አገሮችና ሕዝቦች
ፓናማን እንጎብኝ
ፓናማ ይበልጥ የምትታወቀው የአትላንቲክና የፓስፊክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኝ የባሕር መተላለፊያ ቦይ ያላት በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም። ፓናማ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካን የምታገናኝ እንደመሆኗ መጠን ውቅያኖሶቹን ብቻ ሳይሆን ሕዝቦችንም ታገናኛለች። የበርካታ ዘርና ባሕሎች መናኸሪያ ነች። አብዛኞቹ ዜጎቿ ጥንታዊ የአገሬው ተወላጆችና የአውሮፓውያን ድብልቅ ናቸው።
ከስፔን የመጡ አገር አሳሾች በ1501 ፓናማ ሲደርሱ የአገሬው ተወላጅ የሆኑ በርካታ ጥንታዊ ማኅበረሰቦችን ያገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ቀደም ሲል ኩና ተብለው ይጠሩ የነበሩት ጉናዎች ይገኙበታል። ብዙዎቹ ጉናዎች የሚኖሩት በሳን ብላስ ደሴቶች እንዲሁም በፓናማና በኮሎምቢያ ወሰን አቅራቢያ በሚገኘው የፓስፊክ ጠረፍ አካባቢ ነው። ጉናዎች አደን የሚወጡ ከመሆኑም ሌላ ከግንድ በተፈለፈሉ ታንኳዎች ታግዘው ዓሣ ያጠምዳሉ፤ እንዲሁም ለቀለብ የሚሆን እህል ያመርታሉ።
በጉና ማኅበረሰብ አንድ ወንድ ሚስት ሲያገባ የሚስቱን ቤተሰቦች በሥራ እያገዘ አብሯቸው ይኖራል። ሚስቱ ሴት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ ግን ቤተሰቡን ይዞ ከአማቶቹ በመለየት የራሱን ቤት ማስተዳደር ይችላል።
በፓናማ 300 የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ። ከስፓንኛ በተጨማሪ በቻይንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጉጃራቲ፣ በጉና፣ በሄይቲኛ ክሪኦል፣ በንጋቤሬ እንዲሁም በፓናማ የምልክት ቋንቋ ስብሰባዎች ይመራሉ።