የዓለም መጨረሻ የምታስበው ዓይነት ላይሆን ይችላል
ባለፈው ርዕስ ላይ ያየናቸው ስለ ዓለም መጨረሻ የቀረቡ ሐሳቦች ያንን ጊዜ የመዓት ቀን እንደሚሆን አድርገው የሚገልጹት ከመሆኑም ባሻገር ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ሁሉም የተመሠረቱት በሰዎች ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ ሲሆን ሰዎች ደግሞ ወደፊት የሚሆነውን በትክክል መገመት እንደማይችሉ ታሪክ ያሳያል። ሁለተኛ፣ በእነዚያ ሐሳቦች መሠረት የሰው ልጆች ከጥፋቱ መትረፋቸው አጠያያቂ ሲሆን ከተረፉም እንኳ በአጋጣሚ ነው። ሦስተኛ፣ ከዓለም መጨረሻ የሚተርፉት ሰዎች በሕይወት ለመቆየት ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይጠይቅባቸዋል።
በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚገልጸው ነገር ለማመን የሚከብድ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ታላቅ ለውጥ መምጣቱ የተረጋገጠ ነገር እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሁሉ ከጥፋቱ የመትረፍ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር በእሳት ጋይታ አመድ እንደምትሆን አሊያም በጣም ቀዝቅዛ ግግር በረዶ እንደምትሆን አይናገርም። እንዲያውም በተቃራኒው መላዋ ምድር ተለውጣ ገነት ትሆናለች።
ይሁንና ብዙ ሰዎች እንዲህ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መቀበል ይከብዳቸዋል። ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታላቅ መከራ፣ ስለ አርማጌዶን፣ ስለ ሺህ ዓመት ግዛትና ስለ ገነት የሚሰጠውን ትምህርት እንደ ተረት ይቆጥሩታል። የሃይማኖት ሊቃውንት ስለ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ማብቂያ የሌላቸው ውይይቶችንና ክርክሮችን ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ እንደመሰላቸው ተርጉመዋቸዋል። እነዚህ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ንድፈ ሐሳቦች እርስ በርስ የማይስማሙ አልፎ ተርፎም የሚጋጩ ናቸው። ብሩስ ሮቢንሰን የተባሉት ደራሲ የመጨረሻውን ዘመን አስመልክተው እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ከሌላ ከማንኛውም የሕዝበ ክርስትና ትምህርት ይልቅ በጣም የተድበሰበሱ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች የተጻፉት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሳይሆን አይቀርም።” ታዲያ ይህ ምን አስከትሏል? ግራ መጋባት።
ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙት ሐሳብ ግን የተድበሰበሰ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተላከ መልእክት ሲሆን አምላክ ደግሞ ወደፊት ስለሚመጣው ነገር ግራ እንድንጋባ አይፈልግም። ቀጥሎ፣ ብዙ ሰዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና መጽሐፍ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ እንመለከታለን። ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።
ምድርና የሰው ዘር ይጠፉ ይሆን?
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
የሚጠፉ ሰዎች ይኖራሉ?
“ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
አምላክ ከዚህ ቀደም በክፉ ሰዎች ላይ እርምጃ ወስዶ ያውቃል?
አምላክ “የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም። በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆን የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:5, 6
አምላክ የፍርድ እርምጃ የሚወስድበትን ቀን ማወቅ እንችላለን?
“ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም። በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም። የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:36-39
መጨረሻው በቅርቡ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነገር አለ?
“በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፣ ኃይሉን ግን ይክዳሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
የሰው ዘር ወደፊት በምድር ላይ ምን ዓይነት ሕይወት ይመራል?
አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4
አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል”
ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሁሉንም ነገር ባይነግሩንም የሰው ልጆች ከምድር ገጽ እንደማይጠፉ ያረጋግጡልናል። የወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ከምንችለው በላይ እጅግ አስደናቂ ይሆናል። አንተም፣ ይሖዋ አምላክ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እንደሚችል እርግጠኛ በመሆን በዚህ ተስፋ ላይ እምነት ልትጥል ትችላለህ።