በረከት ነው ወይስ እርግማን?
በረከት ነው ወይስ እርግማን?
አንድ ሾፌር በጉዞ ላይ እያለ በድንገት መኪናው ከቁጥጥሩ ውጭ ይሆንበትና መንገድ ዳር ከተተከለ ምሰሶ ጋር ይጋጫል፤ በዚህ ጊዜ አብራው በምትጓዝ ሴት ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ወዲያውኑ በሞባይል ስልኩ ተጠቅሞ እርዳታ ለማግኘት ይደውላል። ይሁን እንጂ መጀመሪያውኑ መኪናው ከቁጥጥሩ ውጭ ሊሆንበት የቻለው እንዴት ነው? ስልክ ተደውሎለት መልስ ለመስጠት ሲል ለቅጽበት ዓይኑን ከመንገዱ ላይ አንስቶ ስለነበረ ነው።
ከዚህ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በረከት ሊሆንልን ወይም እርግማን ሊሆንብን ይችላል፤ ምርጫው በአጠቃቀማችን ላይ የተመካ ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ኋላ ቀር በሆኑት ጊዜ ያለፈባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመጠቀም አይመርጡም። ለምሳሌ ያህል፣ ኮምፒውተሮች ከአድካሚ ሥራዎች የሚገላግሉን ከመሆኑም በላይ ያለ አንዳች ውጣ ውረድ በኢንተርኔት አማካኝነት እንድንገበያይና በባንክ የገንዘብ ዝውውር እንድናደርግ ያስችሉናል፤ እንዲሁም ኢ-ሜይል በመላላክ፣ የድምፅ መልእክት በመለዋወጥ ወይም በኮምፒውተር ላይ በተገጠመ ካሜራ አማካኝነት ከሌሎች ጋር ለመገናኘት ይረዱናል።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጠዋት በየፊናቸው የተሰማሩ የቤተሰብ አባላት እስከ ማታ ድረስ መነጋገር የሚችሉበት መንገድ አልነበረም። ዩኤስኤ ቱደይ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ እንደሚገልጸው በአሁኑ ጊዜ ግን “ሁለቱም ሞባይል ስልክ ካላቸው ባልና ሚስት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሰላም ለመባባል ሲሉ ብቻ በየቀኑ የሚደዋወሉ ሲሆን 64 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ፕሮግራማቸውን ለማቀናጀት ሲሉ ይደዋወላሉ፤ እንዲሁም 42 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ልጆቻቸውን ለማነጋገር በሞባይል ስልክ ይጠቀማሉ።”
ጠቃሚ የሆነው ነገር ችግር እንዲፈጥርብህ አትፍቀድለት
ቴክኖሎጂን ከልክ ባለፈ ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀም በአእምሮም ሆነ በአካል ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?
በአንድ ምዕራባዊ አገር የሚኖሩ በቅርብ የተጋቡ ባልና ሚስትን ሁኔታ እንመልከት። አንድ የዜና ዘገባ እንደገለጸው እነዚህ ባልና ሚስት “በመኪናቸውም ሆነ በስፖርት ማዘውተሪያ ውስጥ ሆነው እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ በተለያየ ክፍል በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ሁልጊዜ በሞባይል ስልካቸው ይደዋወሉ ነበር።” አንዳንድ ጊዜ በስልክ በማውራት በየወሩ 4,000 ደቂቃዎች ይኸውም ከ66 ሰዓታት በላይ የሚያጠፉ ሲሆን ከስልካቸው መላቀቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። የአእምሮ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሃሪስ ስትሬትነር፣ እነዚህ ባልና ሚስት “የሱሰኝነት ምልክት” እንደሚታይባቸው ገልጸዋል። “ግንኙነታቸው የተመሠረተው [በሞባይል ስልካቸው] ላይ የሆነ ያህል ነው።”ከላይ የተጠቀሰው ምሳሌ በጣም የተጋነነ ሊመስል ቢችልም ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ አሳሳቢ የሆነ አዝማሚያ እንዳለ ያሳያል። ብዙ ሰዎች ለአንድ ሰዓትም እንኳ ከሌሎች ጋር ሳይገናኙ ስለመቆየት ማሰቡ እንኳ ይከብዳቸዋል። “በኢ-ሜይል መልእክት ተልኮልን እንደሆነ ሁልጊዜ ማየት ያስፈልገናል፤ ሁልጊዜ ኢንተርኔት መጠቀም ይኖርብናል እንዲሁም ምንጊዜም ከጓደኞቻችን ጋር ፈጣን መልእክት መለዋወጥ ያስፈልገናል” በማለት በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሴት ተናግራለች።
