ፀሐይዋ ቀይ የሆነችበት ጊዜ
ፀሐይዋ ቀይ የሆነችበት ጊዜ
በ1783 ሞቃታማ ወቅት ላይ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የሚገኙ ብዙ አገሮች ለበርካታ ወራት እርጥበት የሌለው ለየት ያለ ጭጋግ ሸፍኗቸው ነበር። ፀሐይዋ ደም መሰለች፣ ዕፅዋት ጠወለጉ እንዲሁም በጣም ብዙ ሰዎች ሞቱ። እንዲያውም ይህ ጭጋግ በፈረንሳይና በእንግሊዝ ብቻ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይገመታል። እንዲሁም ሌሎች በጣም ብዙ ሰዎች በመታመማቸው ገበሬዎች ከአደጋው የተረፈውን ምርታቸውን የሚሰበስብላቸው ሠራተኛ ለማግኘት ተቸግረው ነበር።
ይህ ጭጋግ ‘ባለፈው ሺህ ዓመት በምድርና በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡት እጅግ አስደናቂ ክስተቶች አንዱ’ እንደሆነ ተገልጿል። ይሁን እንጂ በወቅቱ ይህ ጭጋግ የተፈጠረበትን ምክንያት ያወቁት የአይስላንድ ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ይህ ክስተት የተፈጠረው በአይስላንድ በደረሰ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተነሳ ሲሆን ሊቃውንት እንዲህ ያለው ፍንዳታ የሚከሰተው በየተወሰኑ መቶ ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ ክስተት የከፋ ጉዳት የደረሰባት አይስላንድ ስትሆን 20 በመቶ የሚሆኑትን ሕዝቦቿን እንዳጣች ይገመታል።
የላኪ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ
ሰኔ 8, 1783 በደቡባዊ አይስላንድ የሚገኘው የሲዛ አካባቢ ነዋሪዎች ላኪ የተባለው እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶችን አዩ፤ ይህ ፍንዳታ በአሁኑ ጊዜ የላኪ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ (ላኪ ፊሸር ኢረፕሽን) በመባል ይታወቃል። በወቅቱ የተከሰተውን ነገር በበርካታ አገሮች ይኖሩ የነበሩ ተመልካቾች ስለመዘገቡት ተመራማሪዎች እሳተ ገሞራው የፈጠረው ደመና በየቀኑ የተጓዘበትን አቅጣጫ ለማወቅ ችለዋል። በአይስላንድ ከነበሩት የዓይን ምሥክሮቹ አንዱ ዮን ስታይንግሪምሰን ሲሆኑ ከወደ ሰሜን “ጥቁር ዳመና” ሲመጣ እንዳዩ ዘግበዋል። ሰማዩ የጨለመ ሲሆን መሬቱ ደቃቅ በሆነ አመድ ተሸፈነ። ከዚያም የምድር መናወጥና መንቀጥቀጥ ጀመረ። ስታይንግሪምሰን እንደገለጹት ከአንድ ሳምንት በኋላ “ከስካፍታው ሸለቆ የወጣው በጣም ኃይለኛ የሆነ የእሳት ጎርፍ” በመንገዱ ላይ ያገኘውን ሁሉ እየጠራረገ መሄድ ጀመረ። ስታይንግሪምሰን ለስምንት ወራት ያህል የሆነውን ነገር መዝግበዋል።
ኮንቲኔንታል ፍለድ ባሳልት ኢረፕሽን ተብሎ በተጠራው በዚህ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በመሬት የላይኛው ክፍል ላይ በተከሰተው 25 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ስንጥቅ በኩል 15 ኪሎ ሜትር ኩብ የሚሆን የቀለጠ ድንጋይ ገንፍሎ የወጣ ሲሆን ይህም እስከዛሬ ከተመዘገቡት ሁሉ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም! እሳተ ገሞራው የተፋው የቀለጠ ዐለት በመቶ የሚቆጠሩ ሜትሮች ወደ ሰማይ የተረጨ ሲሆን ከስንጥቁ የወጣው የቀለጠ ድንጋይ ደግሞ እስከ 80 ኪሎ ሜትር ድረስ ርቆ በመፍሰስ 580 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ አልብሷል፤ እንዲሁም የስካፍታ ወንዝ የሚሄድበትን ሸለቆ ሞላው።
ከዚያ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የአይስላንድን የሣር መስክ የሸፈነው አመድና መርዛማ ኬሚካል 50 በመቶ የሚሆኑትን ከብቶች እንዲሁም 80 በመቶ የሚሆኑትን ፈረሶችና በጎች ፈጃቸው። ረሃብ በእጅጉ ተስፋፋ። በተጨማሪም የላኪ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ 122 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ከከባቢ አየር ጋር እንዲቀላቀል ያደረገ ሲሆን ይህም በከባቢ አየር ውስጥ ይገኝ ከነበረው ተን ጋር ተዋህዶ 200 ሚሊዮን ቶን የሚሆን አሲድ የቀላቀለ እርጥበት አዘል ብናኝ እንዲፈጠር አድርጓል። *
ራቅ ባሉ አካባቢዎች ያስከተለው ጉዳት
መርዛማ የሆነው አየር በነፋስ እየተነዳ ራቅ ብለው ወደሚገኙ አካባቢዎች ተዳረሰ። በብሪታንያና በፈረንሳይ የሚኖሩ ሰዎች በሕይወታቸው አይተው የማያውቁት “ለየት ያለ ጭጋግ ወይም ጉም” እንደተመለከቱ ተናግረዋል። መጥፎ ጠረን ያለውና ድኝ የያዘው ይህ ጭጋግ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ በሽታዎች፣ ተቅማጥ፣ ራስ ምታት፣ የዓይንና የጉሮሮ ሕመም እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል። ጥቅጥቅ ያለው የሰልፈር
