መጠበቂያ ማማዎች የሞሉባት ምድር—ተራራማዋ ስቫኔቲ
መጠበቂያ ማማዎች የሞሉባት ምድር—ተራራማዋ ስቫኔቲ
የ800 ዓመት ዕድሜ ባለው የድንጋይ ማማ ላይ ወጣንና የጣራውን ወራጅ ጥብቅ አድርገን ከያዝን በኋላ በመስኮት በኩል አንገታችንን አውጥተን ወደ ታች መመልከት ጀመርን። በጆርጂያ የሚገኘው ይህ ማማ ከፍታው 25 ሜትር ሲሆን እዚያ ላይ ሆነን ስንመለከት የስቫኔቲ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በመስትያ ተበታትነው የተሠሩ በርካታ ጥንታዊ ማማዎችን አየን።
በአረንጓዴ ሣር የተሸፈነው ተረተር በበረዶ ከተሸፈኑ ሰማይ ጠቀስ ተራሮች ጋር ተዳምሮ ለአካባቢው ልዩ ሞገስ ሰጥቶታል። ወደ መካከለኛው ክፍለ ዘመን የተመለስን እስኪመስለን ድረስ ይህ ጥንታዊ ቦታ ባለው ውበት እጅግ ተማረክን።
ለነገሩ ወደዚህ ቦታ የመጣንበት ዋነኛ ዓላማ ዝነኞቹን የስቫኔቲ መጠበቂያ ማማዎች መጎብኘት ነው።በአካባቢው ያደረግነው ጉብኝት
ተራራማ ወደሆነችው ወደ ስቫኔቲ ለመሄድ ጉዟችንን የጀመርነው በጥቁር ባሕር አጠገብ ከምትገኘው ዞግዲዲ የተባለች የጆርጂያ ከተማ ነው። ገና በማለዳው ሁሉ ነገር ወገግ ብሎ ይታይ ስለነበር ከተበሊሲ ስንነሳ ጀምሮ ዕጹብ ድንቅ የሆኑትን በበረዶ የተሸፈኑ የተራራ ጫፎች ማየት ችለን ነበር። ከዚያም የኢንጉር ወንዝን ሸለቆ ተከትለን በዝግታ ጉዟችንን ቀጠልን። በደን የተሸፈነው ይህ አካባቢ ፈርን፣ አዛሊያ፣ ላውሮና ሮዶዴንድሮን በተባሉ በአበባ ያጌጡ ዕፅዋት የተሞላ ነው።
አመሻሹ ላይ የጉዞ ቡድናችን ውብ መልክዓ ምድር ወዳላት ቤኮ የተባለች መንደር ደረሰ። ይህች መንደር የምትገኘው አናቱ ላይ ሾጠጥ ብለው የወጡ መንታ ጫፎች ባሉት ኡሽባ በተባለው ማራኪና ውብ ተራራ ግርጌ ነው። የእሳት እራቶች ወደ ሻማ ብርሃን እንደሚሳቡ ሁሉ ተራራ ላይ መውጣት የሚያስደስታቸው ሰዎችም ጫፎቹ በበረዶ የተሸፈኑት ኡሽባ ተራራ ቀልባቸውን ይስበዋል። ከካውካሰስ የተራሮች ሰንሰለት አንዱ የሆነውና 4,710 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ተራራ፣ በአልፕስ ተራሮች ላይ ከሚገኘው ማተርሆርን ተራራ ጋር ስለሚመሳሰል ሰዎች ብዙውን ጊዜ “የካውካሰሱ ማተርሆርን” ብለው ይጠሩታል።
በጉዞው ደክሞንና ርቦን ስለነበር በአካባቢው አንዱን የበግ እረኛ አስቆምንና በግ ገዝተን ለራታችን አዘጋጀነው። ብዙም ሳይቆይ እንጨት አቀጣጠልንና የአገሬው ተወላጅ ከሆኑት ጓደኞቻችን ጋር በእሳቱ ዙሪያ ተቀምጠን ምስቫዲ ብለው የሚጠሩትን ሽሽ ክበብ በላን። ሽሽ ክበቡ የቀረበልን ላቫሽ ከሚባል በጆርጂያውያን ባሕል መሠረት በሸክላ ምጣድ ላይ ከተጋገረ ትኩስ ቂጣ ጋር ነው። ራታችንን በልተን እንደጨረስን ለማወራረጃ እንዲሆነን ሱፔራቪ የተባለውን የጆርጂያ ደረቅ ቀይ የወይን ጠጅ ወሰድን።
በማግስቱ ጠዋት ወደ መስቲያ ጉዟችንን ቀጠልን። መግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው በመጠበቂያ ማማ ላይ ወጥተን አካባቢውን የቃኘነው በዚህ ስፍራ ሆነን ነው፤ ባየነው ነገር በጣም ከመደመማችን የተነሳ ስቫኔቲ በዓለም ላይ ካሉት ውብ ተራራማ አካባቢዎች መካከል አንዷ መሆን አለባት ብለን አሰብን። ከመስቲያ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተራሮች የተከበበች ኡሽጉሊ የምትባል መንደር ትገኛለች። የመንደሩ ሰዎች የሚኖሩት 2,200 ሜትር ከፍታ ባለው ቦታ ላይ ነው። ኡሽጉሊ “በአውሮፓ ውስጥ በቋሚነት ሰው ከሚኖርባቸው መንደሮች ሁሉ በከፍታዋ ተወዳዳሪ የሌላት” ተብላ ተጠርታለች።
