በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሃሎዊን—እውነታው ምንድን ነው?

ሃሎዊን—እውነታው ምንድን ነው?

አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሃሎዊን ይከበራል? በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ሃሎዊን በስፋት የሚታወቅ በዓል ሲሆን በየዓመቱ ጥቅምት 31 ቀን ይከበራል። ይሁን እንጂ ከሃሎዊን አከባበር ጋር የተያያዙ ልማዶች በሌሎች የዓለም ክፍሎችም በብዛት ይታያሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ሃሎዊን በሚለው ስም ባይታወቁም ተመሳሳይ ልማዶች የሚንጸባረቁባቸው ሌሎች በዓላት አሉ፤ በእነዚህ በዓላት ላይ ሰዎች ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ለመገናኘት ጥረት ያደርጋሉ። ይህም ከሙታን መናፍስት፣ ከአድባር፣ ከጠንቋዮች ሌላው ቀርቶ ከዲያብሎስና ከአጋንንት ጋር እንኳ መገናኘትን ይጨምራል።— “በዓለም ዙሪያ የሚከበሩ ከሃሎዊን ጋር የሚመሳሰሉ በዓላት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ምናልባት አንተ መናፍስታዊ ኃይላት አሉ ብለህ አታምን ይሆናል። በሃሎዊን ወይም ተመሳሳይ በሆኑ ሌሎች ክብረ በዓላት ላይ የምትካፈለው የደስታ ጊዜ ለማሳለፍና ልጆችህ የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለመርዳት ብለህ ይሆናል። ብዙ ሰዎች ግን በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ እነዚህ ክብረ በዓላት ጎጂ እንደሆኑ ይሰሟቸዋል፦

  1. ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አሜሪካን ፎክሎር እንደሚለው “ሃሎዊን ከመንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ለመገናኘት ታስቦ የሚደረግ ክብረ በዓል ነው፤ አብዛኞቹ ፍጥረታት ደግሞ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው።” ( “ከሃሎዊን ጋር የተያያዘ የጊዜ ሰሌዳ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በተመሳሳይም እንደ ሃሎዊን ያሉ ብዙ ክብረ በዓላት ሥረ መሠረታቸው አረማዊ ሲሆን ከቀድሞ አባቶች አምልኮ ጋርም በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች በዓሉ በሚከበርበት ዕለት፣ የሙታን መናፍስት ብለው ከሚጠሯቸው የሞቱ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ጥረት ያደርጋሉ።

  2. ሃሎዊን በዋነኝነት የአሜሪካውያን በዓል እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም ይህን በዓል የሚያከብሩ አገሮች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓሉን ማክበር የጀመሩ ብዙ ሰዎች፣ ከመናፍስታዊና ከአስማታዊ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የሃሎዊን ምልክቶች፣ ጌጣጌጦችና ልማዶች ምንጫቸው አረማዊ አምልኮ መሆኑን አይገነዘቡም።—  “ምንጫቸው ከየት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

  3. የጥንቶቹን የአውሮፓ ኬልቶች ሥርዓተ አምልኮ የሚከተሉ በሺህ የሚቆጠሩ የዊካ እምነት (የጥንቆላ ሥርዓት የሚከተል ሃይማኖት) ተከታዮች ዛሬም ሃሎዊንን የሚጠሩት ሳምሄን በተባለው ጥንታዊ ስሙ ሲሆን በዓመቱ ውስጥ እጅግ ቅዱስ እንደሆነ ምሽት አድርገው ይቆጥሩታል። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው ጋዜጣ አንዲት ጠንቋይ ነኝ የምትል ሴት “ክርስቲያኖች ልብ ሳይሉት የእኛን በዓል አብረውን እያከበሩ ነው። . . . በዚህም ተደስተናል” በማለት እንደተናገረች ጽፏል።

  4. እንደ ሃሎዊን ያሉ ክብረ በዓላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ።”—ዘዳግም 18:10, 11፤ በተጨማሪም ዘሌዋውያን 19:31⁠ን እና ገላትያ 5:19-21⁠ን ተመልከት።

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ስለ ሃሎዊንና ተመሳሳይነት ስላላቸው ሌሎች በዓላት አመጣጥ ማወቅህ ጥሩ ይሆናል። በዚህ ረገድ የተሟላ ግንዛቤ ማግኘትህ እነዚህን በዓላት ከማያከብሩ ሰዎች መካከል እንድትሆን ሊያነሳሳህ ይችላል።

“ክርስቲያኖች ልብ ሳይሉት የእኛን በዓል አብረውን እያከበሩ ነው። . . . በዚህም ተደስተናል።” —ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተሰኘው ጋዜጣ አንዲት ጠንቋይ ነኝ የምትል ሴት የሰጠችውን ሐሳብ ጠቅሶ የተናገረው

^ አን.37 “ቅዱስ” የሚል ትርጉም ያለው ጥንታዊ የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ኦል ሃሎውስ ዴይ ወይም ኦል ሴንትስ ዴይ (“የሁሉም ቅዱሳን ቀን”) የሞቱ ቅዱሳን የሚታወሱበት በዓል ነው። የኦል ሃሎውስ ዴይ የዋዜማ ምሽት ኦል ሃሎ ኢቭን ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ይህ ስም አጥሮ ሃሎዊን መባል ጀመረ።