በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ ሆኖብኛል?
የወጣቶች ጥያቄ
በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ ሆኖብኛል?
እነዚህን ሦስት ወጣቶች የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
“መልእክት መጻጻፍ በጣም በጣም እወዳለሁ! ከምንም ነገር የበለጠ እንደሆነ ይሰማኛል። መላ ሕይወቴን ተቆጣጥሮታል ማለት ትችላላችሁ።”—አለን *
“እናቴ ለመኝታ ክፍሌ ቴሌቪዥን ስትገዛልኝ በጣም ፈነደቅኩ! ማታ ማታ ቶሎ ከመተኛት ይልቅ ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን እያየሁ አመሽ ነበር። ከቤተሰቤና ከጓደኞቼ ጋር ከመሆን ይልቅ ቴሌቪዥን ማየት እመርጥ ነበር።”—ቴሬሳ
“በድረ ገጼ ላይ መልእክት ተቀምጦልኝ እንደሆነ ሳላይ የትም ቦታ መሄድም ሆነ ምንም ነገር ማድረግ አልችልም ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ ከእንቅልፌ ብነቃ እንኳ ኢንተርኔት እከፍታለሁ። የሆነ አጋጣሚ ሳገኝ፣ በከፈትኩት ብሎግ ላይ የዕለት ውሎዬን አሰፍራለሁ።”—አና
በአንተ አመለካከት ከእነዚህ ሦስት ወጣቶች መካከል በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የመጠቀም ሱስ ያለበት ማን ነው?
□ አለን □ ቴሬሳ □ አና
ወላጆችህ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳሉ በስፋት የሚታወቁት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ነበሩ። በዘመኑ የነበሩት ስልኮች የድምፅ መልእክት ከማስተላለፍ ያለፈ አገልግሎት አልነበራቸውም፤ ምናልባትም እነዚህን ስልኮች ከተቀመጡበት ቦታ እንደ ልብ ማንቀሳቀስ አይቻል ይሆናል። እንዲህ ያለው ስልክ ኋላቀር ነው አይደል? አና የተባለች አንዲት ወጣት እንደዚያ ይሰማታል። “ወላጆቼ ያደጉት ቴክኖሎጂ ባልረቀቀበት የጨለማ ዘመን ውስጥ ነው” ብላለች። “ሞባይል ስልኮቻቸውን በተሟላ መንገድ ለመጠቀም ገና እየታገሉ ነው!”
በአሁኑ ጊዜ በኪስህ ውስጥ ልትይዛት በምትችል ሞባይል አማካኝነት ስልክ ልትደውል፣ ሙዚቃ ልታዳምጥ፣ ፊልም ልታይ፣ ጌም ልትጫወት፣ ለጓደኞችህ ኢሜይል ልትልክ፣ ፎቶ ልታነሳና ኢንተርኔት ልትጠቀም ትችላለህ። ኮምፒውተር፣ ሞባይል፣ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት እየተጠቀምክ ስላደግክ ‘በእነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ ብጠቀም ምን ችግር ይኖረዋል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ወላጆችህ ግን የእነዚህ ነገሮች ሱሰኛ እንደሆንክ ይሰማቸው ይሆናል። በዚህ ረገድ ስጋታቸውን ከገለጹልህ ትክክል እንዳልሆኑ ተሰምቶህ አስተያየታቸውን ችላ አትበል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነት . . . ይሆንበታል” ብሏል።—ምሳሌ 18:13
ወላጆችህ ያለህበት ሁኔታ የሚያሳስባቸው ለምን እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? በአንዳንድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መጠቀም ሱስ ሆኖብህ እንደሆነ ለማወቅ ከዚህ ቀጥሎ በቀረቡት ሐሳቦች አማካኝነት ራስህን ፈትሽ።
‘ሱሰኛ ሆኛለሁ?’
አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ ሱስ የሚለው ቃል “አንድ ሰው ጉዳት የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ማቆም ያቃተውን ወይም ለማቆም የማይፈልገውን ሥር የሰደደ ልማድ” እንደሚያመለክት
ገልጿል። ከዚህ ፍቺ አንጻር በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሦስት ወጣቶች ለኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሱሰኛ ናቸው ወይም ነበሩ ማለት ይቻላል። አንተስ? እስቲ ከላይ የተገለጸውን ፍቺ ከፋፍለን እንየው። አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን አስተያየት አንብብና አንተም ተመሳሳይ ነገር ተናግረህ ወይም አድርገህ እንደሆነ ለማወቅ ራስህን ገምግም። ከዚያም በክፍት ቦታው ላይ መልስህን ጻፍ።ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ልማድ። “የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በመጫወት ብዙ ሰዓት አጠፋ ነበር። ጌሞቹ የእንቅልፍ ሰዓቴን የሚሻሙብኝ ከመሆኑም ሌላ ያለ እነሱ ወሬ አልነበረኝም። ራሴን ከቤተሰቦቼ አግልዬ የነበረ ሲሆን የምጫወታቸው ጌሞች በፈጠሩት ምናባዊ ዓለም እመሰጥ ነበር።”—አንድሩ
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም በየቀኑ ምን ያህል ሰዓት ማሳለፍ ምክንያታዊ ይመስልሃል? ․․․․․
ወላጆችህስ ምን ያህል ሰዓት ማሳለፍ እንዳለብህ ይሰማቸዋል? ․․․․․
የጽሑፍ መልእክት በመላላክ፣ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ፎቶዎችንና አንዳንድ ሐሳቦችን ድረ ገጽ ላይ በማስቀመጥ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በመጫወትና በመሳሰሉት ነገሮች በየቀኑ በአጠቃላይ ምን ያህል ሰዓት ታሳልፋለህ? ․․․․․
ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ከሰጠኸው መልስ አንጻር የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም የምታሳልፈው ጊዜ ከመጠን በላይ እንደሆነ ይሰማሃል?
□ አዎ ❑ አይ
ማቆም አለመቻል ወይም ፈቃደኛ አለመሆን። “ወላጆቼ ሁልጊዜ የጽሑፍ መልእክት ስላላክ ስለሚመለከቱኝ በጣም እንዳበዛሁት ይነግሩኛል። በእኔ ዕድሜ ካሉ ልጆች ጋር ሲነጻጸር ግን እኔ ምንም አልክም ማለት ይቻላል። እርግጥ ከወላጆቼ አንጻር ከታየ የእኔ ይበልጣል። ግን እኮ እኔንና ወላጆቼን ማወዳደር ፖምን ከብርቱካን ጋር ከማወዳደር ተለይቶ አይታይም። እነሱ 40 እኔ ደግሞ ገና 15።”—አለን
ወላጆችህ ወይም ጓደኞችህ አንዳንድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ብዙ ጊዜ እንደምታሳልፍ ነግረውህ ያውቃሉ?
□ አዎ □ አይ
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በመጠቀም የምታሳልፈውን ጊዜ ለመቀነስ ፈቃደኛ አይደለህም ወይም አቅቶሃል?
□ አዎ □ አይ
አስከፊ መዘዝ። “ጓደኞቼ ሁልጊዜ ሌላው ቀርቶ መኪና እየነዱ እንኳ የጽሑፍ መልእክት ይልካሉ። ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው!”—ጁሊ
“ሞባይል መያዝ የጀመርኩ ሰሞን በጣም እደውል ወይም የጽሑፍ መልእክት እልክ ነበር። ያለዚህ ሥራ አልነበረኝም። ከቤተሰቤ እንዲያውም ከአንዳንድ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አበላሽቶብኛል። ከጓደኞቼ ጋር እያወራሁ እያለ ብዙ ጊዜ ጨዋታችንን አቋርጠው ‘ቆይ አንድ ጊዜ፤ ለዚህ መልእክት መልስ መጻፍ አለብኝ’ ሲሉኝ አንድ ነገር አስተዋልኩ። ከእነዚህ ጓደኞቼ ጋር በጣም ያልተቀራረብኩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።”—ሸርሊ
መኪና እየነዳህ አሊያም ክፍል ውስጥ ሆነህ የጽሑፍ መልእክት አንብበህ ወይም ልከህ ታውቃለህ?
