መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጤና
አምላክ ለሰውነታችን የምናደርገው እንክብካቤ ያሳስበዋል?
“ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ።”
—ምሳሌ 23:20
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ አይደለም፤ ደግሞም ሰዎች የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር የሚቆጣጠር መመሪያ አልያዘም። ያም ቢሆን አምላክ፣ ጤንነትን ስለ መጠበቅ ያለውን አመለካከት የሚጠቁሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ሐሳቦችን ማወቅህ ይጠቅምሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ለሰውነታችን የምናደርገው እንክብካቤ አምላክን እንደሚያሳስበው የሚጠቁሙ በርካታ ሐሳቦች ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሆዳምነትንና ሰካራምነትን ጨምሮ ከልክ በላይ የሚደረጉ ጎጂ ነገሮችን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:20) አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ በሽታዎች እንዳይስፋፉ ለመቆጣጠር ከተቻለም እንዳይከሰቱ ለመከላከል መደረግ ያለባቸው ነገሮች ተካትተዋል። በተጨማሪም ሕጉ በሰው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚረዱ የደህንነት መመሪያዎችን ይዟል። (ዘዳግም 22:8) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰውነታችንን እንድንንከባከብና ጤንነታችንን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ነገር እንድናደርግ ያበረታታል።
የምንታመምበትን ምክንያት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።”
—ሮም 5:12
ሰዎች ምን ይላሉ?
ብዙዎች በሽታ ሰው በዝግመተ ለውጥ ሲገኝ በአጋጣሚ የተከሰተ ችግር እንደሆነ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ክፉ መናፍስት ያሉ ሚስጥራዊ ኃይሎች የጤና መቃወስ እንደሚያስከትሉብን አድርገው ያስባሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንታመመው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በአምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት እንደሆነ ይናገራል። (ሮም 5:12) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ከማመፃቸው በፊት ፍጹም ጤንነት ነበራቸው። አፍቃሪ የሆነውን አምላክ እንክብካቤ ካጡ እንደሚሞቱ ያውቁ ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይሁንና ሆን ብለው ከአምላክ ጋር እንዲቆራረጡ የሚያደርግ ነገር ፈጸሙ፤ በመሆኑም ፍጽምናቸውን አጡ። *
ፍጽምናቸውን ያጡት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለእኛም አለፍጽምናን አወረሱን። በመሆኑም የጤና እክሎችን ለማስወገድ የቱንም ያህል ጥረት ቢደረግ መታመማችን አይቀርም።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
አምላክ ያወጣቸውን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው መመሪያዎች በመታዘዝ ከእሱ ጋር እርቅ ከፈጠርክ ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ፍጹም ጤንነት አግኝተህ መኖር እንደምትችል መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ኢሳይያስ 33:24) አምላክ ሕመምን፣ በሽታንና ሞትን ለማስወገድ ቃል ገብቷል።—ራእይ 21:3, 4
መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና እርዳታ ማግኘትን ይቃወማል?
“ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”
—ማቴዎስ 9:12
ሰዎች ምን ይላሉ?
አንዳንዶች የሕክምና እርዳታ ከማግኘት ይልቅ ሃይማኖታዊ ፈውስ (ወይም የእምነት ፈውስ) ማግኘት የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በጥንት ዘመን በነበሩ የአምላክ ሕዝቦች መካከል የጤና እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች የነበሩ ሲሆን አምላክ ይህን ሙያቸውን አልተቃወመም። (ዘፍጥረት 38:28፤ ቆላስይስ 4:14) እነዚህ ሰዎች ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎችንና ቅባቶችን በመጠቀም እንዲሁም ለሕመምተኞቹ አንድ ዓይነት የአመጋገብ ሥርዓት በማዘዝ ወይም በሌሎች የሕክምና ዘዴዎች ተጠቅመው ሕክምና በመስጠታቸው አምላክ እንዳልተደሰተ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። እንዲያውም ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 9:12
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጤነኛ ለመሆን ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕት መከፈል አለበት የሚለውን አመለካከት አይደግፍም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዛሬው ጊዜ የሚከናወነውን የእምነት ፈውስ አይደግፍም። ከዚህም ሌላ በመናፍስታዊ ድርጊቶች አማካኝነት ፈውስ ለማግኘት መሞከር በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። (ገላትያ 5:19-21) የጤና እክል በሚያጋጥመን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያወግዛቸው መንገዶች መጠቀም ተገቢ ባይሆንም የሚቻል ከሆነ ወዲያውኑ ጥሩ ሕክምና ለማግኘት መሞከር የጥበብ እርምጃ ነው።
^ စာပိုဒ်၊ 10 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ፍጹም” እና “ፍጽምና” የሚሉትን ቃላት የተጠቀምነው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክ ሲፈጥራቸው የነበራቸውን ጤንነት ለማመልከት ነው፤ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሕመም፣ በበሽታና በሞት አይጠቁም ነበር።