ታንኳ የካናዳ “ተስማሚ ተሽከርካሪ”
ታንኳ የካናዳ “ተስማሚ ተሽከርካሪ”
ሳሙኤል ዲ ሾምፕላ የተባለው ፈረንሳዊ አገር አሳሽ አትላንቲክ ውቅያኖስን ካቋረጠ በኋላ ዛሬ ካናዳ ተብሎ በሚታወቀው አገር እስከሚገኘው እስከ ሴይንት ሎረንስ ወንዝ ድረስ በመርከብ ተጓዘ። ብዙም ሳይጓዝ ግን ሞንትሪያል ሲደርስ ትልቅ እንቅፋት አጋጠመው፤ ለሺን አካባቢ ቁልቁል የሚጋልበው ወንዝ አላስኬድ አለው። በጀልባዎቹ ተጠቅሞ ይህን የወንዙን ክፍል ለመሻገር ያደረገው ማንኛውም ጥረት ከንቱ እንደሆነበት በ1603 በጻፈው ማስታወሻ ላይ ገልጿል። አካባቢው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ በመሆኑ በእግር መጓዝም የማይሞከር ነበር። ታዲያ ሾምፕላና አብረውት የነበሩት ሰዎች ጉዟቸውን እንዴት ቀጠሉ?
የአገሬውን ሰዎች ፈለግ በመከተል በታንኳዎች ተጠቀሙ። “ታንኳዎች በመላው አገሪቱ በሚገኙት ትናንሽም ሆነ ትላልቅ ወንዞች ላይ እንደልብ ለመጓዝ አመቺ ከመሆናቸውም ሌላ ፈጣን ናቸው” ሲል ሾምፕላ ጽፏል።
“ተስማሚ ተሽከርካሪ”
የካናዳ ሐይቆችና ወንዞች ከአውራ ጎዳናዎች ጋር የሚመሳሰሉ ሲሆን ታንኳ ደግሞ ለእነዚህ መንገዶች ተስማሚ ተሽከርካሪ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የአገሬው ተወላጅ የሆኑ የአሜሪካን ሕንዶች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር፣ ለማደንና ዕቃዎችን ለማጓጓዝ በታንኳ ይጠቀማሉ። የታንኳ ንድፍና አሠራር እንደ አገልግሎቱና በአካባቢው እንደሚገኘው ጥሬ ዕቃ ዓይነት ይለያያል። ለምሳሌ በካናዳ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች ግዙፍ ከሆነ ቀይ የጥድ ዝርያ የተፈለፈለ ታንኳ ይሠራሉ። በተፈለፈለው ግንድ ውስጥ ውኃና ትኩስ ድንጋዮች ይጨመራል፤ ይህ ደግሞ ውስጡ እንዲለሰልስ ስለሚያደርግ
በቀላሉ ትክክለኛውን ቅርጽ ለማስያዝ ያስችላል። በዚህ መንገድ ከተሠሩት ታንኳዎች መካከል አንዳንዶቹ እስከ ሃያ ኩንታል መሸከም የሚችሉ ሲሆን ፈጣንና አስተማማኝ ናቸው፤ እንደ ዓሣ ነባሪ ያሉትን ግዙፍ የባሕር እንስሳት እንኳ ለማደን ያገለግሉ ነበር።ከሰሜን አሜሪካ ታንኳዎች በሙሉ እጅግ ዝነኛ የሆነው በርች ከሚባለው ዛፍ ቅርፊት የሚሠራው ታንኳ ሳይሆን አይቀርም። የበርች ቅርፊት ቤቱሊኖል የሚባል ንጥረ ነገር ስላለው ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ከመሆኑም በላይ ውኃ አያስገባም። በተጨማሪም እንደልብ የሚታዘዝና እጅግ ጠንካራ ነው። ዴቪድ ጊድማርክ የተባሉ ታንኳ ሠሪ “ከበርች ቅርፊት የተሠራ ታንኳ ከእንጨትና ከሸራ የተሠሩ ታንኳዎችን ሊሰባብሩ የሚችሉ ኃይለኛ ወንዞችን ማቋረጥ ይችላል” ብለዋል።
የበርች ቅርፊት ታንኳ ለመሥራት ከሚያገለግሉት ጥሬ ዕቃዎች መካከል የበርች ዛፍ እንጨት፣ የጥድ ዝርያ የሆነ ዛፍ እንጨት፣ የስፕሩስ ሥርና የዛፍ ሙጫ ይገኙበታል። እነዚህ ጥሬ ዕቃዎች በሙሉ እዚያው ጫካ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ታንኳዎችን በቀላሉ መጠገን ይቻላል። ከዚህም በላይ በዚህ መንገድ የተሠሩት ታንኳዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል በመሆናቸው በፍጥነት የሚንደረደሩ ኃይለኛ ወንዞችና ሌሎች እንቅፋቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ታንኳዎቹን ተሸክሞ ማለፍ ይቻላል። በተጨማሪም እነዚህ ታንኳዎች አካባቢውን አይበክሉም። አንድ ታንኳ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ በሚጣልበት ጊዜ እንደወደቀ ዛፍ በስብሶ አፈር ይሆናል።