□ አዎ □ አይ
ከወላጆችህ ወይም ከጓደኞችህ ጋር እያወራህ እያለ ለተላከልህ የኢሜይል ወይም የሞባይል መልእክት መልስ ለመስጠት አሊያም ስልክ ለማንሳት ስትል
በተደጋጋሚ ጭውውቱን ታቋርጣለህ?□ አዎ □ አይ
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የእንቅልፍ ወይም የጥናት ጊዜህን ይሻሙብሃል?
□ አዎ □ አይ
ሚዛናዊ መሆን የሚቻልበት መንገድ
አንድ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ለምሳሌ ኮምፒውተር ወይም ሞባይል የምትጠቀም ከሆነ ከዚህ በታች የሚገኙትን አራት ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮችን መከተልህና ልታደርጋቸው የሚገቡና የማይገቡ ነገሮችን ለይተህ ማወቅህ ከአደጋ የሚጠብቅህ ከመሆኑም በላይ በአጠቃቀምህ ላይ ገደብ እንድታበጅ ይረዳሃል።
1. ይዘቱ ምንድን ነው? “አእምሮአችሁ በእነዚህ ከሁሉ በሚበልጡና ክብርን በሚያሰጡ መልካም ነገሮች የተሞላ ይሁን፤ እነዚህም መልካም ነገሮች፣ እውነትን፣ ጨዋነትን፣ ትክክለኛነትን፣ ንጽሕናን፣ ፍቅርን፣ ስመጥሩነትን የያዙ ናቸው።”—ፊልጵስዩስ 4:8 የ1980 ትርጉም
አድርግ፦ ለጓደኞችህና ለቤተሰብህ አባላት የሚያንጹ ነገሮችንና ሐሳቦችን በማካፈል ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት አጠናክር።—ምሳሌ 25:25፤ ኤፌሶን 4:29
አታድርግ፦ ሐሜት አታሰራጭ፣ የብልግና መልእክቶችንም ሆነ ምስሎችን አትላክ እንዲሁም ወራዳ የሆኑ የቪዲዮ ክሊፖችን ወይም ፕሮግራሞችን አትመልከት።—ቆላስይስ 3:5፤ 1 ጴጥሮስ 4:15
2. መጠቀም ያለብኝ መቼ ነው? “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1
አድርግ፦ መልእክት በመላላክ፣ ስልክ በመደዋወል፣ ፕሮግራም በመመልከት ወይም ጌም በመጫወት ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንደሚኖርብህ ወስን። የአምልኮ ስብሰባዎችን ለመሳሰሉ አስፈላጊ ዝግጅቶች ያለህን አክብሮት ለማሳየት በእነዚህ ጊዜያት እንደ ሞባይል ያሉ መሣሪያዎችን አጥፋ። ለተላኩልህ መልእክቶች በኋላ ላይ መልስ መላክ ትችላለህ።
አታድርግ፦ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያህን የምትጠቀምበት መንገድ ከጓደኞችህና ከቤተሰብህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ፣ ለማጥናትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የመደብከውን ጊዜ እንዲነካብህ አትፍቀድ።—3. የምቀራረበው ከእነማን ጋር ነው? “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮንቶስ 15:33
አድርግ፦ እነዚህን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ጥሩ ልማድ እንድታዳብር ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ለማጠናከር ተጠቀምባቸው።—ምሳሌ 22:17
አታድርግ፦ ራስህን አታታል፤ በኢሜይል፣ በሞባይል፣ በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የምታገኛቸው ሰዎች ያላቸውን የአቋም ደረጃ፣ አነጋገርና አስተሳሰብ መኮረጅህ አይቀርም።—ምሳሌ 13:20
4. ምን ያህል ጊዜ እያጠፋሁ ነው? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
አድርግ፦ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፍ መዝግብ።
አታድርግ፦ ጓደኞችህ ወይም ወላጆችህ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከመጠን ያለፈ ጊዜ እንደምታባክን ከነገሩህ የሚሰጡህን አስተያየት ችላ አትበል።—ምሳሌ 26:12
ቀደም ሲል የተጠቀሰው አንድሩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለመጠቀም ሲናገር ሁኔታውን እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በጣም አስደሳች ናቸው፤ ይህ የሚሆነው ግን ለአጭር ጊዜ ስንጠቀምባቸው ነው። ቴክኖሎጂ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ከመቀራረብ እንዲያግደኝ መፍቀድ እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ።”
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ ምን ይላሉ?
