ሌሎች ከባድ የመሬት ነውጦች እንደሚከሰቱ ይጠበቃል
ሌሎች ከባድ የመሬት ነውጦች እንደሚከሰቱ ይጠበቃል
የመሬት ነውጦችን መጠን ለመለካት የሚረዱ መሣሪያዎች ከተፈለሰፉ ወዲህ የሳይንስ ሊቃውንት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ከባባድ ርዕደ መሬቶችን መዝግበዋል። ሰው ከሚኖርባቸው አካባቢዎች ርቀው በሚገኙ ስፍራዎች የሚደርሱ የመሬት ነውጦች እምብዛም አሳሳቢ ስላልሆኑ በመገናኛ ብዙኃን ያን ያህል ሰፊ የዜና ሽፋን አይሰጣቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የመሬት ነውጥ አንድን ትልቅ ከተማ ከመታ ውድመቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጥፋት በሕዝቡ ብዛትና ሕዝቡ እንዲህ ዓይነቱን አደጋ ለመቋቋም ባለው ዝግጁነት ላይ የተመካ ነው።
ጥር 12, 2010 በሄይቲ የተከሰተው ርዕደ መሬት፣ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከደረሰው ጥፋት አንጻር ሲታይ በታሪክ ዘመናት ከተመዘገቡት አስከፊ የመሬት ነውጦች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ በሄይቲ የደረሰው ርዕደ መሬት ለዚህ ዓመት የመጀመሪያውም ሆነ በኃይለኝነቱ ብቸኛው የመሬት ነውጥ አይደለም። የሄይቲን ዋና ከተማ ካወደመው የማይተናነስ ወይም የሚበልጥ ኃይል እንዳላቸው ከተመዘገቡት በ2010 በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ከተከሰቱት ነውጦች ውስጥ አንዳንዶቹ ቀጥሎ ቀርበዋል።
ጥር 3፦ 7.1 የደረሰ ነውጥ፣ የሰለሞን ደሴቶች
መጀመሪያ ላይ በሬክተር ስኬል ሲለካ ከ7.1 ይበልጥ የነበረው ይህ ታላቅ የመሬት ነውጥ “የውኃው ከፍታ ከ6 እስከ 10 ጫማ (ከ2-3 ሜትር) የሚደርስ” ሱናሚ አስከትሏል። የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ የሆኑት ሎቲ ዬትስ ከአውሮፕላን ላይ ሆኖ ሲታይ አካባቢው “ሙሉ በሙሉ በውኃ ተጥለቅልቆ ነበር” በማለት ተናግረዋል። እኚህ ባለሥልጣን እንደገለጹት ከሆነ በሬንዶቫ ደሴት ላይ ባለችው የባይናራ መንደር 16 ቤቶች ከጥቅም ውጪ ሲሆኑ ሌሎች ብዙ ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከዚህ የመሬት ነውጥ ቀደም ብሎ 6.6 የደረሰ አነስተኛ ነውጥ ተከስቶ ነበር። ብዙ ሰዎች አነስተኛ ኃይል ያለው ይህ ነውጥ ከተከሰተ በኋላ ስጋት ስላደረባቸው ወደ ኮረብታዎች ሸሽተው ነበር። እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰዳቸው ሁለት ሰዓት ቆይቶ በተከሰተው ከባድ የመሬት ነውጥ ሳቢያ የተነሳው ሱናሚ የሚኖሩበትን የባሕር ዳርቻ ሲመታ ለመትረፍ አብቅቷቸዋል።
የካቲት 26፦ 7.0 የደረሰ ነውጥ፣ የሪዩኪዩ ደሴቶች፣ ጃፓን
ይህ የመሬት ነውጥ የተከሰተው ከሌሊቱ 11:31 ላይ ሲሆን መነሻውም ከጃፓን የሪዩኪዩ ደሴቶች አንዷ ከሆነችው በኦኪናዋ የምትገኘው ናሀ ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ቦታ ነው። ሱናሚ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ማስጠንቀቂያው ተሻረ። በኦኪናዋ ከ90 ዓመት በላይ የኖሩ አንዲት አረጋዊት ይህ ነውጥ ከዚህ በፊት ከደረሱት ሁሉ እጅግ ኃይለኛው እንደሆነ ተናግረዋል።
የካቲት 27፦ 8.8 የደረሰ ነውጥ፣ ቺሊ
ይህ የመሬት ነውጥ ከ1900 ወዲህ ከደረሱት ውስጥ በኃይለኛነቱ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው። ከሁሉ የሚበልጠው እጅግ ኃይለኛ የመሬት ነውጥም የተከሰተው በ1960 በቺሊ ሲሆን መጠኑ በሬክተር ስኬል 9.4 ነበር። ይህ የመሬት ነውጥ ብሎም በ1985 የቺሊን ዋና ከተማ ያወደመውና በሬክተር ስኬል 7.7 የደረሰው የመሬት ነውጥ አገሪቱ ጥብቅ የግንባታ ሕጎችን እንድትከተል አስገድደዋታል።
