እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
● የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰሜን አሜሪካ ሕዝቦች እያንዳንዱን ሌሊት በአማካይ ከሰባት እስከ ሰባት ተኩል ሰዓት በእንቅልፍ ያሳልፋሉ። * ይሁንና እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሌሊት ተኝተህ ሳለ ከ60 እስከ 90 በሚሆኑ ደቂቃዎች ውስጥ ደጋግሞ በሚመጣው በባለ ሕልም የእንቅልፍ ዑደት ውስጥ ታልፋለህ። በዚህ የእንቅልፍ ዑደት ውስጥ አንጎላችን በጣም ንቁ የሚሆን ሲሆን ተመራማሪዎች እንደሚያምኑት አንጎላችን በዚህ ጊዜ አንድ ዓይነት ራስን የመጠገን ሥራ እያከናወነ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ የእንቅልፍ ዑደት ሲስተጓጎልና እንቅልፍ ሲጠፋ ችግሮቹ ይጠራቀሙና በሰውነታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተል ይጀምራሉ። በተጨማሪም አንጎላችን ሥራውን እንዳያከናውን ሳንካ የሚገጥመው ሲሆን ይህ ደግሞ የንቃት ማነስንና በርካታ አካላዊ ሕመሞችን ያስከትላል።
እንደ ካፌይን ያሉ ንጥረ ነገሮች እንቅልፍ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁመን ኬሚካላዊ ውሕድ ሥራውን እንዳያከናውን ሊያግዱት ይችላሉ። ሆኖም ሰውነታችን በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ከቀረ አንጎላችን ሳይታወቀን ለጥቂት ሴኮንዶች እንድናሸልብ (microsleep) የሚያደርግበት የራሱ አሠራር አለው። ዘ ቶሮንቶ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው ከሆነ “እየሠራህ ያለኸው ነገር ምንም ሆነ ምን፣ እንቅልፍ የተነፈገው አንጎልህ አለፍ አለፍ እያለ ቢያንስ ለአሥር ሴኮንድ ቢበዛ ደግሞ ከአንድ ደቂቃ ትንሽ ለሚበልጥ ጊዜ የመጀመሪያውን ደረጃ እንቅልፍ (ሸለብታ) ይተኛል።” በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት መኪና እየነዳህ እያለህ ይህ ዓይነቱ እንቅልፍ ወሰደህ እንበል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ካለው ርዝመት የሚበልጥ ርቀት ትጓዛለህ። ሰውነትህ ለበሽታ መንስኤ የሆኑ ባክቴሪያዎችን የሚዋጉትን ቲ ሴሎች የሚያመርተው በእንቅልፍ ሰዓት በመሆኑ ሰውነትህን እንቅልፍ መንፈጉ በሽታ የመከላከል አቅምህንም ሊያዳክመው ይችላል። በተጨማሪም ሰውነታችን የምግብ ፍላጎታችን የተስተካከለ እንዲሆን የሚያደርገውን ሌፕቲን የተባለ ሆርሞን የሚያመርተው በእንቅልፍ ላይ እያለን ነው። በእርግጥም ሰውነታችን ተገቢ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴና ምግብ የሚያስፈልገውን ያህል እንቅልፍም ያስፈልገዋል።
ታዲያ የሥራ መብዛት በጣም የሚያስፈልግህን እንቅልፍ እያሳጣህ ነው? የኑሮ ጭንቀትና ለነገ ብለህ ያካበትከው ንብረት የፈጠረብህ ስጋት እንቅልፍ ነስቶሃል? ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በአንድ ወቅት “ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል” ብሎ ነበር።—መክብብ 5:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 “የእንቅልፍ ዕዳ አለብህ?” የሚለውን የሚያዝያ 2004 ንቁ! ተመልከት።