በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት የሚኖረው ሕይወት

ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት የሚኖረው ሕይወት

ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት የሚኖረው ሕይወት

ኢየሱስ የሞቱ ሰዎች እንደገና ሕያው እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት የተናገረ ሲሆን ይህ ሁኔታ መፈጸሙ እንደማይቀር ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። “በሚመጣው አዲስ ዓለም [“በዳግም ፍጥረት፣” NW]” ‘የዘላለም ሕይወት እንደሚወርሱ’ ገልጾላቸዋል። ኢየሱስ “በዳግም ፍጥረት” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?—ማቴዎስ 19:25-29

መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሉቃስ በጻፈው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‘በሚመጣው ዘመን’ “የዘላለም ሕይወት” እንደሚቀበሉ ተናግሯል። (ሉቃስ 18:28-30) መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሚመጣው ዘመን’ እና “ዳግም ፍጥረት” ተመሳሳይ እንደሆኑ የሚናገረው ለምንድን ነው?

በግልጽ ማየት እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የተናገረው ይሖዋ አምላክ፣ የሰው ዘር ገነት በሆነችው ምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት እንዲያገኝ የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚያስፈጽም ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ነው። ሰዎች አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት የነበራቸውን ዓይነት ፍጽምና ዳግም ያገኛሉ። ስለዚህ “በሚመጣው ዘመን” በኤደን የአትክልት ሥፍራ የነበሩት ገነት መሰል ሁኔታዎች ‘ዳግም ይፈጠራሉ።’

ገነት ተመልሳ የምትቋቋምበት መንገድ

ኢየሱስ በምድር ሳለ አምላክ በመላው ምድር ላይ ጽድቅን ለማስፈን የሚጠቀምበትን መሣሪያ አስመልክተው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ ልጁን የዚህ መንግሥት ገዢ እንዲሆን ሾሞታል፤ ይህ መንግሥት አምላክ በገነት ውስጥ የነበረው ሁኔታ በመላው ምድር ላይ እንዲሰፍን ለማድረግ ያለውን ዓላማ ከግብ ያደርሳል።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሾመውን ገዢ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ [“ለመስፍናዊ አገዛዙ፣” NW] ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።” (ኢሳይያስ 9:6, 7) ሆኖም ‘በመስፍናዊ አገዛዝ’ የሚተዳደረው ይህ መንግሥት የአምላክን ፈቃድ የሚያስፈጽመው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጠናል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

የአምላክ ልጅ በአባቱ መንግሥት ላይ ‘መስፍናዊ ገዢ’ ሆኖ ሥልጣኑን በሚጠቀምበት ጊዜ ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት ማለትም “በዳግም ፍጥረት” ውስጥ የሚሰፍኑትን ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።

በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን ይመስላል?

የሙታን ትንሣኤ

“መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።”—ዮሐንስ 5:28, 29

“ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ይነሳሉ።]”—የሐዋርያት ሥራ 24:15

በሽታ፣ እርጅና ወይም ሞት አይኖርም

“በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6

“እግዚአብሔርም ራሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4

የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል

“ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።”—መዝሙር 67:6

“በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ። ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ፤ በከተማ ያለውም እንደ ሜዳ ሣር እጅብ ብሎ ይውጣ።”—መዝሙር 72:16

ሁሉም ተስማሚ ቤትና አስደሳች ሥራ ይኖረዋል

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

ወንጀል፣ ዓመፅ ወይም ጦርነት አይኖሩም

“ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ።”—ምሳሌ 2:22

“ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4

ፍርሃት ተወግዶ በሁሉም ቦታ ሰላም ይሰፍናል

“በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።” —ሕዝቅኤል 34:28

“በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:9

በምድር ላይ በማንኛውም ሥፍራ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚሰፍንበት እንዲሁም ሰው ሁሉ አምላክንና ሌሎች ሰብዓዊ ፍጡራንን በሚወድበት በዚያ ዘመን መኖር ምንኛ አስደሳች ይሆናል! (ማቴዎስ 22:37-39) በዚያን ጊዜ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አምላክ “ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ” በማለት ተናግሯል።—ኢሳይያስ 46:11, 12 የ1954 ትርጉም

ስለ ይሖዋ አምላክም ሆነ ቃል ስለገባው አዲስ ዓለም መማር የሚያስፈልግህ ገና ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ይህ አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ? የአምላክ መንግሥት የምድር መንግሥታትን ሁሉ የሚተካቸው እንዴት ነው? ደግሞስ ከዚያ በፊት የሚፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖች ምንድን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።—ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የዚህን መጽሔት ገጽ 32 ተመልከት።

ሰዎች ለብዙ ዓመታት ሲናፍቁት የኖሩት ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ሊመጣ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው። በሞት ያንቀላፉት አብዛኞቹ የሰው ዘሮች እንደገና ሕያው መሆናቸው አይቀርም። ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙት የሚቻል ነገር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የአምላክ ፈቃድ ስለሆነም ጭምር ነው። በእርግጥም ከመቃብር ወጥቶ እንደገና በሕይወት መኖር ይቻላል! ይህ ሕይወት ‘እንደሚመጣ’ የሚጠበቀው ‘እውነተኛው ሕይወት’ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 6:19