በዚህ ተራራማ አካባቢ ወደሚኖረው ማኅበረሰብ ለመድረስ ያለን ብቸኛው አማራጭ የተራራውን ጥግ ጥግ ይዞ የተሠራውን መንገድ ተከትሎ መሄድ ነበር፤ በመንገዱ ዙሪያ ጭው ያለ ገደል ያለ ሲሆን ከሥር ደግሞ ወንዝ አለ። ጉዞው አስፈሪ ቢሆንም ኡሽጉሊ እንደደረስን ያየነው ነገር መቼም ቢሆን ከአእምሯችን የሚጠፋ ባለመሆኑ ተክሰናል። በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በተሠሩ መጠበቂያ ማማዎች ዙሪያ ችምችም ብለው የተሠሩ ቤቶች አሉ። ከመንደሩ በስተጀርባ ደግሞ ግዙፉ የሽካራ ተራራ ይገኛል። ተራራው የለበሰው ነጭ የበረዶ ካባ ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ካለው ጥርት ያለ ሰማይ ጋር ተዳምሮ የፈጠረው ውበት ዓይን ያፈዝዛል።
የጆርጂያ ረጅሙ ተራራ የሆነውና 5,201 ሜትር ከፍታ ያለው የሽካራ ተራራ በዘንጊ ዎል በመባል የሚታወቀው 12 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የተራራ ሰንሰለት ክፍል ነው። ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ከፍታ ያላቸው እነዚህ ተራሮች ደግሞ 1,207 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የታላቁ የካውካሰስ ተራራ ሰንሰለት ክፍል ናቸው። በዞርንበት አቅጣጫ ሁሉ የምንመለከታቸው ሸለቆዎች ታይቶ በማይጠገብ ልምላሜ የተሞሉ ናቸው። ሆኖም አደገኛ ጉዞ ማድረግ ለሚደፍሩ ወይም ስቫኔቲን መኖሪያቸው ላደረጉ ሰዎች ካልሆነ በቀር ወደ ሸለቆዎቹ መሄድ የሚታሰብ አይደለም።
የአካባቢው ነዋሪዎች
በላይኛው ስቫኔቲ የሚኖሩት ስቫኖች የራሳቸው ቋንቋና ረጅም ታሪክ ያላቸው ሕዝብ ናቸው። ከድሮ ጀምሮ በማንም ለመገዛት አሻፈረኝ በማለታቸው የሚታወቁ ናቸው። በ18ኛው መቶ ዘመን አንድ አሳሽ፣ ስቫኖች “ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለግለሰቦች መብት በመሆኑ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል አዲስ ዓይነት ኅብረተሰብ አቋቁመዋል” በማለት የታዘበውን ገልጾ ነበር።
በስቫኔቲ እንዲህ ያለ ልዩ ነፃነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛው ምክንያት እንደ ሰንሰለት የተያያዙት በጣም ረጃጅሞቹ ተራሮች እንደ አጥር
ሆነው ሕዝቡን ከሌላው ዓለም የለዩት መሆኑና ከወራሪዎችም የጠበቋቸው መሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መጠበቂያ ማማዎቹ እያንዳንዱ ቤተሰብ እንዳይደፈር ለመጠበቅ ስላገለገሉ ነው። መጠበቂያ ማማው አልፎ አልፎ ከጠላትና ከአጎራባች መንደሮች ከሚሰነዘርባቸው ጥቃት ብሎም አጠር ያሉ ቤቶችን ከሚሸፍነው የበረዶ ናዳ ጠብቋቸዋል።በመጠበቂያ ማማው ላይ ያለው ኑሮ