ዶክተር ብራያን ያው፣ ዘ ቢዝነስ ታይምስ ኦቭ ሲንጋፖር በተሰኘ ጋዜጣ ላይ እንደገለጹት ከሌሎች ጋር ለመገናኘት በሚያስችሏችሁ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም “ብዙ ጊዜ የምታጠፉ ከሆነ እንዲሁም በሕይወታችሁ ውስጥ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ችላ በማለት በእነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች የምትጠመዱ ከሆነ ይህ አንድ ችግር እንዳለባችሁ የሚጠቁም ምልክት ነው።” ከዚህም በላይ በእነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠምደው ለብዙ ሰዓታት ብቻቸውን የሚቆዩ ሰዎች አካላዊ እንቅስቃሴ ስለማያደርጉ ለልብ በሽታ፣ ለስኳር በሽታ ወይም ለሌላ ከባድ ሕመም ይጋለጣሉ።
እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ለሌሎች አደጋዎችም የተጋለጡ ናቸው። ሞባይል ስልክን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በቅርብ ጊዜ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው መኪና እየነዱ በእጅ በሚያዙም ሆነ በእጅ መያዝ በማያስፈልጋቸው ስልኮች የሚያወሩ ሾፌሮች የሚያጋጥማቸው ጉዳት ሰክረው መኪና ከሚያሽከረክሩ ሰዎች ጋር የሚመጣጠን ነው! መኪና እየነዱ አጫጭር የጽሑፍ መልእክት መላላክም ሞት ሊያስከትል የሚችል ሲሆን አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ27 ዓመት በታች ከሆኑ አሽከርካሪዎች መካከል ወደ 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት መኪና እየነዱ የጽሑፍ መልእክት ይላላካሉ። ከዚህም በላይ መኪና እየነዳህ በስልክ ለማውራት ወይም የጽሑፍ መልእክት ለመላክ የሚቃጣህ ከሆነ አደጋ ቢደርስብህ ፖሊስና የመኪናህ ኢንሹራንስ ኩባንያ ግጭት ባጋጠመህ ሰዓት ሞባይል ስልክ ስትጠቀም እንደነበረ ለማረጋገጥ ስልክህን ሊያዩት እንደሚችሉ አስታውስ። የስልክ ጥሪ መቀበልም ሆነ መደወል ወይም አጭር የጽሑፍ መልእክት መላላክ እጅግ ውድ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል! * በ2008 በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የደረሰውን የ25 ሰዎች ሕይወት የቀጠፈ የባቡር አደጋ በተመለከተ የተደረገው ምርመራ እንዳሳየው ነጂው ግጭቱ ከመድረሱ ከጥቂት ሴኮንዶች በፊት የጽሑፍ መልእክት ልኮ ነበር። ነጂው ፍሬኑን መያዝ እንኳ አልቻለም ነበር።
ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ልጆች ሞባይል ስልክና ኮምፒውተር እንዲሁም በተለያዩ የሚያዝናኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስለሚጠቀሙ እነዚህን መሣሪያዎች በጥበብና ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ እነዚህን ልጆች መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ለመኖር የሚጥሩ ሰዎች አደጋ ሊያስከትል በሚችል በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሳሉ ትኩረታቸው በምንም ነገር እንዳይሰረቅ ሊጠነቀቁ ይገባል።—ዘፍጥረት 9:5, 6፤ ሮም 13:1
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሌሎች ጋር ለመገናኘት በሚያስችሉህ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ብዙ ጊዜ ታጠፋለህ?