የስፔን ፍርድ ቤት አንዲት እናት ልጆቿን እንድታሳድግ ወሰነላት
የስፔን ፍርድ ቤት አንዲት እናት ልጆቿን እንድታሳድግ ወሰነላት
● የወላጅነት ብቃታችሁ ጥያቄ ውስጥ ቢገባ ምን ይሰማችሁ ነበር? አንድ ሰው በልጆቻችሁ ላይ ባሳደራችሁት ተጽዕኖ የተነሳ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታቸው እንደቀነሰ፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን መለየት እንደማይችሉና የማሰብ ችሎታቸው እንዳልዳበረ ቢናገር ምን ይሰማችኋል?
በስፔን የምትኖረው የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሮሳ ሎፔስ የቀድሞ ባሏ ልጆቻቸውን የማሳደግ ሕጋዊ መብት ለማግኘት እርምጃ በወሰደ ጊዜ እንዲህ የሚል ክስ መሥርቶባት ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ሮሳ የቀድሞ ባሏ በእሷ ሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት ልጆቹ ማኅበራዊ ሕይወታቸው እንደተቃወሰ፣ የትምህርት ችሎታቸው እንደቀነሰና የሥነ ምግባር አቋማቸው እንደተዛባ ተከራክሮ ነበር። የአካባቢው ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ ሲያደርግበት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ።
ፍርድ ቤት ልጅ ከማሳደግ መብት ጋር በተያያዘ ክርክር ሲነሳ ጉዳዩን ከአድሎ ነፃ በሆነ መንገድ ለማየት ጥረት ያደርጋል፤ አንድ ሰው ፍርድ ቤት የቀረበው በእምነቱ ምክንያት እንደሆነ በሚያስመስል ሃይማኖታዊ ክርክር ውስጥ ጣልቃ አይገባም። ከዚህ ይልቅ የሚከተሉትን ጉዳዮች ይመረምራል፦ ልጁን ይበልጥ የሚጠቅመው የትኛው ነው? አሁን ልጁን በማሳደግ ላይ ያለው ወላጅ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በሆነ መንገድ ልጁ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አለ? ልጁ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት የተሻለ ብቃት ያለው የትኛው ወላጅ ነው?
ፍርድ ቤቱ ከሮሳ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ለልጆቹና ለወላጆቹ ቃለ መጠይቅ የምታደርግ አንዲት የሥነ ልቦና ባለሙያ መደበ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ልጆቹ ለስድስት ዓመታት ያህል ከእናታቸው ጋር የነበሩ ቢሆንም በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ማለትም በትምህርት፣ በማኅበራዊ ኑሮና በቤተሰብ ረገድ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ አረጋግጣለች። ዳኛው፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ባቀረበችው የምርመራ ውጤት እንዲሁም ወላጆቹ በሰጡት የምሥክርነት ቃል ላይ ተመሥርተው “ልጆቹ በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ውስጥ በማደጋቸው ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ ማለትም በስሜታዊም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወታቸው እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆነባቸው ጎጂ ነገር” እንዳለ የሚጠቁም ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ ገልጸዋል። በተጨማሪም ዳኛው የሮሳ የቀድሞ ባል የሰነዘረውን ክስ “ግብታዊነት የተንጸባረቀበትና መሠረት የሌለው” በማለት ውድቅ አድርገውበታል።
አንዳንድ ሰዎች፣ በሃይማኖታዊ ጥላቻ ወይም በተሳሳተ መረጃ የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸውን “በተገቢው” መንገድ እንደማያሳድጓቸው ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት የሚያድጉ ልጆች በደል አይደርስባቸውም። ከዚህ ይልቅ ሚዛናዊና አሳቢ እንዲሆኑ ብሎም በተለያዩ የሕይወታቸው ዘርፎች የሚጠቅማቸውን እውቀት እንዲቀስሙ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።—ኤፌሶን 6:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15-17
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮሳ ሎፔስ ሁለት ሴት ልጆቿን የማሳደግ ሕጋዊ መብቷ ተከበረላት