በመሆኑም በዚህ ዓመት በተከሰተው የመሬት ነውጥ ሳቢያ በሳንቲያጎም ሆነ በሌሎች ከተማዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሕንፃዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ይሁን እንጂ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ከመሆኑም ሌላ ሀብት ንብረታቸውን አጥተዋል። ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የሚታመን ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት የሞቱት በቺሊ የባሕር ዳርቻ ላይ በደረሰው ሱናሚ ምክንያት ነው።
ሚያዝያ 4፦ 7.2 የደረሰ ነውጥ፣ ባጃ ካሊፎርኒያ፣ ሜክሲኮ
ይህ ነውጥ የተነሳው በሜክሲኮ ከምትገኘው ጓደሎፕ ቪክቶሪያ 18 ኪሎ ሜትር፣ ከሜክሲካሊ ደግሞ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። አካባቢው በጣም ርቆ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ አብዛኛው ክፍል ሰው የማይኖርበት ነው። ይሁን እንጂ በሜክሲኮና በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ባሉት በርካታ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች ውስጥ መንቀጥቀጡ በደንብ ተሰምቷል።
ግንቦት 9፦ 7.2 የደረሰ ነውጥ፣ ሰሜን ሱማትራ፣ ኢንዶኔዥያ
ይህ የባሕር ውስጥ የመሬት ነውጥ የተከሰተው በኢንዶኔዥያ ሰሜናዊ ጫፍ ከምትገኘው ባንዳ አቼ ከተማ 217 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን ጊዜውም እኩለ ቀን ነበር። ብዙ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው የሸሹ ከመሆኑም በላይ ነውጡ ዳግመኛ እንደሚከሰት በመፍራት ወደቤታቸው ለመመለስ ለተወሰነ ጊዜ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁን እንጂ የሰው ሕይወት መጥፋቱን የሚገልጽ ሪፖርት አልቀረበም።
ተጨማሪ ነውጦች እንደሚከሰቱ ይጠበቃል
ፕላኔታችንን የናጧት ከባባድ የመሬት ነውጦች ካስመዘገቡት ረዥም ታሪክ አንጻር ሲታይ በመጪዎቹ ዓመታትም ሌሎች የመሬት ነውጦች እንደሚከሰቱ መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም “ከዚህ በፊት ከባባድ የመሬት ነውጦች እንደደረሱ ሁሉ ወደፊትም መከሰታቸውን ይቀጥላሉ” በማለት እቅጩን ተናግሯል።
አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ እንደሚከተለው በማለት የሰጠው አስተያየት ትኩረት የሚስብ ነው፦ “በቅርቡ የተከሰቱት ሁሉም የመሬት ነውጦች ከሰው ልጆች አቅም በላይ ናቸው፤ እነዚህ ነውጦች የሚያስገነዝቡን ነገር ቢኖር ሰው ደካማ መሆኑን ብቻ ነው። እንዲህ ሲባል . . . በእኛ አቅም ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገሮችን በቸልታ እናልፋለን ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደፊትም ከቁጥጥራችን በላይ የሆኑ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚከሰቱ መጠበቅ ይኖርብናል ማለት ነው።”
ይህ ሁኔታ፣ ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ መድረሱን ከሚጠቁሙት የምልክቱ ገጽታዎች መካከል አንዱ የመሬት ነውጥ እንደሆነ ለይተው የሚጠቅሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል።—ማቴዎስ 24:3, 7፤ ማርቆስ 13:8፤ ሉቃስ 21:11
[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከጥር እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ቢያንስ በሬክተር ስኬል 7.0 የደረሰ የመሬት ነውጥ ከተከሰተባቸው ቦታዎች መካከል ጥቂቶቹ
ሜክሲኮ
ሄይቲ
ቺሊ
ጃፓን
ኢንዶኔዥያ
የሰለሞን ደሴቶች