ሁሌ የምንጨቃጨቀው ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
ሁሌ የምንጨቃጨቀው ለምንድን ነው?
ከታች በተገለጸው ታሪክ ውስጥ ሪቸል ከእናቷ ጋር ለተፈጠረው ጭቅጭቅ በሦስት መንገዶች ምክንያት ሆናለች። እነዚህን ምክንያቶች ለይተህ መጥቀስ ትችላለህ? መልስህን ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ፤ ከዚያም በዚህ ርዕሰ ትምህርት መጨረሻ ላይ ከሚገኘው “መልስ” ጋር አመሳክር።
ዕለቱ ረቡዕ ማታ ነው። የ17 ዓመቷ ሪቸል የቤት ውስጥ ሥራዋን ጨርሳ ትንሽ አረፍ ብላ ለመዝናናት ተዘጋጅታለች! ቴሌቪዥኑን ከፍታ በምትወደው ሶፋ ላይ ቁጭ አለች።
ሪቸል ገና ከመቀመጧ እናቷ ብቅ አለች፤ የከፋት ትመስላለች። “ሪቸል! እህትሽ የቤት ሥራዋን ስትሠራ ልትረጂያት ሲገባ ቴሌቪዥን በማየት ጊዜሽን የምታባክኚው ለምንድን ነው? የሚነገርሽን ፈጽሞ አትሰሚም ማለት ነው?” አለቻት።
ሪቸል ለእናቷ በሚሰማ ድምፅ “ጀመረች ደግሞ” በማለት አጉተመተመች።
እናቷም “ምናልሽ የእኔ እመቤት?” በማለት ጠየቀቻት።
ሪቸል በረጅሙ ተንፍሳ ዐይኗን እያጉረጠረጠች “ምንም” ብላ መለሰች።
በዚህ ጊዜ እናቷ በጣም ተናደደች። “በዚህ መንገድ ነው የምትመልሺልኝ?” አለቻት።
ሪቸልም “አንቺስ እንዴት ነው የምታናግሪኝ?” በማለት መለሰችላት።
መዝናናቱ ቀረና . . . ሌላ ጭቅጭቅ ተጀመረ።
1. ․․․․․
2. ․․․․․
3. ․․․․․
አንተስ ሁልጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥምሃል? ከወላጆችህ ጋር ነጋ ጠባ ትጨቃጨቃለህ? ከሆነ አንድ አፍታ ቆም ብለህ ሁኔታውን ለማጤን ሞክር። ብዙውን ጊዜ የሚያጨቃጭቋችሁ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ከሚከተሉት ምርጫዎች ጎን ምልክት አድርግ፤ የሚያጨቃጭቃችሁ ነገር በምርጫው ውስጥ ከሌለ ደግሞ “ሌላ” በሚለው ቦታ ላይ የራስህን ምክንያት ጻፍ።
○ አመለካከት
○ የቤት ውስጥ ሥራዎች
○ አለባበስ
○ ሰዓት እላፊ
○ መዝናኛ
○ ጓደኞች
○ ተቃራኒ ፆታ
○ ሌላ ․․․․․
ኤፌሶን 6:2, 3) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማሰብ ችሎታህን’ እንድታዳብርና የማመዛዘን ችሎታህን እንድትጠቀምበት ያበረታታል። (ምሳሌ 1:1-4፤ ሮም 12:1) እንዲህ ስታደርግ አንዳንድ ጊዜ ከወላጆችህ የተለየ የራስህ የሆነ አመለካከት ማዳበርህ አይቀርም። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በሚያደርጉ ቤተሰቦች ውስጥ ወላጆችና ልጆች በማይስማሙበት ጊዜም ጭምር ሰላማዊ በሆነ መንገድ መወያየት ይችላሉ።—ቆላስይስ 3:13