ዳይኦክሳይድና የሰልፈሪክ አሲድ ደመና ወጣት አረጋዊ ሳይል የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።ከጀርመን የተገኘ አንድ ሪፖርት እንደገለጸው መርዛማው ጭጋግ በኤምስ ወንዝ ዳርቻዎች የነበሩትን ዛፎች ቅጠሎች በሙሉ በአንድ ሌሊት አደረቃቸው። በእንግሊዝ ደግሞ አትክልቶችና ቅጠላ ቅጠሎች በእሳት የተለበለቡ ያህል ጠወለጉ። በሃንጋሪ፣ በሩማኒያ፣ በስሎቫክያ፣ በስካንዲኔቪያ፣ በኔዘርላንድስ፣ በጣሊያንና በፈረንሳይም ተመሳሳይ ነገር እንደተፈጸመ ሪፖርት ተደርጓል። እንዲያውም ኬሚካል ያዘለው ይህ ጭጋግ እስከ ፖርቹጋል፣ ቱኒዝያ፣ ሶርያ፣ ሩሲያ፣ ምዕራባዊ ቻይና እና ኒውፋውንድላንድ ድረስ ታይቷል።
ከመጠን በላይ የተበከለው ከባቢ አየር የፀሐይን ጨረር ስለከለለው የአንዳንድ አካባቢዎች ሙቀትም ቀንሶ እንደነበረ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች አሉ። በ1784 በአውሮፓ አህጉር ሙቀቱ በ18ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ወዲህ በነበሩት ዓመታት ከታየው አማካይ የሙቀት መጠን በ2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ያህል ቀንሶ ነበር። በአይስላንድ ደግሞ የሙቀቱ መጠን 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ያህል ቀንሶ ነበር። በሰሜን አሜሪካ በ1783/1784 ቀዝቃዛ ወቅት አየሩ እጅግ ቀዝቅዞ ስለነበር “ከሚሲሲፒ ወንዝ አንስቶ . . . እስከ ሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ድረስ የበረዶ ግግሮች ተንሳፈው” ይታዩ ነበር።
አንዳንድ ምሑራን፣ በሰሜናዊ ምዕራብ አላስካ ይኖሩ የነበሩት ካውራክ የሚባሉ የኢንዊት ጎሳ ሕዝቦች ለመጥፋት የተቃረቡት በላኪ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት በተከሰተው ረሃብ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። በ1783 የሞቃት ወቅት በአላስካ የነበረው ቅዝቃዜ ከዚያ በፊት በነበሩት 400 ዓመታት ውስጥ ከታየው የቅዝቃዜ መጠን ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ እንደነበር በዛፎች ግንድ ላይ ከሚገኙ ክበቦች የተወሰደው ማስረጃ ያመለክታል። የካውራክ ሕዝቦችም ቢሆኑ ሞቃቱ ወቅት በሰኔ ወር አብቅቶ በጣም ከፍተኛ ቅዝቃዜና ረሃብ የተከተለበት አንድ ዓመት እንደነበር የሚገልጽ አፈ ታሪክ አላቸው።
የላኪ እሳተ ገሞራና ዘመናዊው ዓለም
በ1783 የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ከረጅም ዘመን በፊት የደረሰ በመሆኑ እንዲሁም ጉዳቱ የደረሰባቸው አብዛኞቹ ሰዎች ምክንያቱ ምን እንደነበረ ባለማወቃቸው በአሁኑ ወቅት ጨርሶ ተረስቷል ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በአይስላንድ የላኪ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ታላቅ የተፈጥሮ እልቂት በመሆኑ ይታወሳል።
አንዳንዶች አደጋው መለኮታዊ ቅጣት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን አመለካከት አይደግፍም። (ያዕቆብ 1:13) አምላክ ‘መንገዱ ሁሉ ትክክል’ ወይም ፍትሐዊ በመሆኑ ጥሩ ሰዎችንና ክፉዎችን በጅምላ አያጠፋም። (ዘዳግም 32:4) ወደፊት አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ ፍትሑ አስደናቂ በሆነ መንገድ ይታያል። የአምላክ ዓላማ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ ለሰው ልጆች ሞትና መከራ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ማስወገድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ዛሬም የአሲድ ዝናብ የሚያስከትል አደገኛ ጋዝ ነው። ይህ ጋዝ የሚፈጠረው እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ጋዝና ድፍድፍ ዘይት የመሰሉት ነዳጆች ሲቃጠሉ ነው።
[በገጽ 14,15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የላኪ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተከሰተበት አካባቢ ከአየር ሲታይ
[በገጽ 14,15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ እሳት የሚያበራ የቀለጠ ድንጋይ ወደ ላይ ሲረጭ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አይስላንድ በሳተላይት ስትታይ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Lava fountain: © Tom Pfeiffer; aerial photo: U.S. Geological Survey; satellite photo: Jacques Descloitres, MODIS Rapid Response Team, NASA/GSFC