ጥቃቅኖቹ የኒሂሃው ውድ ሀብቶች
ጥቃቅኖቹ የኒሂሃው ውድ ሀብቶች
ሃዋይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በየዓመቱ ክረምት ላይ የሚነሳው ማዕበል “ክልክል ደሴት” በመባል ከምትታወቀውና ከሃዋይ ደሴቶች አንዷ ከሆነችው ከኒሂሃው ደሴት ዳርቻ ጋር ይጋጫል። በዚህ ጊዜ ቀንድ አውጣን ከመሰሉ ጥቃቅን የባሕር ፍጥረታት የሚገኙ ዛጎሎች በማዕበሉ ተገፍተው ወደ ባሕሩ ዳርቻ የሚወጡ ሲሆን በአንዳንዶቹ የባሕሩ ዳርቻዎች ላይ ይቆለላሉ። ደሴቷ 180 ካሬ ሜትር ስፋት ያላት ስትሆን ሰዎች ከሚኖሩባቸው ሰባት የሃዋይ ደሴቶች መካከል ትንሿ ናት። በእሳተ ገሞራ አማካኝነት የተፈጠረችው ይህቺ ትንሽ ደሴት፣ ጥቃቅን ለሆኑት የዓለም ውድ ሀብቶች ማለትም ውብ ለሆኑት ለኒሂሃው ዛጎሎች መገኛ መሆኗ ተስማሚ ነው።
ኒሂሃው፣ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከአጎራባቿ ከካዋይ ደሴት በተለየ በዝቅተኛ ስፍራ ላይ የምትገኝ ስትሆን ድርቅም ያጠቃታል። ይሁንና ኒሂሃው “ክልክል ደሴት” የተባለችው ለምንድን ነው? ኒሂሃው በግለሰብ ይዞታ ሥር የምትገኝ ስትሆን ፈቃድ ያላገኙ ጎብኚዎችም ወደ ደሴቲቱ መግባት አይችሉም። ከሌላው ዓለም ምንም ሳይፈልጉ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩት የደሴቷ ነዋሪዎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያ፣ የቧንቧ ውኃ፣ ሱቆችና ፖስታ ቤት የላቸውም። በዚህች ደሴት ላይ የሚኖሩት 230 ገደማ የሚሆኑ የሃዋይ ተወላጆች ባሕላቸውን ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ በጥንታዊው የሃዋይ ቋንቋ ይነጋገራሉ። ከነዋሪዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ በጎች ወይም ከብቶች በማይጠብቁበት ጊዜ “የወርቅ ማዕድናቸው” የሆኑትን ጥቃቅን ዛጎሎች በመልቀም ሥራ ላይ ይሠማራሉ። *
ሞቃታማ በሆኑት የሃዋይ የክረምት ወራት፣ ቤተሰቦች በኅብረት ሆነው አቧራማ በሆኑት መንገዶች ላይ በእግር ወይም በብስክሌት በመጓዝ ዛጎል ሲሰበስቡ ወደሚውሉባቸው ጥርት ያሉ ዓለታማ የባሕር ዳርቻዎች ይደርሳሉ። ዛጎሎቹ ከተሰበሰቡ በኋላ እንዲደርቁ ጥላ ባለበት ስፍራ ይሰጣሉ። በኋላም በመጠናቸው፣ በዓይነታቸውና በጥራታቸው ይለዩና የሚያማምሩ የአበባ ጉንጉኖች ወይም የአንገት ሐብል ይሠራባቸዋል። በጣም ለምለም በሆኑ ደሴቶች ላይ አብዛኞቹ የአበባ ጉንጉኖች የሚሠሩት ከአበባ ነው። በኒሂሃው ደግሞ ዛጎሎች እንደ “አበባ” ሆነው ያገለግላሉ።
ከባሕር የተገኙ “ዕንቁዎች”
ዛጎሎች በሃዋይ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ጌጣጌጦችን ለመሥራት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በ18ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ካፕቴን ጀምስ ኩክን ጨምሮ በባሕር ላይ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ አሳሾች በሃዋይ የዛጎል ጌጣ ጌጦችን ማግኘታቸውን በማኅደራቸው ላይ ጽፈዋል። በተጨማሪም ወደ አገራቸው ለናሙና የሚሆኑ ጌጣጌጦችን ይዘው