የሚያጨቃጭቃችሁ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፣ ጭቅጭቅ በአንተም ሆነ በወላጆችህ ላይ ውጥረት ያስከትላል። እርግጥ ነው፣ ጸጥ ብለህ ወላጆችህ በሚናገሩት ሁሉ እንደተስማማህ ማስመሰል ትችላለህ። ይሁንና አምላክ የሚጠብቅብህ እንዲህ እንድታደርግ ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “አባትህንና እናትህን አክብር” በማለት እንደሚያዝ ግልጽ ነው። (ታዲያ የምታደርጉት ውይይት ወደ ቃላት ጦርነት ሳይለወጥ ስሜትህን መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው? “የወላጆቼ ጥፋት ነው። ደግሞም ነጋ ጠባ የሚጨቀጭቁኝ እነሱ ናቸው!” ብሎ መናገር ቀላል ነው። ይሁን እንጂ እስቲ የሚከተለውን አስብበት፦ ወላጆችህን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች እንዲለወጡ ማድረግ ትችላለህ? መለወጥ የምትችለው ራስህን ብቻ ነው። ደስ የሚለው ነገር ውጥረቱን ለማርገብ የበኩልህን ካደረግክ መናገር በምትፈልግበት ጊዜ ወላጆችህም ተረጋግተው የምትለውን ማዳመጣቸው የማይቀር ነው።
ስለዚህ ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር ለማድረግ በበኩልህ ልታደርገው የምትችለውን ነገር እንመልከት። ቀጥሎ የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊ አድርግ፤ በዚህ ረገድ ባደረግከው ለውጥ አንተም ሆንክ ወላጆችህ መደነቃችሁ አይቀርም።
(የመፍትሔ ሐሳብ፦ ልትሠራበት በሚያስፈልግህ ነጥብ ላይ ምልክት አድርግ።)
○ መልስ ከመስጠትህ በፊት አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ደጋግ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:28 የ1980 ትርጉም) ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደተናገሩህ ሲሰማህ አፍህ ላይ የመጣውን ነገር ከመናገር ተቆጠብ። ለምሳሌ ያህል፣ እናትህ “ዕቃ ያላጠብከው ለምንድን ነው? ሰው የሚልህን ፈጽሞ አትሰማም ማለት ነው?” አለችህ እንበል። ወዲያው የሚመጣልህ መልስ “ለምን ትጨቀጭቂኛለሽ?” የሚል ሊሆን ይችላል። እስቲ የማሰብ ችሎታህን አሠራ። እናትህ እንዲህ እንድትልህ ያነሳሳትን ምክንያት ለመረዳት ሞክር። አብዛኛውን ጊዜ “ሁልጊዜ” እና “ፈጽሞ” የሚሉትን አነጋገሮች ቃል በቃል መረዳት የለብህም። እንዲህ ያሉት አነጋገሮች ከበስተጀርባቸው አንድ ነገር እንዳለ የሚጠቁሙ ናቸው። ይህ ነገር ምን ሊሆን ይችላል?
