ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
“ከዓለም ሕዝብ መካከል 60 በመቶ የሚሆነው የሞባይል ስልክ [ተጠቃሚ] ነው። . . . ከስድስት ዓመታት በፊት ከ15 በመቶ በታች የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ከነበሩበት ጊዜ አንፃር ሲታይ ይህ በጣም ከፍተኛ ለውጥ ነው።”—ማክሊንስ፣ ካናዳ
ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ታላቁ ሜኮንግ በሚባለው ክልል 1,068 አዳዲስ ዝርያዎች ተገኝተዋል።—ዎርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“አሜሪካ ያላት የሕዝብ ብዛት ከዓለም ሕዝብ ብዛት ጋር ሲወዳደር ከ5 በመቶ ያነሰ ቢሆንም ከሕዝቧ 25 በመቶ የሚያህለው እስረኛ ነው። በአሜሪካ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል 756ቱ እስረኞች ሲሆኑ በዓለም ላይ ከሚታሰሩት ሰዎች አማካይ ቁጥር ጋር ሲወዳደር በአምስት እጥፍ ይበልጣል።”—ዚ ኢኮኖሚስት፣ ብሪታንያ
‘ሐሳብ የሚበታትኑ ነገሮች ከምንጊዜውም በላይ’ ጨምረዋል
የረቀቀ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ አንዳንድ የመገናኛ ዘዴዎች ሰዎች በሌሎች ሥራዎቻቸው ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ሰዎች ከኮምፒውተር ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠኑ ባለሙያዎች ሪፖርት እንዳደረጉት ፈጣን መልእክቶች፣ በኮምፒውተር ቀን መቁጠሪያዎች ላይ የሚሞሉ ማስታወሻዎች፣ የኢ-ሜይል መልእክት መምጣቱን የሚያሳውቁ ምልክቶች፣ ድንገት ብቅ የሚሉ ማስታወቂያዎች ወይም ምስሎችና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች የኮምፒውተር ተጠቃሚዎች “ከምንጊዜውም በላይ ሐሳባቸው እንዲበታተንና በአንድ ነገር ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ማተኮር እንዳይችሉ” አድርገዋል። ኒውስዊክ መጽሔት እንደተናገረው አንድ ሰው ትኩረት የሚበታትኑ ነገሮች ቶሎ ቶሎ የሚያጋጥሙት መሆኑ “በአንድ ሐሳብ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የማተኮር ችሎታውን እንዲያጣ እንዲሁም አንድን ነገር ጀምሮ ቶሎ እንዳይጨርስ ሊያደርገው ይችላል።” በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ የሐሳብ መበታተን ከሚያስከትላቸው ነገሮች መካከል “የማስታወስ ችሎታን ማጣት” እና “ነገሮችን በትክክል የማስታወስ ችሎታ መቀነስ” ብሎም የከፋ ስህተት መፈጸም ይገኙበታል።
አስተርጓሚዎች ያስፈልጋሉ
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች፣ ሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሰዎች የሚናገሩትን ለመረዳት ብዙውን ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የሮይተርስ የዜና ዘገባ “ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች እየጨመሩባት ያለች ዓለም” ብሎ በጠራት በዩናይትድ ስቴትስ፣ ከሰዎች ጋር ለመግባባት በርካታ ድርጅቶች ተርጓሚዎችን እያቀረቡ ነው። ዋና መሥሪያ ቤቱ በካሊፎርኒያ የሚገኝ አንድ ድርጅት 176 ቋንቋዎችን የሚናገሩ 5,200 አስተርጓሚዎችን ቀጥሯል፤ ይህ ደግሞ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ተናጋሪዎች ካሏቸው እንደ ቻይንኛ፣ ሩሲያኛና ስፓንኛ የመሳሰሉትን ቋንቋዎች ጨምሮ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራትና በሜክሲኮ የሚነገሩ እምብዛም የማይታወቁ ቋንቋዎችን ማስተርጎምን ያካትታል። እንዲህ ያሉ ድርጅቶች ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ “ግለሰቡ የሚናገረው ቋንቋ ምን እንደሆነ ለይተው ማወቅ” እና ደንበኞቻቸው “የሚያናግራቸው ሰው” እንዲያገኙ ለመርዳት አስተርጓሚዎችን ማገናኘት እንደሚችሉ ሪፖርቱ ገልጿል።
ወርቅ የሚገኝበት ያልተጠበቀ ቦታ
ከጃፓን የተገኘ የሮይተርስ የዜና ዘገባ፣ ከቶኪዮ በሰሜን ምዕራብ በሚገኘው በናጋኖ ግዛት “አዲስ የማዕድን ሀብት ምንጭ አግኝቷል፤ ይህ ምንጭ የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ነው” በማለት ተናግሯል። ጥናቶች እንዳመለከቱት ሱዋ በምትባለው ከተማ የሚገኘው ፍሳሽን አጣርቶ ጥቅም ላይ የሚያውል ተቋም የፍሳሹን ዝቃጭ ካቃጠለ በኋላ ከሚቀረው አመድ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ አግኝቷል፤ ይህ የወርቅ መጠን ከጃፓን የማዕድን ማውጫዎች ተቆፍሮ ከሚወጣው ወርቅ የበለጠ ነው። የግዛቱ አስተዳዳሪዎች፣ በአንድ የበጀት ዓመት ብቻ እንኳ 15 ሚሊዮን የጃፓን የን ወይም ከ167,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጣ ወርቅ እንደሚያገኙ ይጠብቃሉ። በፍሳሽ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት ሊኖር የቻለው “በአካባቢው ይህን ቢጫ ብረት [ወርቅ] የሚጠቀሙና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን መሣሪያዎች የሚያመርቱ በርካታ ፋብሪካዎች” ስላሉ እንደሆነ ዘገባው ይናገራል።