በ12ኛው መቶ ዘመን የተሠራውን የአንዱን ቤተሰብ መጠበቂያ ማማ እንድንጎበኝ ተጋበዝን። በግቢው ውስጥ ጎላ ብለው የሚታዩ ሁለት ሕንፃዎች ያሉ ሲሆን እነሱም መርክቫም ተብሎ የሚጠራው መጠበቂያ ማማና ከእሱ ጋር ተያይዞ የተሠራው ኮር ተብሎ የሚጠራው መኖሪያ ቤት ናቸው። የኮሩ የመጀመሪያው ደርብ እሳት ማቀጣጠያ ምድጃ ያለው ሲሆን ይህም የሙቀትና የብርሃን ምንጭ በመሆን ያገለግላል። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላው ነገር ደግሞ የቤተሰቡ አባወራ የሚቀመጡበት የእንጨት ወንበር ነው፤ አባወራው ሚስታቸውን፣ ልጆቻቸውንና የልጆቻቸውን ሚስቶች ጨምሮ በጣም ሰፊ ቤተሰብ ያስተዳድራሉ። ሴቶቹ የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እየተቀያየሩ እንዲሠሩ ይመደብላቸዋል። ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል እህል መፍጨት፣ ዳቦ መጋገር፣ ቤት ማጽዳት፣ ለእንስሳት ምግብ መስጠትና የትልቁ ምድጃ እሳት እየነደደ እንዲቀጥል ማድረግ ይገኙበታል።
ግዙፉ መጠበቂያ ማማ ከድንጋይ የተሠራና የተለሰነ ነው። ማማው አራት ደርቦች አሉት። በመሆኑም ከጎኑ ካለው ባለ ሁለት ደርብ መኖሪያ ቤት ከፍ ብሎ ይታያል። ከቤቱ ወደ ማማው ውስጥ ስንገባ ደብዘዝ ያለውን ብርሃን ዓይናችን እስኪለምደው ድረስ ትንሽ ጊዜ ወሰደብን። የመጠበቂያ ማማው የታችኛው ደርብ የሚያገለግለው ውኃ፣ ዱቄት፣ ፍራፍሬ፣ አይብ፣ ወይንና ሥጋ ለማስቀመጥ ነው።
አስገዳጅ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ቤተሰቡ በታችኛውና በመካከለኛው ደርቦች ውስጥ ይተኛል። ጣሪያው በጠፍጣፋ የድንጋይ ንጣፍ የተሠራው የላይኛው ደርብ እንደ መስኮት ያሉ ቀዳዳዎች ያሉት ሲሆን በዋነኝነት የሚያገለግለው ለውጊያ ነው። በ19ኛው መቶ ዘመን ላይ ስቫኔቲን የጎበኘ አንድ ሰው “በአካባቢው ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል ምንም ዓይነት ባለሥልጣን ባለመኖሩ ሕዝቡ ምንጊዜም ለችግሩ መፍትሔ አድርጎ የሚወስደው ውጊያን ነበር” በማለት ዘግቧል። ስለዚህ እያንዳንዱ ቤተሰብ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል ሁልጊዜም ለውጊያ ዝግጁ ነበር።
ወደ ቤታችን የተመለስነው በስቫኔቲ ባሉት አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በተንጸባረቀው ውበት ላይ እያሰላሰልን ስለነበር ልባችን ለይሖዋ ባለን የአድናቆት ስሜት ተሞላ። ጥንት በስቫኔቲ የመጠበቂያ ማማዎች ውስጥ የኖሩ ሰዎች ወደፊት በሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ አላቸው። በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ራሱን ለመከላከል መጠበቂያ ማማም ሆነ ምንም ዓይነት ምሽግ መሥራት አያስፈልገውም። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ወቅት “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—ሚክያስ 4:4፤ ሮም 8:21, 22
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Top: Paata Vardanashvili