ምናልባት እናትህ የቤት ውስጥ ሥራ ሁሉ በእሷ ላይ እንደተከመረ ስለተሰማት ተበሳጭታ ይሆናል። እንደምትደግፋት የሚያሳይ ሐሳብ እንድትናገር ፈልጋ ሊሆን ይችላል። አሊያም እንዲህ ያለችው ምናልባት የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት የመለገም ልማድ ስላለህ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ “ለምን ትጨቀጭቂኛለሽ?” ብለህ መልስ መስጠትህ ጭቅጭቅ ከመፍጠር ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም! ከዚህ ይልቅ እናትህን ሊያረጋጋት የሚችል ሐሳብ
ለምን አትናገርም? ለምሳሌ “እማዬ፣ እንደተናደድሽ ይሰማኛል። በቃ ዕቃውን አሁኑኑ አጥበዋለሁ” ልትል ትችላለህ። ይሁንና አነጋገርህ የሽሙጥ እንዳይመስል ተጠንቀቅ። ስሜቷን እንደተረዳህላት በሚያሳይ መንገድ መናገርህ በመካከላችሁ ሊፈጠር የሚችለውን ውጥረት ሊያረግበው ይችላል።ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ እናትህ ወይም አባትህ ምን ሲሉ እንደሚያበሳጭህ ጻፍ።
․․․․․
አሁን ደግሞ የወላጆችህን ስሜት እንደምትረዳ በሚያሳይ መንገድ እንዴት ብለህ መልስ እንደምትሰጥ አስብ።
․․․․․
○ በአክብሮት ተናገር። ሚሼል እናቷን ተገቢ በሆነ መንገድ ማነጋገሯ ያለውን ጠቀሜታ ከተሞክሮ ተምራለች። ሚሼል “ምንም ልናገር ምን፣ የምናገርበት መንገድ እናቴን ሁልጊዜ እንደሚያበሳጫት ተገነዘብኩ” በማለት ተናግራለች። አንተም ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥምህ ከሆነ ድምፅህን ዝቅ አድርገህ ረጋ ባለ ሁኔታ ተናገር፤ እንዲሁም ዓይንህን አታጉረጥርጥ ወይም እንደተበሳጨህ የሚያሳይ አካላዊ መግለጫ አትጠቀም። (ምሳሌ 30:17) ስሜትህን መቆጣጠር እንደማትችል ከተሰማህ በልብህ ወደ አምላክ አጭር ጸሎት አቅርብ። (ነህምያ 2:4) እርግጥ ነው፣ የአምላክን እርዳታ የምትለምነው ከወላጆችህ ጭቅጭቅ እንድትገላገል ሳይሆን በመካከላችሁ እሳት እንዳይጫር ራስህን መግዛት እንድትችል ነው።—ያዕቆብ 1:26
ከዚህ በታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ልታስወግዳቸው የሚገቡህ አንዳንድ ቃላቶችንና አካላዊ መግለጫዎችን ጻፍ።
ቃላቶች (የምትናገራቸው ነገሮች)፦
․․․․․
አካላዊ መግለጫዎች (በፊትህና በሌሎች የሰውነትህ ክፍሎች የምታሳያቸው እንቅስቃሴዎች)፦
․․․․․
○ አዳምጥ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከብዙ ንግግር ውስጥ ስህተት አይጠፋም” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 10:19 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ እናትህ ወይም አባትህ እንዲናገሩ እድል ስጣቸው፤ እንዲሁም ወላጆችህ ሲናገሩ በትኩረት አዳምጣቸው። ወላጆችህ ሲያናግሩህ የከፈትከው ሙዚቃ ካለ አጥፋ፣ የምታነበውን መጽሐፍ ወይም መጽሔት ዝጋና ዓይን ዓይናቸውን እያየህ አዳምጥ። ሰበብ ለማቅረብ ስትል ንግግራቸውን አታቋርጥ። ዝም ብለህ አዳምጥ። ወላጆችህ ተናግረው ሲጨርሱ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ወይም ሐሳብህን ለመግለጽ በቂ ጊዜ ታገኛለህ። በሌላ በኩል ግን እልኸኛ ሆነህ ሐሳቤን ካልተናገርኩ ካልክ ነገሩን ከማባባስ ውጪ የምትፈይደው የለም። በተጨማሪም መናገር የምትፈልገው ነገር ቢኖር እንኳ ‘ጊዜው የዝምታ’ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ።—መክብብ 3:7
