ንድፍ አውጪ አለው?
ንዝረትን ውጦ የሚያስቀር የግንደ ቆርቁር ጭንቅላት
● በጂ-ፎርስ * መለኪያ ከ80 እስከ 100 የሚደርስ ምት በጭንቅላትህ ላይ ቢያርፍ ራስህን እስከመሳት ሊያደርስህ ይችላል። ግንደ ቆርቁር የተባለው ወፍ ግን የዛፍ ግንድ ሲቆረቁር እስከ 1,200 ጂ-ፎርስ የሚደርስ ምት ጭንቅላቱ ላይ ቢያርፍም ምንም ጉዳት አይደርስበትም። ታዲያ ይህ ወፍ ራሱን መሳት ይቅርና ራስ ምታት እንኳ ሳይዘው ይህን ተግባሩን የሚያከናውነው እንዴት ነው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ተመራማሪዎች የግንደ ቆርቁር ጭንቅላት ንዝረትን ውጦ እንዲያስቀር የሚያስችሉ አራት ነገሮች እንዳሉት ደርሰውበታል።
1. ጠንካራ ሆኖም መለመጥ የሚችል መንቁር
2. ሃይኦድ ማለትም በራስ ቅሉ ዙሪያ የሚገኝ የመለጠጥ ባሕርይ ያለው ለስላሳ አጥንት
3. በራስ ቅሉ ላይ የሚገኝ እንደ ስፖንጅ ያለ አጥንት
4. ሰረብራል ስፓይናል የተባለ ፈሳሽ የሚገኝበት በራስ ቅሉና በአንጎሉ መካከል ያለ አነስተኛ ስፍራ
እነዚህ አራቱ ነገሮች እያንዳንዳቸው ንዝረትን ውጦ የማስቀረት ችሎታ አላቸው፤ ይህም ግንደ ቆርቁሩ በአንጎሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት በሴኮንድ 22 ጊዜ አንድን የዛፍ ግንድ ለመቆርቆር ያስችለዋል።
ተመራማሪዎች የግንደ ቆርቁርን ጭንቅላት በመኮረጅ እስከ 60,000 ጂ-ፎርስ የሚደርስን ምት መቋቋም የሚችል ልባስ መሥራት ችለዋል። ይህ ግኝታቸው ብዙ ነገሮችን ለመሥራት በር የሚከፍትላቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ የተሻለ የበረራ ሁኔታ መመዝገቢያ ሣጥን መሥራት ይገኝበታል፤ በአሁኑ ጊዜ ያለው የበረራ ሁኔታ መመዝገቢያ ሣጥን መቋቋም የሚችለው እስከ 1,000 ጂ-ፎርስ ብቻ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የክሬንፊልድ ዩኒቨርስቲ ኢንጂነር የሆኑት ኪም ብላክበርን ስለ ግንደ ቆርቁር ጭንቅላት የተገኘው እውቀት “መጀመሪያ ላይ ፈጽሞ የማይፈታ የሚመስልን ችግር፣ ተፈጥሮ በተራቀቀ መንገድ የተሠሩ የተለያዩ ክፍሎችን እርስ በርስ በማቀናጀት እንዴት መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚችል የሚያሳይ አስደናቂ ምሳሌ ነው” ብለዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ንዝረትን ውጦ የሚያስቀረው የግንደ ቆርቁር ጭንቅላት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ጂ-ፎርስ፣ የስበት ኃይል ወይም በፍጥነት እየተንቀሳቀሰ ያለ ነገር በሌላ አካል ላይ ሲያርፍ የሚያሳድረውን ግፊት ወይም ምት መለኪያ ነው።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
1
2
3
4
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Redheaded woodpecker: © 2011 photolibrary.com