የአሠራሩ ዘዴ የሚያስደንቅ ነው። በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረ አንድ ታዛቢ እንደዘገበው የአገሬው ሰዎች “ሚስማርም ሆነ ብሎን አይጠቀሙም፤ ሁሉንም ነገር የሚያያይዙት በመስፋትና አንድ ላይ በማሰር ነው። . . . ስፌቶቹና ቋጠሮዎቹ የተስተካከሉ፣ በደንብ የጠበቁና የሚያምሩ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ማሻሻያ አያስፈልጋቸውም።”
የባቡር መጓጓዣ ከመጀመሩ በፊት በአብዛኞቹ የካናዳ ክፍሎች ታንኳ ፈጣንና አስተማማኝ መጓጓዣ ሆኖ ያገለግል ነበር። ባቡር ከጀመረ በኋላም ቢሆን ሰዎች በባቡርና በታንኳ ይጓዙ ስለነበር በታንኳ መጠቀም ወዲያው አልቀረም።
ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት የሰሜን አሜሪካ ነዋሪዎች ታንኳ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ክፍል ስለነበር በባሕላቸውና በእምነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ከታላቁ የውኃ መጥለቅለቅ ሊተርፉ የቻሉት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በመርከብ ሳይሆን በታንኳዎች እንደሆነ የሚገልጹ አንዳንድ አፈ ታሪኮች አሉ።
የታንኳ አገልግሎት በዘመናችን
ዛሬም ቢሆን በካናዳ በመዝናኛነት ይሁን እንጂ በታንኳ መጓዝ በጣም የተለመደ ነው። የሚያሳዝነው ግን የበርች ቅርፊት ታንኳዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ዛፎች እየተመናመኑ መጥተዋል። ያም ቢሆን እንደ አሉሚኒየም፣ ሸራ፣ እንጨትና ፋይበርግላስ የመሳሰሉትን ታንኳ ለመሥራት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
ስለ ታንኳ የሚያወሱ መጻሕፍትንና ፊልሞችን በመሥራት የታወቁት ቢል ሜሰን በታንኳ መጓዝ ያለውን ሌላ ጥቅም ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥንታዊ ወንዞች ላይ በታንኳ መጓዝ፣ ከተፈጥሮ እንዲሁም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከረጅም ዘመናት በፊት አቀናብሮ ካስቀመጠው ፈጣሪ ጋር የነበረንን ዝምድና ለማደስ ያስችለናል።” ብዙዎች በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ!
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ካያክ
ኢኑዊት የሚባሉት ሕዝቦች የሚኖሩት ደን አልባ በሆነ የካናዳ ክፍል ነው። ይሁን እንጂ እንጨት ማጣታቸው የውኃ ላይ መጓጓዣ እንዳይሠሩ አላገዳቸውም። የኢኑዊት ሕዝቦች የአቆስጣንና ካሪቡ የተባለውን የአጋዘን ዝርያ ቆዳ እንዲሁም አጥንቶችንና ወደ አርክቲክ የባሕር ዳርቻ በባሕሩ ላይ ተንሳፍፈው የመጡ እንጨቶችን በጥሬ ዕቃነት ይጠቀማሉ። ታንኳዎቹ ውኃ እንዳያስገቡ የእንስሳት ስብ ይቀቧቸዋል። በዚህ ዓይነት የተሠራው ታንኳ ካያክ ተብሎ ይጠራል።
በተራው ታንኳና በካያክ መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነት ካያክ፣ በተወሰነ መጠን ከዝናብና ከነፋስ የሚከልልና በሚገለበጥበት ጊዜ ብዙ ውኃ እንዳያስገባ የሚያደርግ መሸፈኛ ያለው መሆኑ ነው። ዘመናዊው ካያክ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው ከፋይበርግላስና ከሌሎች ሰው ሠራሽ ጥሬ ዕቃዎች ነው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Library of Congress