○ ይቅርታ ለመጠየቅ አታመንታ። ለጭቅጭቁ መፈጠር ያደረግከው አስተዋጽኦ ካለ “ይቅርታ አድርጉልኝ” ማለትህ ምንጊዜም ቢሆን ተገቢ ነው። (ሮም 14:19) መንስኤው ምንም ይሁን ምን ለተፈጠረው ጭቅጭቅ ይቅርታ መጠየቅህ ጥሩ ነው። ፊት ለፊት ይቅርታ መጠየቅ ከባድ ከሆነብህ ስሜትህን በጽሑፍ መግለጽ ትችላለህ። ለጭቅጭቅ መንስኤ ሊሆን የሚችል ማንኛውም ባሕርይ በማስወገድ ‘እጥፉን ኪሎ ሜትር ሂድ።’ (ማቴዎስ 5:41) ለምሳሌ ያህል፣ መሥራት ያለብህን የቤት ውስጥ ሥራ ሳትሠራ መቅረትህ ለጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆን ከሆነ ሥራውን በመሥራት ወላጆችህን ለምን አታስደስታቸውም? ሥራውን ባትወደውም እንኳ ባለመሥራትህ ምክንያት ከወላጆችህ ጋር ከመጨቃጨቅ ይልቅ መሥራቱ አይሻልም?—ማቴዎስ 21:28-31
በመጨረሻም የተፈጠረውን ጭቅጭቅ ለመፍታት ወይም ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር መጣርህ ሕይወትህ ውጥረት የሰፈነበት እንዳይሆን ያደርጋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 11:17) ስለዚህ በአንተና በወላጆችህ መካከል ያለውን ውጥረት ለመቀነስ የበኩልህን ማድረግ ምን ያህል እንደሚጠቅምህ አስብ።
በተሳካላቸው ቤተሰቦች ውስጥም እንኳ ጭቅጭቅ ሊፈጠር እንደሚችል እሙን ነው፤ ሆኖም የተፈጠረውን ጭቅጭቅ በሰላማዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ያውቃሉ። በዚህ ርዕሰ ትምህርት ላይ የቀረቡትን ምክሮች ተግባራዊ አድርግ፤ እንዲህ ማድረግህ ከወላጆችህ ጋር በጣም ከባድ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችንም ጭምር ያለ ጭቅጭቅ መወያየት እንደምትችሉ ትመለከታለህ!
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
● ብዙውን ጊዜ ከእኩዮቻችሁ አንዳንዶቹ በመጨቃጨቅ ረገድ ችሎታን ማዳበር ጥሩ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
● ይሖዋ ተጨቃጫቂ የሆነን ሰው እንደ ተላላ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 20:3
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት
“እየሠራሁ ራሴን የምረዳ ቢሆንም የምኖረው ከእናቴ ጋር በመሆኑ እሷን ማዳመጥ እንዳለብኝ መገንዘብ አስፈልጎኛል። ለብዙ ዓመታት እኔን ስትንከባከበኝ ቆይታለች፤ ስለዚህ ሰዓት እላፊን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ስትቆጣጠረኝ ሙሉ በሙሉ ስሜቷን እረዳለሁ።”[5]
“እኔና ወላጆቼ ያልተስማማንበት ጉዳይ ካለ በነገሩ ላይ እንጸልያለን፤ ጉዳዩን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንሞክራለን፤ ከዚያም እንወያይበታለን። በዚህ መንገድ ሁልጊዜም የሚያስማማን ነጥብ ላይ እንደርሳለን። ምንጊዜም በጉዳዩ ላይ የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ ስንጥር ሁልጊዜ ፍጻሜው ያማረ ይሆናል።”[5]
[ሥዕሎች]
ዳንኤል
ካምረን
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መልስ
1. በሽሙጥ መናገሯ (“ጀመረች ደግሞ”) የእናቷን ንዴት ከማባባስ ይልቅ የሚፈይደው ነገር የለም።
2. ሪቸል በፊቷ ላይ የታየው ነገር (ዓይኖቿን ማጉረጥረጧ) የበለጠ ችግር ፈጥሯል።
3. እኩል መመላለስ (“አንቺስ እንዴት ነው የምታናግሪኝ?”) ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት አያመጣም።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ
በዚህ ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተገለጸውን ሁኔታ ተመልከቱ። የሪቸል እናት ካደረገቻቸው ለጭቅጭቁ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹን ለይታችሁ መናገር ትችላላችሁ? በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር የሚፈጠረውን ጭቅጭቅ ማስወገድ የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ልታስቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦
“አንተ ሁልጊዜ . . .” እና “ፈጽሞ . . .” የመሳሰሉ የተጋነኑ አነጋገሮችን አስወግዱ። እንደዚህ ያሉት አነጋገሮች የምትናገሩት ሰው የመከላከያ መልስ እንዲሰጥ ከመጋበዝ ይልቅ የሚፈይዱት ነገር የለም። ደግሞም እንዲህ ያሉ ንግግሮች የተጋነኑ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ልጃችሁም ቢሆን ይህን ያውቃል። የተጋነነ ነገር የተናገራችሁት እናንተ በጣም ስለተናደዳችሁ እንጂ ስህተቱ ያን ያህል የሚያስቆጣ እንዳልሆነም ያውቃል።
“አንተ” በሚሉት ቃላት የሚጀምሩ በልጃችሁ ላይ ያነጣጠሩ አነጋገሮችን ከመጠቀም ይልቅ የልጃችሁ ባሕርይ እናንተን ምን ያህል እንዳሳዘናችሁ ለመግለጽ ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ “. . . ስታደርግ . . . ይሰማኛል” ማለት ትችላላችሁ። ልጃችሁ ልቡ እንዲነካ የሚያደርገው ውስጣዊ ስሜታችሁን ማወቁ እንደሆነ መገንዘባችሁ ጥሩ ነው። በመሆኑም ምን ያህል እንዳሳዘናችሁ ልጃችሁ እንዲያውቅ በማድረግ ከእናንተ ጋር እንዲተባበር ልታደርጉት ትችላላችሁ።
ቀላል ላይሆን ቢችልም፣ ቁጣችሁ እስኪበርድ ድረስ ከመናገር ተቆጠቡ። (ምሳሌ 10:19) የጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆነው የቤት ውስጥ ሥራ ከሆነ ከልጃችሁ ጋር ተወያዩበት። ከእሱ የሚጠበቀው ምን እንደሆነ ለይታችሁ በጽሑፍ አስፍሩ፤ ካስፈለገም የሚጠበቅበትን ነገር ካልፈጸመ የሚደርስበትን ቅጣት ጭምር ግልጽ አድርጉለት። የልጃችሁ አመለካከት ስህተት መስሎ ቢሰማችሁም እንኳ ሲናገር በትዕግሥት አዳምጡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ማድረግ ስላለባቸው ነገር መግለጫ ከሚሰጣቸው ሰው ይልቅ ትኩረት ሰጥቶ ለሚያዳምጣቸው ነው።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ በዓለም ላይ የሚታየው የዓመፀኝነት መንፈስ ተጋብቶበታል ብላችሁ በችኮላ ከመደምደም ይልቅ በልጃችሁ ላይ የምትመለከቱት አብዛኛው ነገር በዚህ ዕድሜ የሚያጋጥም እንደሆነ ተገንዘቡ። ልጃችሁ እያደገ መሆኑን ለማሳየት ሲል ብቻ በአንድ ጉዳይ ላይ ሊከራከር ይችላል። ጭቅጭቅ ውስጥ እንድትገቡ የሚገፋፋችሁን ውስጣዊ ስሜት ተቋቋሙ። የማትስማሙበት ነገር ሲነሳ መልስ የምትሰጡበት መንገድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚገኘው ልጃችሁ ትምህርት እንደሚያስተላልፍለት አስታውሱ። ትዕግሥትና የቻይነት ባሕርይን አዳብሩ፤ እነዚህን ባሕርያት ማሳየታችሁ ለወንድ ወይም ለሴት ልጃችሁ ጥሩ ምሳሌ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል።—ገላትያ 5:22, 23
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከወላጆችህ ጋር መጨቃጨቅ በመሮጫ ማሽን ላይ ከመሮጥ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ያለ የሌለ ኃይልህን ብትጠቀምም የትም አትደርስም