የተመለሱ ሲሆን ከናሙናዎቹ መካከል አንዳንዶቹ የተወሰዱት ከኒሂሃው ሳይሆን አይቀርም። ከጊዜ በኋላ፣ ተወዛዋዦችንና የንጉሣውያን ቤተሰቦችን ጨምሮ በሃዋይ የሚኖሩ ታዋቂ ሴቶች የኒሂሃው ደሴትን ማራኪ የአበባ ጉንጉኖች አንገታቸው ላይ ማድረግ ጀመሩ። በ20ኛው መቶ ዘመን፣ የባሕል ዕቃ መሸጫዎች እንዲሁም ቱሪዝምና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሃዋይ በኩል ያለፉ ወታደሮች እነዚህ ልዩ “ዕንቁዎች” ከሃዋይ ውጪ እንዲታወቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በዛሬው ጊዜ፣ ቀደም ሲል ታዋቂ የሆኑ የሃዋይ ሴቶች ሲዋቡባቸው የነበሩትን የሚያማምሩ የአንገት ሐብሎች በቅርብም ሆነ በርቀት በሚገኙ አገሮች ውስጥ ያሉ አድናቂዎቻቸው ሲያጌጡባቸው ይታያል።
አብዛኛውን ጊዜ የአበባ ጉንጉኖችን ለመሥራት የሚያገለግሉት
የኒሂሃው ዛጎሎች በሃዋይ ቋንቋ ሞሚ፣ ላይኪ እና ካሄሌላኒ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። ዛጎሎቹ የተለያየ ቀለምና ዲዛይን ያላቸው መሆኑ ዛጎሎቹን በጥንቃቄ እየሰኩ እጅግ ማራኪ የአንገት ጌጦችን ለሚሠሩት ሰዎች (አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ናቸው) ተፈታታኝ ሆኖም አስደሳች ሥራ ይፈጥርላቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንደ ዕንቁ የሚያንጸባርቁና ሞላላ ቅርጽ ያላቸው 20 ዓይነት ልዩ ልዩ ሞሚዎችን ይጠቀማሉ፤ አንዳንዶቹ ሞሚዎች በጣም ነጭ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጥቁር ቡናማ ቀለም አላቸው። በጣም የሚያብረቀርቁትና 10 ሚሊ ሜትር ርዝመት ብቻ ያላቸው ትንንሽ ሞሚዎች በውድ ዋጋ በሚሸጠው ሌይ ፒካኬ በሚባለው ዲዛይን ሲሠሩ፣ ጣፋጭ መዓዛና ነጭ አበባ ካለው ጃስሚን ከሚባለው ተክል ወይም በሃዋይ ቋንቋ ከፒካኬ ጋር በጣም ይመሳሰላሉ።ጥልፍልፍ ተደርገው የሚሠሩት ለስላሳና አንጸባራቂ የሆኑ ሩዝ የሚመስሉ ላይኪዎች ብዙውን ጊዜ የሃዋይን ሙሽሮች ለማስጌጥ ያገለግላሉ። ከእነዚህ የሚያብረቀርቁ ዛጎሎች አንዳንዶቹ በጣም ነጭ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ፈካ ያለ ወይም ወደ ቢጫ ያደላ ቤዥ ቀለም አላቸው፤ ቡናማ መሥመር ያላቸውም አሉ። በአንድ የጥንት የሃዋይ ገዥ ስም እንደተሰየሙ የሚገመቱት ካሄሌላኒ የሚባሉት ዛጎሎች ርዝመታቸው 5 ሚሊ ሜትር ብቻ ነው። እነዚህ በቀላሉ ሊሰበሩ የሚችሉ የጥምጥም ቅርጽ ያላቸው ዛጎሎች ለመሰካት በጣም አስቸጋሪ ሲሆኑ ከእነሱ የሚሠሩ የአበባ ጉንጉኖችም እጅግ ውድ ናቸው። ከእነዚህ ዛጎሎች አንዳንዶቹ ደማቅ ቀይ ቀለም አላቸው፤ ዋጋው ከሌሎቹ ሦስት እጥፍ በላይ የሚያወጣ ያልተለመደ ዓይነት ደማቅ ሐምራዊ ቀለም ያለው ዛጎልም አለ።
ከኒሂሃው ዛጎል የአበባ ጉንጉን መሥራት
