በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዩናይትድ ስቴትስ

ጥቅምት 29, 2012 ላይ በጀመረው ሳምንት በኒው ዮርክ ሲቲ የተፈጸመው ነፍስ ግድያ፣ ከባድ ወንጀልና ዝርፊያ በ2011 በተመሳሳይ ወቅት ላይ በአምስት ቀናት ውስጥ ከተፈጸመው ወንጀል ጋር ሲነጻጸር በአስገራሚ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ምክንያቱ ምን ይሆን? ሳንዲ የተባለችው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የዩናይትድ ስቴትስን ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ አውድማ ስለነበረ ነው፤ በዚህም የተነሳ በብዙ ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ተከስቶ ነበር። የኒው ዮርክ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ፖል ብራውን “የተፈጥሮ አደጋ ወይም ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትል ሁኔታ [መስከረም 11, 2001 የተከሰተው ዓይነት የሽብርተኞች ጥቃት] ከደረሰ በኋላ የተለመደው ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሲቀንስ ይታያል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና ቤት ሰብሮ በመግባት የሚካሄደው ዝርፊያ ተባብሶ የነበረ መሆኑ ብራውንን አላስደነቃቸውም። “በርካታ አካባቢዎች መብራት ጠፍቶባቸው ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

አንታርክቲካ

የሳይንስ ሊቃውንት በአንታርክቲካ ያለው የአካባቢው ሥነ ምህዳር፣ አገር በቀል ባልሆኑ ወራሪ ዝርያዎች አደጋ እየተጋረጠበት በመሆኑ ስጋት ገብቷቸዋል። በየዓመቱ ወደ አህጉሩ የሚመጡ በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ሳይታወቃቸው በአብዛኛው በቡትስ ጫማቸው ወይም በሻንጣቸው አማካኝነት በነፍስ ወከፍ በአማካይ 9.5 የሚሆኑ ዘሮችን ይዘው እንደሚመጡ ተገምቷል። ከዚህ ቀደምም በምዕራባዊ አንታርክቲካ ባሕረ ገብ መሬት ላይ በዚህ መንገድ የመጡ እንግዳ የዕፅዋት ዝርያዎች በብዛት ተገኝተዋል።

ኔዘርላንድ

አንዲት የ83 ዓመት አረጋዊት ሴት በባለ ስሪዲ የሌዘር መሣሪያ አማካኝነት ታይታኒየም ከሚባል እንደ ብረት ያለ ማዕድን የተሠራ ሰው ሠራሽ መንገጭላ የተገጠመላቸው የመጀመሪያዋ ሰው ሆነዋል። መንጋጋቸው በአጥንት ኢንፌክሽን ከጥቅም ውጭ የሆነባቸው እኚህ ታካሚ አሁን ያለምንም ችግር መብላት፣ መተንፈስና መናገር ችለዋል። የሌዘር መሣሪያው የታይታኒየም ቅንጣቶችን ደረጃ በደረጃ እያነባበረ በማጣበቅ ለሴትየዋ አዲስ መንገጭላ ከሠራ በኋላ በቀዶ ጥገና ተገጥሞላቸዋል።

ጀርመን

በጀርመን ሲጋራ ማጨስ በከፊል በታገደባቸው ሕዝብ በሚያዘወትራቸው አንዳንድ አካባቢዎች እገዳው በተጣለ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአንድ ቡድን ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር፤ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው ከልብ ችግር ጋር በተያያዘ ደረት ላይ የሚሰማ ሕመም አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር 13.3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በልብ ድካም ምክንያት የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ደግሞ 8.6 በመቶ ቀንሷል።