“ወላጆቼ ‘አንድ ፊቱን ሞባይልህን እጅህ ላይ ብናጣብቅልህ ይሻላል!’ ይሉኝ ነበር። መጀመሪያ ላይ እየቀለዱ መስሎኝ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን የምራቸውን እንደሆነ ተገነዘብኩ። አሁን መልእክት በመጻጻፍ የማጠፋውን ጊዜ ቀንሻለሁ፤ ያሁኑን ያህል ደስተኛ ሆኜ አላውቅም!”
“ኢንተርኔት ባገኘሁ ቁጥር የተላከልኝ መልእክት መኖሩን ማየት እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። የቤት ሥራዬንም ሆነ ጥናቴን ተውኩት። አሁን ይህን ልማድ እርግፍ አድርጌ ስለተውኩ ትልቅ ሸክም ከትከሻዬ ላይ የወረደ ያህል ይሰማኛል። ቁልፉ ነገር ሚዛናዊ መሆን ነው።”
[ሥዕሎች]
ጆቫርኒ
ማሪያ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ማኅበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትበት ድረ ገጽ ሱሰኛ ነበርኩ”
“ከጥቂት ዓመታት በፊት ቤተሰባችን መኖሪያ ቦታ ቀይሮ ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት መቀጠል ፈልጌ ስለነበር ፎቶ የሚቀመጥበት ድረ ገጽ አባል እንድሆን ጋበዙኝ። ግንኙነታችን እንዳይቋረጥ የሚረዳ ጥሩ ዘዴ ይመስል ነበር። ‘የምገናኘው ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር ሳይሆን ከማውቃቸው ሰዎች ጋር ብቻ ስለሆነ ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል?’ ብዬ አሰብኩ።
“መጀመሪያ ላይ ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር። በሳምንት አንዴ ድረ ገጹን ከፍቼ የጓደኞቼን ፎቶና አይና አስተያየት እጽፋለሁ፤ ከዚያም የራሴን ፎቶ አስገባና የጻፉልኝን አስተያየት አነባለሁ። ብዙም ሳይቆይ ግን ሱስ ሆነብኝ። ለእኔ ባይታወቀኝም እንኳ ረጅም ሰዓት ድረ ገጹ ላይ አሳልፍ ነበር። የጓደኞቼ ጓደኞች ከድረ ገጹ እንደማልጠፋ ሲረዱ ጓደኛቸው እንድሆን ግብዣ ያቀርቡልኝ ጀመር። እንደምታውቁት፣ አንድ ጓደኛችሁ ‘ይህ ሰው አሪፍ ነው’ ብሎ ሲነግራችሁ እናንተም ግለሰቡን ጓደኛ ታደርጉታላችሁ። ምንም ሳይታወቃችሁ 50 የኢንተርኔት ጓደኞች ይኖራችኋል።
“ብዙም ሳይቆይ ሐሳቤ ሁሉ ድረ ገጹን ስለ መጠቀም ብቻ ሆነ። ድረ ገጹን እየተጠቀምኩም እንኳ ሌላ ጊዜ መጥቼ የገባውን አዲስ ነገር የማየውና አዳዲስ ፎቶዎቼን የማስቀምጠው መቼ እንደሆነ ማሰብ እጀምራለሁ። አንድ ጊዜ የሚጻፉልኝን ሐሳቦች ሳነብ ከዚያ ደግሞ ቪዲዮ ሳስገባ ምንም ሳይታወቀኝ ሰዓቱ ይበራል።
“በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት ተኩል አለፈ፤ በመጨረሻም ሱስ እንደያዘኝ ተገነዘብኩ። አሁን ግን በኢንተርኔት አጠቃቀሜ ላይ ጥብቅ ገደብ ያበጀሁ ሲሆን ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሥነ ምግባር አቋም ካላቸው ሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቼ ጓደኝነት በመመሥረት ላይ አተኩራለሁ። አንዳንድ ጓደኞቼ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የወሰድኩት ለምን እንደሆነ አይገባቸውም፤ እኔ ግን ከስህተቴ ተምሬያለሁ።”—ኤለን፣ 18
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለምን ወላጆችህን አትጠይቃቸውም?