የአበባ ጉንጉን የምትሠራው ሴት የዲዛይኑን ዓይነት ከወሰነች በኋላ በዛጎሎቹ ላይ ያለውን አሸዋ በደንብ ጠርጋ በሹል ወስፌ ትበሳቸዋለች። ምንም እንኳ የምትሠራው በጥንቃቄና በዘዴ ቢሆንም ከሦስቱ ዛጎሎች ውስጥ አንዱ ይሰበራል። በመሆኑም ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ዓመታት ሊፈጅ የሚችለውን የአበባ ጉንጉን ለመሥራት ከሚያስፈልጋት በላይ ዛጎሎችን መሰብሰብ ይኖርባታል ማለት ነው! የአበባ ጉንጉኑን ለማያያዝ ቶሎ በሚደርቅ ሲሚንቶ ወይም ሰም ውስጥ የተነከረ ከናይለን የተሠራ ክር ትጠቀማለች። በባሕላዊው አሠራር መሠረት የአበባ ጉንጉኑ ዳርና ዳር ላይ የጥላ ሰዓት የመሰለ ፑካ የሚባል የአዝራር ቅርጽ ያለው ትንሽ ዛጎል ይደረግለታል። ጫፎቹ በሚያያዙበት ቦታ ላይ ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ለስላሳና ደማቅ ቀለም ያለው ዛጎል ይሰካል።
የተለያዩ ዛጎሎች የመኖራቸውን ያህል ብዙ ዓይነት የአበባ ጉንጉን አሠራሮችም አሉ። ከእነዚህም መካከል ከ150 እስከ 190 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያላቸው በቀጭኑ የተሠሩ ነጫጭ የሞሚ የአበባ ጉንጉኖች፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ጥቃቅን የካሄሌላኒ ዛጎሎች በድርቡ የተሠሩ ወፈር ያሉ የአበባ ጉንጉኖች እንዲሁም ዛጎሎችንና የተክል ፍሬዎችን በማደባለቅ ውስብስብ በሆነ መንገድ የሚሠሩ የአበባ ጉንጉኖች ይገኙበታል። የአበባ ጉንጉን መሥራት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅና ጊዜ የሚፈጅ እንዲሁም በዓይን ላይ ጫና የሚፈጥር ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ጥሩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውና ትዕግሥተኞች የሆኑት በኒሂሃው የሚኖሩ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ማራኪ የሆኑና ውስብስብ ዲዛይን ያላቸው የአበባ ጉንጉኖችን አዘውትረው ይሠራሉ። እያንዳንዱ የአበባ ጉንጉን የራሱ የሆነ ውበት አለው። በመሆኑም ከእነዚህ የአንገት ጌጦች መካከል አንዳንዶቹ ከከበሩ ድንጋዮችና ውድ ከሆኑ ቅርሶች እኩል በብዙ ሺህ ዶላር የሚሸጡት ለምን እንደሆነ ማወቅ አያዳግትም።
ኒሂሃው በአንፃራዊ ሁኔታ ስትታይ ጠፍ፣ ብዙ ሕዝብ የማይኖርባትና ከሌሎቹ የሃዋይ ደሴቶች ርቃ የምትገኝ ናት። ይሁን እንጂ የፈጠራ ችሎታ ላላቸውና ውብ የሆኑ የአበባ ጉንጉኖችን ለሚሠሩት ባለሙያዎቿ ምስጋና ይግባቸውና ከኒሂሃው ፀሐያማ የባሕር ዳርቻዎች ርቀው የሚኖሩ ሕዝቦችም ጭምር “ክልክል ደሴት” የምትባለዋን የኒሂሃውን ሀብቶች ሊጋሩ ችለዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 በሌሎቹም የሃዋይ ደሴቶችና በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ተመሳሳይ የሆኑ የዛጎል ዓይነቶች የሚገኙ ቢሆንም ብዛቱና ጥራቱ ግን ከቦታ ቦታ ይለያያል።
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የደረቁ ዛጎሎች በቀለማቸው፣ በዓይነታቸውና በጥራታቸው ከተለዩ በኋላ ማራኪ የሆኑ የአበባ ጉንጉኖች ይሠሩባቸዋል
[ምንጭ]
© Robert Holmes
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጥመለመሉ “የሞሚ” ዛጎሎች
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© drr.net