቅም ስለሚያስገኝላቸው ብቻ ሳይሆን ለአምላክ መለኮታዊ ሥልጣን ካላቸው አክብሮት የተነሳ ክቡር የሆነውን ቦታቸውን በመጠበቅ እሱ ያወጣውን የራስነት ሥርዓት የሚቀበሉ ከሆነ ሞገሱን የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ድጋፉም አይለያቸውም።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የራስነትን ሥልጣን በተመለከተ ፍጹም ምሳሌ የተወልን ማን ነው?—ኤፌሶን 5:25
▪ አምላክ አንድ ባል በሚኖረው ሥልጣን ላይ ገደብ አድርጓል?—1 ቆሮንቶስ 11:3
▪ የጋብቻም ሆነ የራስነት ሥርዓት ዓላማው ምንድን ነው?—ምሳሌ 5:18
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የራስነትን ሥልጣን ክርስቶስ በተወው ምሳሌ መሠረት መወጣት ለሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ደስታና እርካታ ያመጣላቸዋል