መዝናኛን በተመለከተ ወላጆችህን ስትጠይቃቸው የማትጠብቀው ነገር ትሰማ ይሆናል። ሸሪል እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት አባቴ ከሲዲዎቼ ውስጥ አንዱ መጥፎ እንደሆነ ጠርጥሮ ነበር። ሁለታችንም ቁጭ ብለን ሙሉውን ሲዲ እንድናዳምጠው ጠየቅኩት። እሱም ተስማማ። ሲዲውን ካዳመጠ በኋላ ምንም መጥፎ ነገር እንዳላገኘበት ነገረኝ!”
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በሚመለከት ወላጆችህን ለመጠየቅ የምትፈልገውን ጥያቄ ከዚህ በታች ጻፍ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ
በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጃችሁ ኢንተርኔት በመጠቀም ወይም የጽሑፍ መልእክት በመላላክ ብዙ ሰዓት ያሳልፋል? አሊያም ደግሞ ከእናንተ ጋር ጊዜ ከማሳለፍ ይልቅ ኤምፒ3 ማጫወቻውን ተጠቅሞ መዝናናት ይመርጣል? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ቀላሉ መንገድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያውን ከልጃችሁ መንጠቅ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁሉም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መጥፎ ነው ብላችሁ አታስቡ። እናንተም ብትሆኑ በወላጆቻችሁ ዘመን ያልነበሩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ተጠቅማችሁ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። አጥጋቢ የሆነ ሌላ ምክንያት እስከሌላችሁ ድረስ የልጃችሁን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ከመንጠቅ ይልቅ ይህን አጋጣሚ ልጃችሁ መሣሪያውን ሚዛናዊነትና ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚችል ለማሠልጠን ለምን አትጠቀሙበትም? እስቲ ይህን ማድረግ የምትችሉትን መንገድ እንመልከት።
ከልጃችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት። መጀመሪያ ጉዳዩ ያሳሰባችሁ ለምን እንደሆነ ግለጹለት። ሁለተኛ እሱ የሚላችሁን አዳምጡ። (ምሳሌ 18:13) ሦስተኛ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ፈልጉ። ተገቢ መስሎ ከታያችሁ ጥብቅ የሆነ ገደብ ከመጣል ወደኋላ አትበሉ፤ ይሁንና ምክንያታዊ ሁኑ። (ፊልጵስዩስ 4:5) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤለን እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ የጽሑፍ መልእክት መላላክ እንዳበዛሁ ሲሰማቸው ሞባይሌን አይቀሙኝም፤ ከዚህ ይልቅ ገደብ ያበጁልኛል። ወላጆቼ እንዲህ ማድረጋቸው እነሱ አጠገቤ በማይኖሩበት ጊዜም እንኳ በዚህ ረገድ ሚዛናዊ እንድሆን ረድቶኛል።”
ልጃችሁ ምክራችሁን ለመቀበል ቢያንገራግርስ? ልጃችሁ ፈጽሞ እንደማይሰማችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ከዚህ ይልቅ ትዕግሥተኞች በመሆን በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጊዜ ስጡት። በሐሳባችሁ ተስማምቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ ያደርግ ይሆናል። የበርካታ ወጣቶች ሁኔታ ሄሊ ከተባለች ወጣት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፤ ሄሊ እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ወላጆቼ ኮምፒውተር መጠቀም ሱስ እንደሆነብኝ ሲነግሩኝ በጣም ተናድጄ ነበር፤ በኋላ ግን በጉዳዩ ላይ ባሰብኩ ቁጥር እነሱ ትክክል እንደሆኑ እየገባኝ መጣ።”
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችህን ትቆጣጠራቸዋለህ ወይስ እነሱ ይቆጣጠሩሃል?