የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ፍትሕ ያመጣል
የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ፍትሕ ያመጣል
መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለው ዓለም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም እንደሚተካ ይገልጻል። ከዚህም በላይ መጪውን አዲስ ዓለም የሚያስተዳድረው አንድ መንግሥት ብቻ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 11:15) ታዲያ የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መዛባትን የሚያስወግደው እንዴት ነው? ይህን የሚያደርገው በሁለት መንገዶች ነው።
1. የአምላክ መንግሥት ፍትሕ የጎደለውን ሰብዓዊ አገዛዝ ያጠፋል። ዳንኤል 2:44 “በነዚያ ነገሥታት [መንግሥታት] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት ይናገራል።
2. የአምላክ መንግሥት ክፉዎችን ሲያጠፋ ፍትሕን የሚወዱ ሰዎች በሕይወት እንዲተርፉ ያደርጋል። መዝሙር 37:10 “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም” ይላል። ቁጥር 28 ደግሞ “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል” በማለት ይናገራል።
እነዚህ የአምላክ ‘ታማኞች’ ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ የተናገረው ነገር ሲፈጸም ይመለከታሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” (ማቴዎስ 6:10) ለመሆኑ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚገዛበት ጊዜ . . .
ሙስናና ጭቆና ያከትማል። ዕብራውያን 1:9 ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ “ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ” ይላል። ፍትሐዊ ገዥ የሆነው ኢየሱስ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። . . . ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።”—መዝሙር 72:12-14
ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል። “ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።” (መዝሙር 67:6) “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።” (መዝሙር 72:16) ኢየሱስ በአንድ ወቅት፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ የመገበ ሲሆን ይህም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ለሚፈጽመው ነገር እንደ ቅምሻ የሚሆን ነው።—ማቴዎስ 14:15-21፤ 15:32-38
የሰው አቅም ውስንነት ለፍትሕ እንቅፋት መሆኑ ይቀራል። “[ከአምላክ] እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።” (ዕብራውያን 4:13) ክርስቶስን በተመለከተ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል።”—ኢሳይያስ 11:3, 4
የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛበት ጊዜ ቀርቧል
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደው የዓለም ሁኔታ መጨረሻው በጣም መቅረቡን ይጠቁማል። መዝሙር 92:7 “ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣ ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣ ለዘላለሙ ይጠፋሉ” ይላል። ታዲያ የአምላክን ሞገስ ከሚያሳጡ ነገሮች መራቅና እሱ በሕይወት እንዲተርፉ ከሚያደርጋቸው ሰዎች መካከል መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3
ይህን ውድ እውቀት ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት እንደ ሃይዲ፣ ዶረቲና ፊሮዲን ሁሉ አንተም ስለዚህ ጉዳይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለምን አትወያይም? ጥያቄዎችህን ያለ ምንም ክፍያ ሊመልሱልህ ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሕይወት ራሱ ፍትሕ የጎደለው በሚመስልበት ጊዜ
በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ኤመሊ ገና በሰባት ዓመት ዕድሜዋ የደም ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ተረጋገጠ። እንደ ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ ያሉ ቀላል በሽታዎች አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሟቸው እኩዮቿ በተቃራኒ ኤመሊ ኬሞቴራፒን ጨምሮ ከባድ ሕክምናዎችን ለዓመታት መከታተል ግድ ሆኖባታል። ኤመሊ “የደም ካንሰር አስፈሪ በሽታ ነው!” በማለት ተናግራለች።
ኤመሊ በሕይወቷ ውስጥ የገጠማትን ይህን ከባድ ችግር መቋቋም ግድ ቢሆንባትም በተስፋ መቁረጥ ስሜት አልተዋጠችም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንግሥት ሥር “ታምሜአለሁ” የሚል ሰው የማይኖርበትን ጊዜ በተስፋ ትጠባበቃለች። (ኢሳይያስ 33:24) ኤመሊ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በጣም የምወደው ጥቅስ ማርቆስ 12:30 ላይ የሚገኘው ‘አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ’ የሚለው ነው። ወደ ይሖዋ ስጸልይ ብርታት ይሰጠኛል። አሳቢ በሆነ ቤተሰብና ጉባኤ ውስጥ ስለምኖር እንዲሁም ገነት በሚሆነው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ይህ ተስፋ እጅግ በጣም ረድቶኛል።”
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ዘር በሙሉ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ እንዲሁም እውነተኛ ፍትሕ በሰፈነበትና ከጭፍን ጥላቻ ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ በደስታ ይኖራል